በትግራይ ክልል የባንክ ዕዳ ያለባቸው ንብረቶች በሐራጅ እንዳይሸጡ ትእዛዝ ተሰጠ

Date:

ከጦርነቱ በፊት ከባንኮች ለተወሰደ ብድር መመለሻ ተብሎ በዋስትና (ኮላተራል) የተያዘ ማንኛውም የማይንቀሳቀስ ንብረት በሐራጅ ወደ ሦስተኛ ወገን እንዳይተላለፍ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ትእዛዝ ተሰጠ።

ይህ ትዕዛዝ የሚቆይበት የተወሰነ የጊዜ ገደብ አልተቀመጠለትም።

ትእዛዙ የተላለፈው በጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ሌ/ጀ ታደሰ ወረደ ተፈርሞ መጋቢት 10 ቀን 2018 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ ነው።

ደብዳቤው ለክልሉ ከተማና ኮንስትራክሽን ቢሮ የተመራ ሲሆን ለክልሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ ለፍትህ ቢሮ እና ለፖሊስ በግልባጭ እንዲያውቁት ተደርጓል።

ደብዳቤው ምን ይላል ?

” የትግራይ የንግድ ማህበረሰብ ከጦርነቱ በፊት ከባንኮች የወሰዱት ብድር መመለስ አቅቷቸው በከባድ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ ይታወቃል።

ይህ ሆኖ እያለ የወሰዱት ብድርና ወለድ እንዲመልሱ ካልከፈሉ ደግሞ የተበዳሪዎች ሃብት በሐራጅ እንዲሸጥ ከባንኮች የቀረበ ጥያቄ መኖሩን ከአቤቱታዎች መገንዘብ ችለናል።

ስለሆነም የተወሰደው ብድር እንዴት መመለስ እንደሚገባ ከሚመለከታቸው አካላት መግባባት ተደርሶበት መፍትሄ እስኪበጅለት ድረስ በባንኮች ለብድር መመለሻ ተብሎ የተያዘ (ኳላተራል) የማይንቀሳቀስ ንብረት በሐራጅ ወደ ሦስተኛ ወገን የሚደረግ ዝውውር እንዲቆም በትግራይ የሚገኙ ማዘጋጃ ቤቶች እንዲያውቁት መመሪያ እንዲሰጥና ክትትል እንዲደረግ አሳስባለሁ ” ይላል።

ከጦርነቱ በፊት የነበረው ዋና ብድር 32 ቢሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ከወለድ ጋር ተዳምሮ ከ80 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል።

ጉዳዩ ከፕሪቶሪያ ስምምነት (ጥቅምት 24/2015 ዓ.ም) ጀምሮ በተደጋጋሚ ሲነሳ የቆየ ሲሆን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር ውይይት ተደርጎበት ከብሔራዊ ባንክ እና ከገንዘብ ሚኒስቴር የተወጣጣ አገር አቀፍ ኮሚቴ ተቋቁሞለት ነበር። ሆኖም ላለፉት ሦስት ዓመታት ዘላቂ መፍትሄ ሳያገኝ ቆይቷል።

አሁን የተላለፈውን ትእዛዝ ተከትሎ የአበዳሪ ተቋማት ወገኖች ” የክልል መንግስታት በባንኮች አሰራር ውስጥ ገብተው የማዘዝ ህገ-መንግስታዊ ስልጣን አላቸው ወይ? “ የሚል ጥያቄ አንስተዋል።

@tikvahethiopia

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ምርጫ ለሰላም ግንባታ

ግዮን መጽሔት :-ለኢትዮጵያ ሰላም ምርጫ አማራጭ የሌለው መንገድ ነው።...

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ከባለፈው  ዓመት የ130 በመቶ ብልጫ  አተረፈ

መጋቢት 30 በተጠናቀቀው የኩባንያው በጀት ዓመት 15.9 ቢሊዮን ብር...

በዕውቀቱ በታላቁ ዓለም አቀፍ ፌስቲቫል ላይ ተመረጠ

ዝነኛው ደራሲና ገጣሚ በዕውቀቱ ሥዩም በስፔን ባርሴሎና በሚካሄደው 41ኛው...

ግዮን መጽሔት ዛሬ ቅዳሜ ግንቦት 1 2018 ዓ.ም ገበያ ላይ ውሏል !!!

በኢትዮጵያ ነፃ ኘሬስ ከ25 ዓመት በላይአገልግለናል !!! -የአርበኞች አደራና የትውልዱ...