መቀመጫውን በካናዳ ያደረገው እና በOMNI ቻናል በRogers ኔትወርክ ስርጭት የሚያቀርበው አዲስ ቅኝት ቴሌቪዥን አንደኛ ዓመቱን በማስመልከት ባዘጋጀው የሥነ ጽሑፍ ውድድር አሸናፊ ለሆኑት ሦስት ተወዳዳሪዎች የገንዘብ ሽልማታቸውን በይፋ አበርክቷል።
ነዋሪነታቸው በአዳማ፣ ሻሸመኔ እና አቃቂ ለሆኑት ለእነዚህ ፀሐፊያን የገንዘብ ሽልማቱን ያበረከተው የቶሮንቶው TAS የህግ ቢሮ ሲሆን፣ የሽልማት ሥነ ሥርዓቱም የቀድሞው ዳግማዊ ምኒልክ አማካሪ የነበሩት አልፍሬድ ኢልግ መኖሪያ ቤት በነበረው በተወዳጁ አብዲ ነጋሽ የቅርሳ ቅርስና አንቲክ መዘክር ውስጥ ተካሂዷል።
በዚሁ መርሃ ግብር ላይ በውድድሩ ከፍተኛ ነጥብ ያመጡት ተወዳዳሪዎች በቅደም ተከተል ይፋ የተደረጉ ሲሆን፣ ፍቃዱ አሥራት የ1ኛ ደረጃ አሸናፊ በመሆን የ50,000 ብር፣ ቃልኪዳን ፈለቀ የ2ኛ ደረጃ አሸናፊ በመሆን የ40,000 ብር፣ እንዲሁም ሔኖክ ካሳ የ3ኛ ደረጃ አሸናፊ በመሆን የ30,000 ብር ተሸላሚ ሆነዋል።
የውድድሩ ዳኛ ደራሲ፣ ገጣሚና ጋዜጠኛ ሁሴን ከድር መርሃ ግብሩን በስኬት በማስተባበር ተወዳዳሪዎቹ ባሳዩት የፈጠራ ችሎታ የተሰማውን ደስታ ገልጿል። የአዲስ ቅኝት ቴሌቪዥን ፕሮዲዩሰሮች ጋዜጠኛና ደራሲ ሶስና አሸናፊ እና ገዛኸኝ መኮንን ለተወዳዳሪዎች፣ ለዳኞችና ለዝግጅቱ ስኬት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ይህ የሥነ ጽሑፍ ውድድር በኢትዮጵያውያን ደራሲያንና ወጣት ተሰጥኦዎች መካከል የፈጠራ ሥራን ለማበረታታትና የሥነ ጽሑፍ ባህልን ለማጠናከር ያለመ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ አዲስ ቅኝት ሚዲያም በሥነ ጽሑፍና ኪነጥበብ ማኅበረሰቦችን ማስተሳሰሩን እንደሚቀጥል አረጋግጧል።
(ይትባረክ ዋለልኝ)
