የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አሜሪካ ለዩክሬን የምታደርገውን የደህንነት መረጃ ልውውጥ ካቆመች፣ እሳቸውም ለኢራን የሚሰጡትን ድጋፍ ለማቋረጥ ዝግጁ መሆናቸውን የሚገልጽ ጥያቄ ማቅረባቸው ተሰማ።
እንደ ፖለቲኮ ዘገባ ከሆነ፣ ይህ የፑቲን ልዩ መልዕክተኛ ኪሪል ዲሚትሪቭ በሚያሚ ፍሎሪዳ ከፕሬዝዳንት ትራምፕ አማካሪ ስቲቭ ዊትኮፍ እና ከትራምፕ አማች ያሬድ ኩሽነር ጋር ባደረጉት ሚስጥራዊ ስብሰባ የቀረበ ነው።
ምንም እንኳን የትራምፕ አስተዳደር ጥያቄውን ውድቅ ቢያደርገውም፣ የአውሮፓ ባለሥልጣናት ግን ፑቲን በኔቶ አጋሮች መካከል ጥርጣሬን ለመዝራት እያደረጉት ያለው ሙከራ “አሳፋሪ” ነው ሲሉ ገልጸውታል።
በሌላ በኩል ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኔቶ አጋሮቻቸውን “የወረቀት አንበሳ” (paper tiger) ሲሉ በጽኑ ተችተዋል። አጋሮቹ የሆርሙዝ ወሽመጥን ለማስከፈት ለሚደረገው ወታደራዊ እርምጃ እገዛ ለማድረግ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን የገለጹት
ትራምፕ፣ “በነዳጅ ዋጋ መናር ያማርራሉ፤ ነገር ግን ቀላል የሆነውን የባሕር መተላለፊያ የማስከፈት ዘመቻ ለመርዳት አይፈልጉም” ብለዋል። በ “ትሩዝ ሶሻል” ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍም፣ አጋሮቻቸውን “ፈሪዎች” ሲሉ የጠሯቸው ሲሆን አሜሪካ ይህን ድርጊታቸውን እንደማትረሳው አስጠንቅቀዋል።
በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው ውጥረት የካቲት 21 ቀን አሜሪካና እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት ከሰነዘሩ ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።
በዚህ ጦርነት የቀድሞው የኢራን ከፍተኛ መሪ አሊ ካሜኒን ጨምሮ እስካሁን 1,300 ሰዎች ተገድለዋል። ኢራን በበኩሏ የዓለም የነዳጅ ንግድ 20 በመቶ የሚሸፍነውን የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዝጋትና በሳውዲ አረቢያና እስራኤል ላይ የድሮን ጥቃት በመሰንዘር አጸፋ እየመለሰች ሲሆን፣ ይህም በዓለም አቀፍ የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ገበያ ላይ ከፍተኛ ቀውስ ፈጥሯል።
