ቅድስት ሥላሴ በአብርሃም ቤት

Date:


እንኳን ለቅድስት ሥላሴ ዓመታዊ ክብረ በዓል (ሐምሌ ፯)
በሰላም አደረሰን፤ አደረሳችሁ !!!

መ/ር ጌታቸው በቀለ

አጋእዝተ ዓለም ሥላሴ አብርሃም ቤት ገብተው አብርሃምን የባረኩበት፣ በቤቱም የተስተናገዱበት፣ ሣራ ይስሐቅን እንደምትወልድ ያበሠሩበት ዕለት ነው፤ ሐምሌ ፯ ቀን፡፡

ይህ የቅድስት ሥላሴ ክብረ በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በየዓመቱ በደማቅ ሥነ ሥርዓት ይከበራል፡፡ታሪኩን ቅዱሳት መጻሕፍትን መሠረት አድርገን እንደሚከተለው እንመለከታለን፡፡

ቅድስት ሥላሴ

ሥላሴ ማለት የግእዝ ቃል ሲሆን ሦስት፤ ሦስትነት ማለት ነው፡፡ “ሥላሴ” የሚለው ቃል ሠለሰ፤ ሦስት አደረገ› ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲኾን ትርጉሙ ሦስትነት ማለት ነው፡፡ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ (፲፱፻፵፰)፡፡ መጽሐፍ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፡፡ ገጽ ፮፻፷፱/፡፡

በምሥጢረ ሥላሴ ትምህርት እንደምንረዳው ሥላሴ አንድም ሦስትም ናቸው፡፡ ሥላሴ ስንልም አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ ማለታችን ነው፡፡ እግዚአብሔር በስም፣ በግብር፣ በአካል ሦስት ናቸው፡፡ የስም ሦስትነት፡- አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ማለት ነው፡፡

የግብር ሦስትነት፡- አብ አባት፣ ወልድ ልጅ መንፈስ ቅዱስ ሰራፂ፡፡ የአካል ሦስትነት፡- አብ የራሱ የሆነ ፍጹም ገጽ መልክ አለው፤ ወልድ የራሱ የሆነ ፍጹም ገጽ መልክ አለው፤ መንፈስ ቅዱስ የራሱ የሆነ ፍጹም ገጽ መልክ አለው፡፡

የእግዚአብሔር አንድነት በአገዛዝ፣ በሥልጣን፣ ይህን ዓለም በመፍጠርና በማሳለፍ፣ በህልውና፣በመለኮት በፈቃድ በመሳሰሉት ሁሉ አንድ ነው፡፡ / መ/ር ብርሃኑ ጎበና (፲፱፻፹፭)፡፡ ዓምደ ሃይማኖት፡፡ ገጽ 40/፡፡ 

ሥላሴ “ቅድስት” ተብለው በሴት አንቀጽ መጠራታቸው ሴት(እናት) ፈጭታ ጋግራ ቤተሰቦቿን እንደምትመግበው ሥላሴም በዝናም አብቅለው በፀሐይ አብስለው ፍጥረቱን ሁሉ ስለሚመግቡ “ቅድስት ሥላሴ” እያልን እንጠራቸዋለን፡፡

ቅድስት ሥላሴ በአብርሃም ቤት

አብርሃም ከደግነቱና እንግዳ ከመውደዱ የተነሣ በተመሳቀለ ጎዳና ላይ ድንኳን ሠርቶ የወጣ የወረደውን፣ የመጣ የሔደውን ሁሉ እየተቀበለ እግዚአብሔርን እያገለገለ የሚኖር ጻድቅ ነበር፡፡ ሰይጣን ለተንኮል አያርፍምና ይህንን መልካም ግብሩን ለማሰናክል አሰበ፡፡

አስቦም አልቀረ፤ የተጐዳ ሰው መስሎ ከጐዳና ቆሞ አብርሃም እንግዳ መቀበል እንደ ተወ፤ እርሱ ሊበላ ሊጠጣ ከቤቱ ቢሔድ ራሱን ፈንክቶ፣ ደሙን አፍሶ፣ አጥንቱን ከስክሶ፣ ልብሱን ገፎ እንደ መለሰው ወደ አብርሃም ቤት ለሚሔዱ ሰዎች ይናገር ጀመር፡፡ በዚህ የተነሣም እንግዳ ወደ አብርሃም ቤት አይመጣም ነበር፡፡

