ዳንጎቴ በናይጄሪያ የተገጣጠመ የኤሌክትሪክ ከባድ የጭነት መኪና ይፋ አደረገ

Date:

ተሽከርካሪዎቹ በአንድ ቻርጅ እስከ 200 እና 350 ኪሎ ሜትር መጓዝ እንደሚችሉ ተገልጿል

የአፍሪካው ቢሊየነር አልኮ ዳንጎቴ በናይጄሪያ በሀገር ውስጥ የተገጣጠመ ከባድ የኤሌክትሪክ የጭነት መኪና ይፋ አድርገዋል። ይህም በአፍሪካ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ማምረትና መገጣጠም ዘርፍ አዲስ እርምጃ መሆኑ ተጠቁሟል።

ተሽከርካሪው በዳንጎቴ ግሩፕና በቻይናው ሲኖትራክ (SINOTRUK) በጋራ በተቋቋመው የዳንጎቴ ሲኖትራክ ጥምር ኩባንያ በሌጎስ በሚገኘው ፋብሪካ የተገጣጠመ ነው።

በተሽከርካሪው ይፋዊ ሥነ-ሥርዓት ላይ የዳንጎቴ ግሩፕ፣ የሲኖትራክና የሌጎስ ግዛት ባለሥልጣናት ተገኝተዋል። የሲኖትራክ ፕሬዝዳንት ሊዩ ዌይ እንደገለጹት፣ ተሽከርካሪው በአፍሪካ በሀገር ውስጥ የተገጣጠመ የመጀመሪያው ዘመናዊ ከባድ የኤሌክትሪክ የጭነት መኪና ነው።

ከቀረቡት ምርቶች መካከል በአንድ ቻርጅ እስከ 200 ኪሎ ሜትር መጓዝ የሚችል የጭነት መኪና ይገኝበታል። የቻርጅ ጊዜን ለማሳጠርም ፈጣን ቻርጅ መሣሪያ አብሮ ቀርቧል። በተጨማሪም በአንድ ቻርጅ እስከ 350 ኪሎ ሜትር መጓዝ የሚችል ሌላ ትልቅ የኤሌክትሪክ ተሳቢ የጭነት መኪና መዘጋጀቱ ተገልጿል።

ኩባንያው ከ2017 ዓ.ም. ጀምሮ ከ8 ሺህ በላይ በናፍጣና በጋዝ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን ሲገጣጥም መቆየቱን የዘገባው መረጃ ያመለክታል። ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ቴክኖሎጂ መሸጋገሩም የኩባንያውን የምርት አቅጣጫ እያስፋፋ መሆኑን ያሳያል።

የዳንጎቴ ግሩፕ ከፍተኛ ኃላፊ ዴቫኩማር ኤድዊን እንደገለጹት፣ የኤሌክትሪክ የጭነት መኪናዎች አጠቃቀም የአየር ብክለትን ከመቀነስ ባለፈ የነዳጅና የተሽከርካሪ ሥራ ማስኬጃ ወጪን ለመቀነስ የሚያግዝ አማራጭ ነው።

የሌጎስ ግዛት ባለሥልጣናትም ተሽከርካሪዎችን ከውጭ በማስገባት ላይ ብቻ ከመመሥረት ይልቅ በሀገር ውስጥ የማምረትና የመገጣጠም አቅምን ማሳደግ ለኢኮኖሚ እድገትና ለሥራ ዕድል ፈጠራ ያለውን አስተዋጽኦ አድንቀዋል።

ይህ እርምጃ አፍሪካ ከውጭ ምርት አስመጪነት ባሻገር በራሷ የማምረትና የመገጣጠም አቅም እንድትገነባ የሚያግዝ እድል እንደሚፈጥር ተገልጿል።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሞዛምቢክ አቻው ጋር ዛሬ ያደረገውን ወሳኝ ጨዋታ 1ለ0 ተሸነፈ !

በ2027 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ አራተኛ ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ...

በአዲስ አበባ ለሶስት ቀናት የሚቆይ የንባብ ፌስቲቫል ሊካሄድ ነው

የንባብ ባህልን ለማነቃቃት ያለመ 15ኛው ከተማ አቀፍ የንባብ ፌስቲቫል...

የጣሊያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ የኤንሪኮ ማቴይ ሽልማት ተሸለሙ

የጣሊያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ በአፍሪካና በአውሮፓ መካከል ያለውን...