በኢትዮጵያ የሪል እስቴት ዘርፍ የሚስተዋሉ ውስብስብ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት፣ የግንባታ ወጪን ለመቀነስና ለዜጎች ተመጣጣኝ የቤት አማራጮችን ለማቅረብ ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ሪል እስቴት አልሚዎች ማኅበር አስታወቀ።
የማኅበሩ ፕሬዝዳንት አቶ ዓለማየሁ ከተማ፣ ምክትል ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ጀበል የቦርድ አባል ኢንጂነር አብርሃም ደምሴ፣ እና የቦርድ ጸሐፊ አቶ ዝናቡ ተበጀ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በዘርፉ ያሉ ተግዳሮቶችንና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በዝርዝር አብራርተዋል።
በመግለጫው ላይ እንደተገለጸው፣ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ እስከ 1.5 ሚሊዮን፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ከ5.5 እስከ 6 ሚሊዮን የሚገመት የቤት ፍላጎት አለ። ይህንን ክፍተት ለመሙላት መንግሥት በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት 1.5 ሚሊዮን ቤቶችን ለመገንባት የያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ማኅበሩ ከመንግሥት አካላት፣ ከከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር እንዲሁም ከባንኮች ጋር በቅንጅት እየሠራ መሆኑ ተገልጿል።
የማኅበሩ አመራሮች አጽንኦት ከሰጡባቸው ጉዳዮች አንዱ የፋይናንስ ሥርዓቱ ነው። አሁን ባለው የንግድ ባንኮች አሠራር እስከ 20 በመቶ በሚደርስ ወለድ ተበድሮ ቤት መገንባትም ሆነ መግዛት ለመካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች የማይቻል መሆኑ ተጠቁሟል።
ይህንን ለመቅረፍ ረጅም ጊዜ የሚቆይና ዝቅተኛ ወለድ ያለው ብድር የሚያቀርብ የሞርጌጅ ባንክ መቋቋም ወሳኝ መሆኑና መንግሥትም በዚህ ረገድ ዝግጅቱን ማጠናቀቁ ተመላክቷል።
ባለፉት 20 ዓመታት የዜጎች የደመወዝ ዕድገት በ550 በመቶ ገደማ ሲጨምር፣ የግንባታ ወጪ ግን እስከ 5,000 በመቶ ማደጉ በመግለጫው ተነስቷል። ለዚህ ዋነኛ ምክንያቶች የውጭ ምንዛሬ ጥገኝነት፡ የግንባታ ግብዓቶች እስከ 70 በመቶ በውጭ ምንዛሬ ላይ የተንጠለጠሉ የአገር ውስጥ ምርት እጥረት፡ በአገር ውስጥ የሚገኙ የብረት ማዕድናትን (Iron Ore) ወደ ብረት የሚቀይሩ ፋብሪካዎች አለመኖራቸውና የሲሚንቶ ዋጋ መናር፣ የመሬትና የዲዛይን ወጪ፡ የመሬት ዋጋ ከአጠቃላይ የግንባታ ወጪ እስከ 30 በመቶ መያዙ እንዲሁም መኪና ለሌላቸው ገዢዎች ጭምር የመኪና ማቆሚያ (Parking) እንዲገነባ የሚያስገድዱ የዲዛይን መመሪያዎች የቤት ዋጋን ማናራቸው ተገልጿል።
በዘርፉ በጥቂት አልሚዎች ምክንያት የሕዝብ አመኔታ መሸርሸሩን የገለፁት አመራሮቹ፣ አዲሱ የሪል እስቴት አዋጅና በቅርቡ የሚጸድቀው ደንብ ችግሩን እንደሚቀርፉት ገልጸዋል። በዚህም መሠረት፡-
የእስክሮ አካውንት (Escrow Account)፡ ከገዢዎች የሚሰበሰብ ገንዘብ ለታለመለት ፕሮጀክት ብቻ እንዲውልና በቁጥጥር ሥር እንዲተዳደር ይደረጋል።
የግጭት አፈታት (Arbitration)፡ ከዚህ ቀደም በገዢና በአልሚ መካከል የተፈጠሩ አለመግባባቶችን ከንግድ ምክር ቤት ጋር በመተባበር በሽምግልናና በግልግል ዳኝነት የመፍታት ሥራ መጀመሩ ተገልጿል።
የግንባታ ጥራትና ደህንነት (Safety)፡ የግብዓት ፍተሻና የሠራተኞች ደህንነት ጥበቃ በጥብቅ እንዲተገበር ከዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት (ILO) እና ከመንግሥት ተቋማት ጋር በመተባበር ሥልጠናና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑ ተጠቁሟል።
የሪል እስቴት ዘርፉን በእውቀትና በተጠያቂነት ለመምራት አልሚዎችን የመመዘንና ደረጃ የመስጠት (Rating) ሥርዓት እንደሚዘረጋ የገለጸው ማኅበሩ፣ መገናኛ ብዙኃንም በጥናትና በመረጃ ላይ የተመሠረተ ዘገባ በማቅረብ ሕዝቡን እንዲያነቁና ችግሮችን በጋራ ለመፍታት እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርቧል።