አብርሃምም ማዕደ እግዚአብሔርን ያለ እንግዳ አልመገብም ብሎ ሦስት ቀን ሳይመገብ ጾሙን አደረ፡፡ በሦስተኛው ቀን ይህን ደግነቱን እግዚአብሔር ተመልክቶ በኦሪት ዘፍጥረት ፲፰፥፩-፲፱ ተጽፎ እንደምናገኘው በቀትር ጊዜ አብርሃም በድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ እግዚአብሔር በሦስት ሰዎች አምሳል አንድም በሥላሴ (በሦስትነት) በመምሬ አድባር ዛፍ ተገልጦለታል፡፡

አብርሃምም ሦስት ሰዎች ቆመው ባየ ጊዜ ሊቀበላቸው ከድንኳኑ ደጃፍ ተነሥቶ ወደ እነርሱ ሮጠ፡፡ ወደ ምድርም ሰገደና “አቤቱ በፊትህስ ሞገስ አግኝቼ እንደ ኾነ ባርያህን አትለፈኝ?” ብሎ ተማጸነ፡፡ በመቀጠል አብርሃም “ጥቂት ውኃ ይምጣላችሁ፤ እግራችሁን ታጠቡ፤ ከዚህችም ዛፍ በታች ዕረፉ፡፡ ቍራሽ እንጀራም ላምጣላችሁ፤ ልባችሁንም ደግፉ፡፡

ከዚያም በኋላ ትሔዳላችሁ፡፡ ስለዚህ ወደ ባርያችሁ መጥታችኋልና” ሲላቸው እነርሱም “እንዳልህ አድርግ” ብለውታል (ቅዳሴ ማርያም አንድምታ ትርጓሜ፣ ፬፥፴፪)፡፡ የኦሪት ዘፍጥረት አንድምታ ትርጓሜ እንደሚያስረዳው አብርሃም ሥላሴን “ጌቶቼ ከቤት ገብታችሁ ዕረፉ” ሲላቸው “ደክሞናልና አዝለህ አስገባን” አሉት፡፡ እርሱም እሺ ብሎ አንዱን አዝሎ ቢገባ ሁለቱ በግብር አምላካዊ (በአምላካዊ ጥበብ) ከቤቱ ገቡ፡፡

አብርሃምም ወደ ሣራ ዘንድ ፈጥኖ ሔደና “ሦስት መሥፈሪያ ዱቄት ፈጥነሽ አዘጋጂ፤ ለውሺውም፤ እንጎቻም አድርጊ” አላት፤ እርሷም እንዳዘዛት አደረገች፡፡ አብርሃምም ወይፈን አርዶ አወራርዶ አዘገጅቶላቸው ተመግበዋል፡፡

ከዚያም የታረደውና የተወራረደውም ወይፈንም ተነሥቶ በድንኳኑ ደጃፍ “ስብሐት ለአብ ስብሐት ለወልድ ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ፤ ለአብ ምስጋና ይገባል፤ ለወልድ ምስጋና ይገባል፤ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይገባል” ብሎ እግዚአብሔርን አመስገኗል፡፡

ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር አብርሃምን ጠርቶ ‹‹ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት?›› አለው፡፡ አብርሃምም ከድንኳኑ ውስጥ እንዳለች ነገረው፡፡ እግዚአብሔርም ‹‹የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ በእውነት እመለሳለሁ፤ ሚስትህ ሣራም ልጅን ታገኛለች›› ብሎ ለአብርሃም አበሠረው፡፡

ሣራ ይህንን ቃል በሰማች ጊዜ ባለቤቷም አርጅቶ፤ እርሷም የሴቶች ግዳጅ ትቷት ነበርና መውለዷን በመጠራጠሯ ሳቀች፡፡ እግዚአብሔርም ምሥጢሩን በአጽንዖት ለማስረዳትና አስረግጦ ለመንገር አብርሃምን ‹‹ሣራ ለምን ትስቃለች? በውኑ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን?›› አለው፡፡

ሣራም ስለፈራች ‹‹አልሳቅሁም›› አለች፡፡ እግዚአብሔርም መሳቋን እንዳወቀባት ከነገራት በኋላ በድጋሜ በዓመቱ ወደ አብርሃም ቤት እንደሚመጣና ሣራ ወንድ ልጅ (ይስሐቅን) እንደምትወልድ አብሥሯቸዋል፡፡ ከዚህ ትምህርት ብዙ ነገሮች እንማራለን፡፡ ለአብነትም ያህል የተወሰኑትን እንመልከት፡-

