የአውሮፓ ሕብረት ከዓመት በፊት ለኢትዮ-ጅቡቲ የንግድ ኮሪደር ሥራ የሚውልና በትሬድ ማርክ አፍሪካ በኩል ድጋፍ ባደረገው 32 ሚሊየን ዶላር በጀት የተለያዩ ፕሮጀክቶች እየተሰሩ እንደሚገኝ ትሬድ ማርክ አፍሪካ አስታውቋል።
“ትሬድ ማርክ አፍሪካ” በአፍሪካ ውስጥ ትልቅ ተቋምና ዋና መቀመጫውን ናይሮቢ አድርጎ በዋናነት ንግድና ሎጀስቲክስ ላይ አተኩሮ የሚሰራ መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም ስለመሆኑ፤ በኢትዮጵያ የትሬድ ማርክ ዋና ዳይሬክተር አቶ እውነቱ ታየ ለአሐዱ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ እና ጅቡቲ መካከል ያለውን የጋራ የንግድ ኮሪደር ለማሳለጥ የሚያስችል አስተዳደር እንዲቋቋም ለማድረግ፤ በጋራ እየተሰራበት እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
ለዚሁ ሥራ የሚውልም በጠቅላላ በአውሮፓ ሕብረት በኩል ከተሰጠው 32 ሚሊዮን ዶላር በተጨማሪ፤ከፈረንሳይ ልማት ኤጀንሲ (AFD) 1 ሚሊዮን 600 ሺሕ ፓውንድ እንዲሁም ከአይሪሽ ኤድ (irish aid) በኩል ወደ 400 ሺሕ ዶላር ድጋፍ ስለመደረጉ አንስተዋል።
ከዚህ ሌላም ከሌሎች በርካታ ድጋፍ ሰጪ ተቋማትና ተቋሙ ራሱ ከማዕከል በሚያገኘው ገቢ በርካታ ከዚሁ ጋር የተያያዙ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ገልፀው ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም የኮሪደር አስተዳደርን ጨምሮ ለዲጂታል ስርዓት እና በሀገራት መካከል በተለይም የአፍሪካ ቀንድን ለማስተሳሰር የሚያስችሉ እንቅፋቶችን ለማንሳትና የንግድ ግንኙነቱን የበለጠ የተሳለጠ እንዲሆን ለማድረግ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
ድጋፍ ከተደረገው ገንዘብ ላይም በኢትዮጵያ በኩል የንግድና ሎጀስቲክስ ዘርፉ ላይ በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ከእነዚህም ውስጥ ተመርቀው አገልግሎት እየሰጡ ያሉና ገና በሂደት ላይ የሚገኙ እንዲሁም፤ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ይመረቃሉ ተብለው የሚጠበቁ በርካታ ፕሮጀክቶች ስለመኖራቸው ተናግረዋል።
ይህ ሥራም የኢትዮጵያን ገቢና ወጪ ንግድ የበለጠ ተወዳዳሪ እንዲሆን ለማድረግ እንደሚያግዝ ጠቅሰው፤ ከማሰሩት ሥራዎች ውስጥም የተለያዩ ስልጠናዎች መስጠት እና የቴክኖሎጂ ማበልፀጊያ ሥራዎች መኖራቸውን አስታውቀዋል።
የኢትዮ-ጅቡቲ የንግድ ኮሪደር ከ15 ሺሕ በላይ የጭነት ተሽከርካሪዎችን የሚያስተናግድ ሲሆን፤ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር እና የጂቡቲ የመሰረተ ልማት እና ኢክዩፕመንት ሚኒስቴር የኮሪደር አስተዳደር ባለስልጣን ለመመስረት የሚያስችል ስምምነት ባሳለፍነው የሚያዝያ ወር ላይ አድርገዋል፡፡
ትሬድ ማርክ አፍሪካ የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ለቀጣዮቹ ስምንት ዓመታት ተቋሙን በቦርድ ሊቀመንበርነት እንዲመሩ በመስከረም ወር መጀመሪያ ላይ መሾሙ ይታወሳል፡፡
(አሐዱ ሬድዮ)
