ሁዳ ኢንጂነሪንግ በ2009 ዓ.ም. የተመሠረተ ሲሆን፣ በ2015 ዓ.ም. ወደ ሪል እስቴት ዘርፍ ገብቷል።
ድርጅቱ በዘርፉ ያሉ የግንባታና የርክክብ መዘግየት ችግሮችን ለመቅረፍ በዱባይና ቻይና ልምድ ተቀስሞ በቴክኖሎጂ ላይ የተመሠረተ የግንባታ አሠራር መከተሉን አስታውቋል።
በዚህ አሠራር የሕንጻዎችን መዋቅራዊ ሥራ በስድስት ወራት፣ ቀሪ የግንባታ ሥራዎችን በተጨማሪ አንድ ዓመት በማጠናቀቅ በአጠቃላይ ሁለት ዓመት የሚፈጅ ፕሮጀክትን በ18 ወራት ማስረከብ እንደሚቻል በጥናት መድረሱን ገልጿል።
ድርጅቱ እስካሁን አምስት የሪል እስቴት ፕሮጀክቶች ያሉት ሲሆን፣ በቡልቡላ የሚገኙ ሁለት ፕሮጀክቶችን አጠናቆ ለነዋሪዎች አስረክቧል። በቦሌ የሚገኘውን የአደይ ፕሮጀክት በ18 ወራት ማጠናቀቁን እንዲሁም የኒያላ ሞተርስ ፕሮጀክትን መዋቅራዊ ሥራ በዘጠኝ ወራት አጠናቆ ቀሪ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን አስታውቋል።
ሁዳ ኢንጂነሪንግ በቦታ ምርጫ፣ በግንባታ ጥራትና በወቅቱ ርክክብ ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ገልጾ፣ የግንባታ ግብዓቶችን በተለይም ብረትን በጊዜ ለማግኘት ከፕሮጀክቶች መጀመሪያ በፊት ከውጭ አስመጥቶ በማዘጋጀት እንደሚሠራ አመልክቷል። በተጨማሪም አንድን ፕሮጀክት በተያዘለት ጊዜ አጠናቆ ወደ ቀጣዩ የመሸጋገር አሠራር እንደሚከተል አስታውቋል።
