ግዮን መጽሔት :- አዲስ ዓመት የዘመን መለወጫ በዓል ብቻ ሳይሆን የኅሊና መመርመሪያ፣ ያለፈውን መለስ ብሎ ማያ እንዲሁም መጭውን ጊዜ በተስፋና በብርሃናዊ ርእይ ለመቃኘት የሚጣደፉበት ታላቅ የታሪክ ምዕራፍ ነው፡፡ የ2018 ዓ.ም የዘመን ገጽ ተዘግቶ አዲሱ 2019 ዓ.ም ሲከፈት፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ በታሪኳ አይታው የማታውቀውን ያህል ውስብስብ ከሆኑ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ፈተናዎች፣ ድንቅ የቴክኖሎጂ ዕድሎች እና ማኅበራዊ ውጥረቶች ጋር ፊት ለፊት ተጋፍጣ ትገኛለች፡፡ ይህንን የታሪክ መጋጠሚያ መሠረት በማድረግ «ግዮን» መጽሔት በልዩ ልዩ ዘርፎችና ሙያዎች ውስጥ ከሚገኙ አራት የሀገራችንን ታዋቂና አንጋፋ ባለሙያዎች ጋር የሚከተለውን ቆይታ አድርጋለች፡፡ ከጋዜጠኛ ኤልያስ አወቀ ጋር የነበረንን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበናል ። መልካም ንባብ !
ግዮን፦ በ2018 ዓ.ም በጣም ያዘኑበትን እና የተደሰቱበትን አጋጣሚ ቢያካፍሉን?
ኤልያስ፦ በ2018 ዓ.ም የዓለም ሥርዓት ፈርሶ ወዳደገኛ ሁኔታ ባቀናበት ወቅት ታላላቅ ጦርነቶች መከሰታቸው እጅግ አሳዝኖኛል፡፡ ሌላው አሳዛኝ አጋጣሚ ደግሞ ዶናልድ ትራምፕ ካናዳን የአሜሪካ ክልል አደርጋለሁ ማለታቸው ነበር፡፡ በጣሉት የ25 ፐርሰንት ታሪፍ ምክንያት በካናዳ ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ተከስቷል፤ ካናዳውያን ወደ አሜሪካ ሲሄዱ የተንገላቱበትም አጋጣሚ ነበር፡፡ በተቃራኒው በጣም የተደሰትኩበት ቀን፣ የምወደው አምስተኛ ልጄ ተቀጥሮ መሥራት በመጀመሩ ምሳ የጋበዘኝ ዕለት ነው። ያንን የቀን ደስታ ፈጽሜ አልረሳውም፡፡
ግዮን፦ በዚህ «ዲጂታል» ዘመን ከንባብ የራቀ ትውልድ መበራከቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚያስከትለው ችግር ምንድን ነው ይላሉ?
ኤልያስ፦ በካናዳ ማኅበረሰቡ በከፍተኛ ሁኔታ ያነባል፡፡ በኢትዮጵያ ግን አብዛኛው ማኅበረሰብ የማኅበራዊ ሚዲያ ሰለባ በመሆኑ የንባብ ሂደት በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል፡፡ የመጻሕፍት ሕትመትና የስርጭት መጠናቸውም እጅግ አናሳ ነው፤ የዲጂታል ዘመኑና አጠቃላይ የሚዲያ ሥርዓቱ እኩል በመከሰቱ ሰው ንባብን ሙሉ ለሙሉ እንዲተው አድርጎታል፡፡ በካናዳ ግን የንባብ ባሕሉ ስላልሞተ፣ አንድ መጽሐፍ ከጫማ ያነሰ ዋጋ አለው፤ ቶሮንቶ ውስጥ 100 ቤተ መጻሕፍት አሉ፤ ትልልቅ መጽሔቶችም በሕትመትና በኦንላይን እኩል ተነባቢነት አላቸው፡፡
ግዮን፦ ማኅበራዊ ሚዲያ ከመደበኛው ሚዲያ ይልቅ አጀንዳ አፍላቂ መሆኑ ምን ያህል ቀውስ አስከትሏል ብለው ያስባሉ?
