6ኛው የፔፕሲ አዲስ አበባ የክለቦች አቋም መለኪያ ውድድር በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄዱ የመጨረሻ ውድድሮች ፍጻሜ አግኝቷል።
በአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተዘጋጀው ውድድር የአጭር፣ መካከለኛ፣ የመሰናክል ሩጫዎችንና የሜዳ ተግባራትን ያካተተ ሲሆን፣ በመጨረሻው ቀን 1500 ሜትር፣ 200 ሜትር፣ 110 ሜትር መሰናክል፣ የጦር ውርወራ፣ የከፍታ ዝላይ እንዲሁም 4×100 እና 4×400 ሜትር የዱላ ቅብብል ውድድሮች ተካሂደዋል።
በውድድሩ 470 አትሌቶች የተሳተፉ ሲሆን፣ መቻል አትሌቲክስ ክለብ በሴቶች፣ በወንዶችና በአጠቃላይ ውጤት አሸናፊ በመሆን ሶስት ዋንጫዎችን ወስዷል።
ውድድሩ አትሌቶች ብቃታቸውን የሚመዝኑበት፣ ክለቦች አዳዲስ አትሌቶችን የሚመለከቱበትና በቀጣይ ወር ለሚካሄደው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የክለቦች አቋም መለኪያ ውድድር የሚዘጋጁበት መድረክ መሆኑ ተገልጿል።
