የንባብ ባህልን ለማነቃቃት ያለመ 15ኛው ከተማ አቀፍ የንባብ ፌስቲቫል ከነገ ህዳር 9 እስከ 11 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ ለሶስት ተከታታይ ቀናት ሊካሄድ መሆኑን የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል።
ቢሮው በዛሬው ዕለት በሰጠው መግለጫ የፌስቲቫሉ የዝግጅት ምዕራፍ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን ገልጿል።
የቢሮው የባህል ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አዲሱ ሻንቆ (ዶ/ር)እንዳሉት ለሶስት ቀናት የሚቆየው ፌስቲቫል ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ እንዲሆን በከተማዋ በሚገኙ አምስት ዋና ዋና ስፍራዎች ይካሄዳል።
እነዚህም መገናኛ ፣ ሜክሲኮ ፣ 4 ኪሎ ፕላዛ ፣ ሳሪስ አቦ እና ፒያሳ ሲሆኑ ከ60 ሺህ እስከ 100 ሺህ የሚደርሱ የከተማዋ ነዋሪዎች፣ ተማሪዎችና ወላጆች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።
በሶስቱ ቀናት የፌስቲቫሉ ቆይታ የንባብና አንብቦ የመረዳት ውድድሮች ፣ የንባብ ባህልን ለማሳደግ የሚያግዙ ጥናታዊ ጽሑፎችና ውይይቶች እንዲሁም የግጥምና የመነባንብ ስነ ጽሑፋዊ ዝግጅቶች እንደሚቀርቡ ተብራርቷል።
«የንባብ ባህልን በማነቃቃት ፣ እውቀትንና የፈጠራ አቅምን በማሳደግ ለሀገር ግንባታ የሚያግዝ በምክንያታዊ አስተሳሰብ የበለጸገ ትውልድ መፍጠር» በሚል መሪ ቃል እንደሚካሄድ ተጠቅሷል።
ወላጆች ፣ ተማሪዎችና መላው የከተማዋ ነዋሪዎች በተጠቀሱት አምስት ስፍራዎች በመገኘት በፌስቲቫሉ እንዲሳተፉና የንባብ ባህልን በማሳደግ የድርሻቸውን እንዲወጡ ቢሮው ጥሪ አቅርቧል።
