12 ሀገራት የሚሳተፉበት የአፍሪካ መስማት የተሳናቸው እግር ኳስ ሻምፒዮና ሰኞ በአዲስ አበባ ይጀምራል
12 ሀገራት የሚሳተፉበት የአፍሪካ መስማት የተሳናቸው እግር ኳስ ሻምፒዮና በመጪው ሰኞ ህዳር 21 በአዲስ አበባ እንደሚጀምር የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር አስታውቋል።
ውድድሩ በኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው እግር ኳስ ማህበር ከአፍሪካ መስማት የተሳናቸው ማህበር ጋር በትብብር የሚዘጋጅ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ የሻምፒዮናውን የመጀመሪያ ዙር አስተናጋጅ ሀገር ሆናለች።
የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ መኪዩ መሐመድ፣ ኢትዮጵያ ውድድሩን ማስተናገዷ በቀጣይ ሌሎች ሀገራትም ውድድሩን እንዲያስተናግዱ መነሳሳት እንደሚፈጥር ገልጸዋል። በስፖርቱ በሁሉም ዘርፍ መሳተፍ ከተቻለ ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻልም ጠቁመዋል።
አቶ መኪዩ አዲስ አበባ በዚህ ዓመትም እንደ ባለፈው ዓመት በአትሌቲክስ፣ በተለያዩ ኮንፈረንሶችና በሌሎች የስፖርት ውድድሮች አስተናጋጅነቷን እንደምትቀጥል ገልጸው፣ ስፖርቱ አካታች እንዲሆን አስፈላጊነቱን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ፣ ፌዴሬሽኑ ውድድሩን በማዘጋጀትና በመሳተፍ ሁለት ዋና ዓላማዎች ላይ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል። በውድድሩ 20 ኢትዮጵያውያን ዳኞች ጨዋታዎችን እንደሚመሩም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያን የሚወክሉ ተጫዋቾች በሆቴል ተሰባስበው የውድድሩን ዝግጅት እና ልምምድ እያደረጉ ሲሆን፣ የዝግጅታቸውን ወጪ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እየሸፈነ መሆኑን አቶ ኢሳያስ ገልጸዋል።
ውድድሩ በአዲስ አበባ ስታዲየምና በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የሚካሄድ ሲሆን፣ 12 ሀገራት በሚሳተፉበት የአህጉሪቱ ውድድር ኢትዮጵያ የራሷን የስፖርት አቅም ለማሳየትና የአካታች ስፖርት እንቅስቃሴን ለማጠናከር እድል አግኝታለች።
