አካል ጉዳተኝነት የአቅም ገደብ እንዳልሆነ በተግባር በማሳየት በተለያዩ ዘርፎች ስኬት ያስመዘገቡ ዜጎችን ለማበረታታት የተዘጋጀው የመጀመሪያው ዙር “አካታች አዋርድ” የሽልማት መርሐ ግብር ዛሬ በቫምዳስ ሲኒማ ይካሄዳል።
በቱራይዝ መልቲሚዲያ አዘጋጅነት ከቀኑ 8:00 ሰዓት የሚጀምረው መርሐ ግብር፣ በተለያዩ ዘርፎች የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱና አርአያ ለሆኑ አካል ጉዳተኞች እውቅናና ሽልማት የሚሰጥበት መድረክ ነው።
ሽልማቱ በሥራ ፈጠራ፣ በንግድና ኢኮኖሚ፣ በትምህርት፣ በሳይንስና ምርምር፣ በቴክኖሎጂ፣ በኪነ-ጥበብ፣ በስፖርት፣ በበጎ አድራጎት፣ በግብርናና በአካባቢ ጥበቃ ዘርፎች ስኬት ያስመዘገቡ ግለሰቦችን ያካትታል።
በየዓመቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የታለመው ውጥኑ፣ ከሽልማት መርሐ ግብሩ ባለፈ ዘላቂ የማኅበረሰብ ለውጥ ለማምጣት የሚያግዙ ተግባራትንም ይዟል።
በየሁለት ወሩ በሚዘጋጁ የውይይት መድረኮች፣ አካል ጉዳተኞች የመንገድ፣ የትራንስፖርትና የሕንፃ ተደራሽነት ችግሮችን በማንሳት ለሚመለከታቸው የመንግሥትና የግል ተቋማት የመፍትሔ ሃሳቦች የሚያቀርቡበት ዕድል እንደሚፈጠር አዘጋጆቹ ገልጸዋል።
በዝግጅቱ ላይ የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተወካዮች፣ የሚዲያ ባለሙያዎች፣ የጥበብ ሰዎችና በጎ አድራጊዎች በመገኘት አጋርነታቸውን እንዲያሳዩ ጥሪ ቀርቧል።