ኤልያስ፦ ቀደም ሲል የነበረው የጋዜጠኝነት ሥርዓት አሁን የለም፤ ዜጋ ተኮር ጋዜጠኝነት በመጣ ቁጥር ሁሉም ሰው ጋዜጠኛ ሆኗል፡፡ የሙያ ሥነ-ምግባርና እውቀት ድራሻቸው ጠፍቶ፣ ስልክ ያለው ሁሉ ኃላፊነት የጎደለው መልዕክት የማስተላለፍ መብት አግኝቷል፡፡ ቀደም ሲል እንደ ቢቢሲ፣ ሲኤንኤን፣ ቪኦኤ እና አልጀዚራ ያሉ ትልልቅ ተቋማት የሀገራቸውን ብሔራዊ ጥቅም መሠረት አድርገው አጀንዳ ይቀርጹ ነበር፡፡ አሁን ግን አጀንዳ ቀራጩ ዜጋ በመሆኑ ትልቅ አደጋ ተፈጥሯል፡፡ ቲክቶክ የአሜሪካና የቻይና የፖለቲካ መሣሪያ ሆኗል፤ የትልልቅ ሚዲያ ጋዜጠኞችም ፖድካስተር በመሆን «ላይክ» ለማግኘት ብቻ ይሠራሉ፡፡ አሁን አንድ ነገር ኮሽ ሲል ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ስለሚዛመት፣ መንግሥታት ኢንተርኔት እስከ መዝጋት ይደርሳሉ፡፡
ግዮን፦ ሀገሪቱ ከአሁኑ ምስቅልቅል አልፋ የተረጋጋ ነገን ለመገንባት «ሊተዉት» እና «ሊይዙት» የሚገባቸው እሴቶች ምንድን ናቸው?
ኤልያስ፦ እያንዳንዱ ትውልድ የራሱ እውነት አለው፡፡ በእኛ ዘመን የነበረው «መሬት ላራሹ» እና «ዳቦ ለሰፊው ሕዝብ» የሚል የትውልድ ጥያቄ ዓለም አቀፋዊ ነበር፡፡ በእንዲህ ዓይነቱ ማርክሲስታዊ ትርክት የነበረው ስሜት በደንብ ባለመገራቱና አቅጣጫ ባለመያዙ ምክንያት ላለፉት 50 ዓመታት ቀውስ አስተናግደናል፡፡ የፖለቲካ ሳይንቲስቶቻችንና ማኅበራዊ ሳይንቲስቶቻችን ባለፉት 50 ዓመታት በነበሩ ኩነቶች ላይ ጥናትና ውይይት አላደረጉም፡፡ የመኢሶን ከደርግ ጋር ማበር፣ የኢሕአፓ መነጠልና የሁለቱም ዒላማ መሆን ለደርግ አምባገነንነት መንገድ ከመክፈቱም በላይ የብሔርተኛ ድርጅቶች እንዲያብቡ ምክንያት ሆኗል፡፡ ህወሓትና ሻዕቢያ ከሶሻሊዝም ይዘውት የመጡት የዘር ፖለቲካም ኢትዮጵያን በብሔር ለመበየን በመሞከሩ ለትልቅ ቀውስ ዳርጓታል፡፡
የብሔር ፖለቲካ ሁልጊዜ ጠላት ይፈልጋል፤ አውሮፓውያን ከ80 ዓመታት በፊት የጨረሱትን የብሔር ጉዳይ እኛ ዛሬም የግጭት ምክንያት አድርገነዋል፡፡ አውሮፓ 17 ሀገራትን በአንድ ገንዘብ ባስተሳሰረችበት ወቅት፣ እኛ በዚህ ችግር ውስጥ መዘፈቃችን ያሳዝናል፡፡ አሁን ያለው አመራር የወደፊቷን ኢትዮጵያ መገንባት ላይ ትኩረት ማድረግ አለበት፡፡ ኃይለ ሥላሴ ደርግን፣ ደርግ ህወሓትን፣ ኢሕአዴግ ደግሞ ብልጽግናን ወለደ፤ ስለዚህ ከዚህ አዙሪት መውጣት ያስፈልጋል፡፡ አፍሪካዊነታችን እንጂ አማራና ኦሮሞነታችን በዓለም አቀፍ ደረጃ አይታወቅም፡፡
ግዮን፦ ከሀገራችን የወደፊት ዕጣ-ፈንታ ጋር ተያይዞ በእጅጉ የሚያሳስብዎት ምንድን ነው?
