ቡድኑ በቻይና፣ በህንድ፣ በብራዚል በሩስያ፣በደቡብ አፍሪካና በብሪክስ አባል ሀገራት ጉዞ የሚያደርግ ይሆናል።
በ1978 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኪነት ቡድን፤ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለኢትዮጵያ ላደረገው ሰብዓዊ ድጋፍ፤ ምስጋና ለማቅረብ “አደይ አበባ” (ህዝብ ለህዝብ) በሚል መሪ ሀሳብ ወደ ተለያዩ የዓለም ሀገራት በመጓዝ የጥበብ ስራዎችን አቅርበው ነበር።
ከ39 ዓመታት በኃላ ደግሞ “ኪን ኢትዮጵያ- የኢትዮጵያ ማንሰራራት ብስራት” በሚል መሪ ሀሳብ በዓይነቱና በይዘቱ ለየት ያለና፤ የኢትዮጵያን ቱባ ባህልና ጥበብን ለዓለም ህዝብ ለማስተዋወቅ፤ የባህልና የጥበብ ዲፕሎማሲ በመስራት የሀገራችንን መልካም ገፅታ የመገንባት ዓላማ ያነገበ ኩነት ተጀምሯል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከሻኩራ ፕሮዳክሽን ጋር በመተባበርና
በዝነኛው የሙዚቃ ባለሙያ ካሙዙ ካሳ የቡድን መሪነት ወደ ብሪክስ አገራት በሚደረገው የጥበብ ጉዞ ኪነ-ጥበብን፣ ሥነ- ጥበብን እንደ ትልቅ መሣሪያ በመጠቀም ለሀገር ገጽታ ግንባታ የማይተካ ሚና ይኖረዋል ተብሏል።
በዓድዋ ሙዚየም በተካሄደው የሽኝት መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ሸዊት ሻንካም ተከታዩን መልዕክት አስተላልፈዋል ይህንን ታላቅ ሀገራዊ ተልዕኮ ይዛችሁ የምትጓዙ የልኡካን ቡድን አባላት መርሐ-ግብሩ የታለመለትን ዓላማ በማሳካት ግቡን እንዲመታ የበኩላችንሁን ታላቅ ሙያዊና ሀገራዊ ኃላፊነት እንድትወጡ አደራ እላችሁሀለሁ ብለዋል።
እንዲሁም ባገኛችሁት አጋጣሚ ሁሉ ያላችሁን አቅም አሟጣችሁ በመጠቀም የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ከፍ የማድረግ ታሪካዊ አደራ የተሸከማችሁ እያስገነዘብኩ ይሔንኑ ታላቅ ኃላፊነት በታማኝነት በቁርጠኝነትና በፍጹም ትጋት እንዲትወጡት ከአደራ ጭምር መልዕክት ሳስተላልፍ በታላቅ መተማመንና በጠነከረ መንፈስ ነው ብለዋል።
አሁን ሀገራችን ኢትዮጲያ በፈጠራ ጥበብ በኩል አኩሪ ባህሏን ታሪኳንና የተፈጥሮ ዘጋዋን ለዓለም በተገቢው መንገድ በመግለፅ የዓለምን ትኩረት መሳብና ከውጤቱ ተጠቃሚ ለመሆን የምትችልበት ታላቅ ተግባር ተጀምሯል።
ሻኩራ ፕሮዳክሽን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ስራ በመስራት “ኪን ኢትዮጵያ፡ የኢትዮጵያ ማንሰራራት ብስራት” የጥበብ ጉዞን አስጀምረዋል።
ኢትዮጵያ አገራችን በቅርቡ በአባልነት በታቀፈችበት የብሪክስ አባል አገራት የሚደረገው ይህ ጉዞ ለውስጥ ሀገራዊ አንድነት፣ ለጠነከረ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርና አብሮነት፣ ለገጽታ ግንባታ፣ ለውስጣዊ ሰላምና ለሁለንተናዊ ብልጽግና ያለንን ባህላዊ ሀብት በተግቢው መልኩ መጠቀም ከማስቻሉም ባሻገር ሀገራችን የላትን አኩሪ ባህሏን፣ ታሪኳንና የተፈጥሮ ፀጋዋን ለዓለም በማስተዋወቅም ከፍተኛ ጥቅምን ያስገኝላታል።
የኢትዮጵያን ቱባ ባህልና ኪናዊ ፀጋ ለዓለም ህዝብ ለማስተዋወቅ ከ39 አመታት በኋላ የሚደረገው የዓለም አቀፍ ጉዞ (ኪን ኢትዮጵያ) ከዚህ ቀደም ከቀረቡ የባህል ሙዚቃዎች ሁሉ ለየት ባለመልኩ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦችን ያማከለ እና ትርዒቱ በሰርከስናና ባህላዊ ፍሽን ትርዒት ከዉብ የመድረክ ገፅታ ጋር የተላበሰ ነበር።
የኢትዮጵያ ማንሰራራት ብስራት በቀጣይነትም ኢትዮጵያን ጨምሮ ብራዚልን፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ቻይና፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ግብጽና ኢንዶኔዥያን በአባልነት ባቀፈው የብሪክስ አባል አገራት እና በሌሎች የአለማችን ሐገራት በተከታታይነት ይካሄዳል።