አንድነትና ሦስትነት

“በፊትህስ ሞገስ አግኝቼ እንደ ኾነ ባሪያህን አትለፈኝ?” የሚለው ኃይለ ቃል አንድነቱን፤ ጥቂት ውኃ ይምጣላችሁ እግራችሁን ታጠቡ ብሎ ሦስትነታቸውን ምሥጢር ይገልጻል፡፡ ሣራ ዳቦ ያዘጋጀችበት ሦስቱ መሥፈሪያ የሦስትነቱ፤ ዳቦው አንድ መኾኑ ደግሞ የአንድነቱ ምሳሌ ነው፡፡

ሥላሴ አብርሃም ያዘጋጀውን እንስሳ ተመገቡ ተብሎ መነገሩም በሰው አምሳል ስለ ተገለጡና ለአብርሃም የበሉ መስለው ስለ ታዩት ነው እንጂ ለሥላሴ መብል መጠጥ አይስማማቸውም (አይነገርላቸውም)፡፡

ከዚህ በተለየ ምሥጢር ሥላሴ “ሣራ ለምን ትስቃለች? በውኑ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን?” ብለው ከጠየቁበት ኃይለ ቃል መካከል “ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን?” የሚለውን እመቤታችንን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና እንደምትወልድ ሲያበሥራት ‹‹ወንድ ሳላውቅ ይህ እንዴት ሊኾን ይችላል?›› /ሉቃ. ፩፥፴፯/ ብላ በጠየቀችው ጊዜ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ደግሞ መናገሩ የእግዚአብሔር ቃል በዘመን ብዛት የማይለወጥ ሕያውና እውነተኛ መኾኑን ያጠይቃል፡፡

የአብርሃም ድንኳን

“በቀትርም ጊዜ እርሱ በድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ እግዚአብሔር በመምሬ የአድባር ዛፍ ተገለጠለት፡፡ ዐይኑንም አነሣና እነሆ ሦስት ሰዎች በፊቱ ቆመው አየ፡፡ ባያቸውም ጊዜ ሊቀበላቸው ከድንኳኑ ደጃፍ ተነሥቶ ሮጠ፡፡ ወደ ምድርም ሰገደ፡፡ እንዲህም አለ አቤቱ በፊትህስ ሞገስን አግኝቼ እንደሆነ ባርያህን አትለፈኝ” /ዘፍ.፲፰፥፲፭/፡፡

አብርሃም በዚህ ምድር ቤት አልነበረውም፤ የሚኖረው በድንኳን ነበርና በድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ ሥላሴ በሰው አምሳል ተገለጡለት፡፡ በግንባሩ ተደፍቶ የአምልኮት ስግደት ሰገደላቸው፤ በአክብሮትም ተቀበላቸው፡፡ ወደ ድንኳኑ እንዲገቡም ተማጸናቸው፡፡ አስተናገዳቸውም፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህች የአብርሃም ድንኳን ትመሰላለች፤ ምክንያቱም ሥሉስ ቅዱስ በማኅፀኗ አድረዋልና ስለዚህ ማኅደረ ሥሉስ ቅዱስ ትባላለች፡፡ ሥላሴን በማኅፀኗ ተቀብላ በትሕትና አስተናግዳለችና፡፡ አብ አጸናት፣ ወልድ ተፀነሰባት፣ መንፈስ ቅዱስ ጋረዳት፡፡/ወላዲተ አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ፤ ገጽ 30/፡፡

በአብርሃም ድንኳን አላፊ አግዳሚው ይመግብበት፣ ያርፍበት እንደ ነበረ ዅሉ በእመቤታችንም አማላጅነትም መንገደኞች ማረፍያ፤ እንግዶች መጠለያ፤ ስደተኞች ተስፋ ያገኛሉና፡፡

ከዅሉም በላይ የነፈስ የሥጋ መድኀኒት፤ የዘለዓለም ማረፍያ፤ እውነተኛ መብልና መጠጥ የኾነውን ኢየሱስ ክርስቶስን የወለደች እርሷ ናትና በአብርሃም ድንኳን ትመሰላለች፡፡

