የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የናይል ወንዝን ተፋሰስ በተለይም ሱዳንና ግብፅን ከአጥፊ ጎርፍ በመከላከል ትልቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑን የኢትዮጵያ መንግስት ገለጸ።
የዉሃና ኢነርጂ ሚኒስትር በመግለጫው፣ ግድቡ ባይኖር ኖሮ በቅርብ ወራት በኢትዮጵያ ደጋማ አካባቢዎች የተከሰተው ከፍተኛ ዝናብ በታችኛው ተፋሰስ አገራት በሰው ሕይወትና በመሰረተ ልማቶች ላይ ታሪካዊ ውድመት ሊያስከትል ይችል እንደነበር አስታውቋል።
ሚኒስቴሩ፤ የግብፅ የመንግስት ተቋማት ስለ ግድቡ በሚያወጧቸው የህዝብ መግለጫዎች ውስጥ ውሸቶች ዋነኛው አካል መሆናቸውን በመጥቀስ እየቀረበ ላለዉ ክስ ምላሽ ሰጥቷል።
በሱዳን ለ93 ዓመታት የተመዘገበው መረጃ እንደሚያሳየው፣ ግድቡ ከመገንባቱ በፊት በነበሩት ነሐሴ ወራት የጎርፍ መጠኑ በቀን ከ 800 ሚሊዮን ሜትር ኩብ በላይ ሊሆን እንደሚችል በመግለጫው ተመላክቷል።
ይሁን እንጂ እኤአ በነሐሴና መስከረም 2025 ከግድቡ የተለቀቀው አማካይ የቀን ውሀ በቅደም ተከተል 154.7 ሚሊዮን ሜትር ኩብ እና 472 ሚሊዮን ሜትር ኩብ ብቻ እንደነበር ሚኒስትሩ አስታዉሷል።
የግብፅ ባለሥልጣናት የጎርፍ አደጋዎችን ምክንያት በማድረግ በኢትዮጵያ ላይ የሚሰነዝሯቸው ክሶች መሠረተ ቢስ መሆናቸውን የኢትዮጵያ መግለጫ አውግዟል።
በተቃራኒው፣ የሱዳን የግብርና እና መስኖ ሚኒስቴር በሱዳን የታየው የጎርፍ መንስኤ በዋነኛነት ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነት የሌለው፣ ከ ነጭ አባይ የሚመጣው የውሃ ፍሰት መጨመር እና ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተያያዘ መሆኑን ማስታወቁን መግለጫው ጠቁሟል።
CapitalNews
