በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ የሚገኙ ባለቤት አልባ ውሾች ቁጥር ከእለት ወደ ዕለት እየጨመረ መምጣቱን ግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል።
የሚኒስቴሩ የውሻ መከላከል እና መቆጣጠር አስተባባሪ ዶ/ር ወንዱ መንገሻ በከተማዋ የሚገኙ ባለቤት የሌላቸው ውሾች ቁጥር ከፍተኛ እየሆነ መምጣቱን ገልጸው ይህም የሆነው በወንዝ ዳር በኮሪደር እና በሌሎችም ምክንያቶች የመኖሪያ አካባቢያቸውን የሚለቁ ሰዎች ያሳድጓቸው የነበሩትን ውሾች ጥለው በመሄዳቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በከፍተኛ መጠን እየጨመረ የመጣውን የውሾች ቁጥር ለመቀነስ የመዋለድ መጠናቸውን ለመቆጣጠር የተለያዩ በሽታዎችን ወደ ሰዎች እንዳያስተላልፉ ለመከላከል እየተሰራ እንደሚገኝ በማንሳትም የተጠቀሱትን የመከላከል እና የመቆጣጠር ሥራዎች ለማከናወን የባለሙያ እጥረት ስለመኖሩ ተናግረዋል፡፡
በመስኩ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን ቁጥር ለመጨመር ግብርና ሚኒስቴር ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር እየሰራ እንደሚገኝም ዶ/ር ወንዱ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በዚህም መሠረት ስልጠናው የውሾችን የዘር ፍሬን ማስወጣት፣ ማኅጸናቸውን ማውጣት እና መሰል ሕክምናዎችን እንደሚያጠቃልል የገለጹ ሲሆን፤ ለዚህም በጅማ በሀዋሳ እና በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ሥር ከሚገኘው ደብረዘይት ኮሌጅ ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የባለቤት አልባ ውሾች ቁጥር እንዳይበራከት የእብድ ውሻ በሽታን ለመከላከል እንዲሁም የጎዳና ላይ ገጽታንና ደህንነትን ለመጠበቅ በሚል፤ በጎዳና ላይ የሚገኙ ውሾችን ወደ መጠለያ በማስገባት በዘመናዊ መንገድ በማምከን እንዳይራቡ ለማድረግ የሚያስችል ደንብ አዘጋጅቶ ወደ ሥራ ለማስገባት በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ማስታወቁ ይታወሳል።
ደንቡ በረቂቅ ደረጃ ያለና በቅርቡ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን በአሠራር ደንቡ መሠረት ባለቤት አልባ የጎዳና ላይ ውሾችን ወደ መጠለያ ለማስገባት መጀመሪያ የውሻ ባለቤትነት ምዝገባ እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡
በዚህም መሠረት ‘ውሻ አለኝ’ የሚል ማንኛውም ሰው ምዝገባ በማድረግ “የውሻ ባለቤትነት ማረጋገጫ የምስክር ሰነድ ይሰጠዋል” ተብሏል፡፡
(አሐዱ ሬድዮ)