ቀትር በኾነ ጊዜ ማለትም በስድስት ሰዓት አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ወደ አብርሃም ድንኳን እንደ ገቡ ሁሉ፣ አምስት ሺሕ አምስት መቶው ዓመት ተፈጽሞ በስድስተኛው ሺሕ ዓመት እግዚአብሔር አብ ለአጽንዖ፤ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ለአንጽሖ፤ እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ ሥጋን ለመልበስ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አድረዋልና እመቤታችን በአብርሃም ድንኳን ትመሰላለች፡፡

እንደ ማጠቃለያ

ሐምሌ ፯ ቀን እግዚአብሔር አምላክ በአብርሃም ቤት ተገኝቶ አብርሃምና ሣራ ካረጁ በኋላ ልጅ እንደሚወልዱ የተበሰረበት፤ ይስሐቅንም እንደሚወልድ የተነገረበት ዕለት ነው፡፡

የእግዚአብሔርን ሰው መኾን የተናገረበት ዕለት ከመኾኑ ሌላ የአብርሃምን ዘሩን እንደሚያበዛለትና አሕዛብ ሁሉ በእርሱ እንደሚከብሩ ማለትም ከአብርሃም ዘር በተገኘው በኢየሱስ ክርስቶስ አሕዛብ እንደሚቀደሱ፤ ይህንን ምሥጢርም እግዚአብሔር ከወዳጁ ከአብርሃም እንደማይሠውር ቃል ኪዳን የገባበት ቀን ነው፡፡

በዓላት የሰው ልጅ በእግዚአብሔር የተደረገለትን የቸርነት ሥራ በማሰብ ቅዱሳን ጻድቃን ሰማዕታት ያደረጉትን ተጋድሎና ተአምራት በመስማትና በማሰማት የተደረገውን ድንቅ ነገር በመዘከር በደስታ የሚከበሩ ዕለታት ናቸው፡፡ “በቃለ አሜን ወበትፍስሕት ድምፁ እለ ይገብሩ በዓለ፡- በዓለ የሚያደርጉ ሰዎች የደስታና የምስጋና ቃል አለው” እንዳለ ቅዱስ ዳዊት /መዝ.፵፩፥፭/፡፡

ዛሬም ሀብት ንብረት ያለን ምእመናን በትሩፋት ሥራ በመሠማራት እንግዶችን በመቀበል፣ ለተራቡ በማብላት፣ በመመጽወት እና በመሳሰለው ተግባር ከኖርን ለተቸገሩ በመራራት፣ በቀና አስተሳሰብ ከተጓዝን እግዚአብሔር ይባርከናል፤ ይቀድሰናል፡፡

ሐምሌ ፯ ቀንም ሥላሴ በአብርሃም ቤት ገብተው ቸርነታቸውና ፍቅራቸውን የገለጹበት፣ አብርሃምን የባረኩትና ልጅ እንደሚወልድ፣ መጻዒው ሕይወቱን የነገሩት ዕለት ስለሆነ በዓሉን ስናዘክር ሥላሴን እናመሰግናለን፡፡ ቸርነታቸው፣ ፍቅራቸው እንዳይለየን እንማጸናለን፡፡

                    የቅድስት ሥላሴ ቸርነት አይለየን፡፡
                       ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ዋቤ መጻሕፍት
✍️ መጽሐፍ ቅዱስ
✍️ ቅዳሴ ማርያም
✍️ መጽሐፍ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ
✍️ ዓምደ ሃይማኖት
✍️ ወላዲተ አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ
✍️ መለከት መጽሔት

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

በአዲስ አበባ የታክስ ዕዳ ምህረት አሰጣጥን የሚያስተዳድር አዲስ ረቂቅ መመሪያ ወጣ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስ ቢሮ፣ በተለያዩ ከግብር ከፋዮች...

እግዚአብሔር የሰጠኝን ተልዕኮዎች ፈጽሜያለሁ የአዛዥነት ዘመኔ እያበቃ ነው

የኡጋንዳ የመከላከያ ኃይሎች አዛዥ (CDF) ጄነራል ሙሁዚ ካይኔሩጋባ ከወታደራዊ...

አሐዱ ባንክ 1ነጥብ 07 ቢሊዮን ብር አተረፈ

ባንኩ በተጠናቀቀው የሂሳብ ዓመት ከ3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር...

በጋምቤላ ከምሽት አንድ ሰዓት በኋላ ነዋሪዎች እንዳይንቀሳቀሱ ተከለከለ

ከጋምቤላ ክልል ዋና ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኘው ጋምቤላ...