(Save the Nation) የተሰኘው አገር በቀል በመንገድ ደሀንነት ዙሪያ የሚሰራ ግብረሰናይ ተቋም ከ “ያንጎ ኢትዮጵያ “ ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ ለትራፊክ አደጋ ተጋላጭ የሆኑ አራት ት/ቤቶችን ለይቶ በአካባቢው ላይ የሰራቸውን አስፈላጊ የደህንነት ማሻሻያ ስራዎች በማጠናቀቅ በዛሬው እለት በጎሮ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት አስመርቋል።
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የሴቭ ዘ ኔሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ምስጋናው ቢምረው እንደገለፁት ፣ በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ5ሺህ በላይ ሰዎች በመንገድ ላይ የትራፊክ አደጋ ህይወታቸው ያልፋል ። ከእነዚህም ውስጥ ከ71 በመቶ በላይ እግረኞች መሆናቸውን አስታውቀዋል።
በአዲስ አበባ ብቻ በየዓመቱ ከ400 በላይ ሰዎች ለህልፈት የሚዳረጉ ሲሆን ተማሪዎች ለዚህ አስከፊ ለትራፊክ አደጋ ተጋላጭ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ይህንን ተከትሎም በአዲስ አበባ ከተማ የመንገድ ደህንነትን ለማረጋገጥ ከተለያዩ መንግስታዊ እና ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰሩ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በተለይም ከ2018 ዓ.ም ጀምሮ ተግባርና ኃላፊነቱ ወደ ሌሎች ተቋማት ከተላለፈው የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ጋር በመተባበር ለትራፊክ አደጋ ከፍተኛ ተጋላጭ ተብለው በተለዩ አራት ት/ቤቶች እና አካባቢ የተለያዩ የምህንድስና ማሻሻያዎችን እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች መከናከናቸውን ተናግረዋል።
በዚህም መሰረት የት/ቤቶችን አጥር የማስተካከልና የእግረኛ መንገዶችን ቀለም መቀባትን ጨምሮ የተለያዩ የመንገድ ደህንነት ስራዎችን በማከናወን ተማሪዎችን ከአደጋ ለመጠበቅ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
በከተማዋ ት/ቤቶች አካባቢ የትራፊክ ፍሰትን ለማሳለጥ በርካታ ስራዎችን እንደሚሰራ የገለፁት ደግሞ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የመንገድ ደህንነትና ትምህርት አቅም ግንባታ ዳይሬክተር አቶ ብርሀኑ ኩማ ናቸው።
የትራፊክ አደጋ ማንኛውም ሰው የማይመርጥ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ በአደጋው ከሞቱት ሰዎች ባሻገርም በርካታ ቤተሰቦችን ለጉዳት እንደሚዳርግ አስገንዝበዋል።
በመሆኑም ያንጎ ኢትዮጵያ እና ሴቭ ዘ ኔሽን የነገ ሀገር ተረካቢ ልጆችን ከትራፊክ አደጋ ለመጠበቅ ለሰሩት ስራ ምስጋና አቅርበው ችግር በአንድ ተቋም ብቻ የማይፈታ በመሆኑ ሁሉም በትብብር እንዲሰራ ጥሪ አስተላልፈዋል።
የ ያንጎ ኢትዮጵያ ዋና ስራአስኪያጅ ዶ/ር ይቅናአለም አበበ በበኩላቸው ፣ ተማሪዎችን ከአደጋ ለመጠበቅ የተለያዩ የግንዛቤ ፈጠራ ስልጠና እየተሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በ25 ቀናት ውስጥ ብቻም ለ12 ሺህ 500 ተማሪዎች ስለመንገድ ደህንነት ስልጠና መሰጠቱን አስታውቀዋል። እንዲህ አይነቱ ተግባር በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