ኤልያስ፦ የተማሩና ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች በአደባባይ ወጥተው ሐሳብን መግለጽና መሞገት አለባቸው፡፡ ባለፉት 50 ዓመታት የኢትዮጵያ ምሁራን በመንግሥት ሳምባ ሲተነፍሱና አድርባይ ሲሆኑ ኖረዋል፡፡ ምሁራዊ ችሎታቸውን የመንግሥትን ዕድሜ ለማራዘም ከመጠቀም ባለፈ የራሳቸው አጀንዳ አልነበራቸውም፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም እንዳሉት፣ አሁን ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያደፈጠ ይመስላል፤ ሕዝብ መንግሥትን ሲረሳ ደግሞ ከባድ ሁኔታ ስለሚፈጠር ሊያሰጋን ይገባል፡፡
ግዮን፦ በዚህ በተዳከመ የሕትመት ሚዲያ ዘርፍ እንደ ግዮን ያለ መጽሔት ሕልውናውን አስጠብቆ እንዲቀጥል ምን መደረግ አለበት?
ኤልያስ፦ ሚዲያ እንደ ምግብና ኦክስጅን የሕይወት አካል ነው፡፡ በካናዳ መንግሥትም ሆነ ኤንጂኦዎች ሚዲያን ይደግፋሉ፤ ጋዜጠኞች ቅናሾች ይደረጉላቸዋል፡፡ በኢትዮጵያ ግን የግል ጋዜጠኞች የመንግሥት ጠላት ተደርገው ስለተፈረጁ፣ ባለሀብቱ ማስታወቂያ ለመስጠት ይፈራል፡፡ 27 ባንኮችና ኢንሹራንሶች ባሉበት ሀገር እንደ ግዮን ያሉ ሚዲያዎች መደገፍ አለባቸው፤ የገንዘብ ማሰባሰቢያ (ፈንድራይዚንግ) ዝግጅቶችንም ማዘጋጀት ይቻላል። ኒውዮርክ ታይምስ 185፣ ዋሽንግተን ፖስት 175 ዓመት ሆኗቸዋል፤ ግዮን መጽሔትም የአዲስ አበባ ሕዝብ መለያ ቀለም ስለሆነች ልትጠፋ አይገባም፡፡
ግዮን፦ አዲሱን ዓመት አስመልክተው ምን መልዕክት ማስተላለፍ ይፈልጋሉ?
ኤልያስ፦ አዲሱ ዓመት የኢትዮጵያ ሕዝብ ልዩነቱን በሰላማዊ መንገድ የሚፈታበት እንዲሆን እመኛለሁ፡፡ መንግሥት ከማኅበራዊ ሚዲያ ብሽሽቅ ወጥቶ የአባትነት ሚናውን መወጣት አለበት፡፡ እንዲሁም በሃይማኖት አባቶች ላይ የሚፈጸም ዘለፋና ውርደት መቆም ይኖርበታል፡፡ ኢትዮጵያ ፍትሕና ሥርዓት የሰፈነባት፣ ዜጎች በእምነታቸው የማይገደሉበት ሀገር እንድትሆን እመኛለሁ፡፡ ከ1600 ዓመታት በላይ የባሕልና የእውቀት ባለቤት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ምዕመኖቿና አገልጋዮቿ መጠቃትም በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል፡፡
ግዮን መጽሔት ቅጽ 8 ቁጥር 236 መስከረም 2019 ዓ.ም
