የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ፔንታገን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የእግረኛ እና የአየር ወለድ አባላት የተካተቱበት ጦር መላኩን ለቢቢሲ አረጋገጠ።
የፔንታገን ቃል አቀባይ ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት የተወሰኑ የ82ኛው አየር ወለድ ዋና ዕዝ፣ የተወሰኑ “ልዩ ኃይሎች” እና የአንደኛ ብርጌድ አባላት በመካለኛው ምሥራቅ ይሰማራሉ።
ቃል አቀባዩ ለደኅንነት በሚል ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እያመሩ ያሉት ኃይሎች የተወጣጡባቸው ክፍሎች በጦርነቱ ውስጥ ምን ዓይነት ተሳትፎ ሊኖራቸው እንደሚችል ያሳያል።
በኖርዝ ካሮላይና መቀመጫውን ያደረገው 82ኛው አየር ወለድ በመደበኛ ውጊያ ውስጥ ዋነኛው ጥቃት ፈጻሚ ቡድን እንደሆነ ይታመናል። የተወሰኑ የቡድኑ አባላት በ18 ሰዓት ውስጥ በየትኛውም ዓለም ክፍል ለመሰማራት ሁሌም በተጠንቀቅ ላይ ናቸው።
እነዚህ ወታደሮች ዒላማ ወደሚደረጉ አካባቢዎች በፓራሹት በመውረድ ወይንም በሂሊኮፕተር በመሄድ ተልዕኳቸውን ይፈጽማሉ።
ይህም በኢራን የኻርግ ደሴትን ወይንም ሌላ ቁልፍ ግዛትን በቁጥጥር ስር ለማዋል ያስችላል።
ነገር ግን ጦሩ በእንቅስቃሴ ውስጥ የሚፈጸም ጥቃት ላይ ስለሚያተኩር ቀጣይነት ላለው ውጊያ የሚያገለግል ከባድ ጦር መሣሪያ አይታጠቅም።
መቀመጫውን ኒው ዮርክ ያደረገው አንደኛ ብርጌድ የጥቃት ቡድን ደግሞ በተራራማ አካባቢዎች በሚደረግ ጦርነት የተካነው 10ኛው ዲቪዥን አባል ሲሆን፣ ለተራዘመ ጦርነት የሚያገለግሉ ከባድ መሣሪያዎችን ይታጠቃል።
