በእስራኤል እና ኢራን መካከል እየተካሄደ የሚገኘው ግጭት ተባብሶ በመቀጠሉ በርካታ አየር መንገዶች ወደ መካከለኛው ምስራቅ የሚያደርጉትን በረራዎች ለመሰረዝ ተገደዋል፡፡
ጦርነቱ አለምአቀፍ የአየር ጉዞን በማስተጓጎል በረራዎች እንዲሰረዙ እንዲሁም የመብረሪያ መስመሮችን እንዲቀይሩ እያደረገ ይገኛል፡፡
በመካከለኛው ምስራቅ የአየር ትራንስፖርት ማዕከል በሆነችው ኳታር የዶሃ አውሮፕላን ማረፊያ ኢራን በአሜሪካ ወታደራዊ ካምፕ ላይ ባካሄደችው ጥቃትን ተከትሎ ስራ አቁሞል፡፡
እንዲሁም የዱባይ አየር መንገድም ሲያደርጋቸው የነበሩትን በረራዎች ለጊዜው ማገዱን አስታውቋል፡፡
ኤር ኢንዲያ ወደ መካከለኛው ምስራቅ የሚያደርጋቸውን በረራዎች በሙሉ እንደሚያቆም እና ወደ ሰሜን አሜሪካ እና አውሮፓ የሚያደርገውን በረራዎች እንደሚሰርዝ አስታውቋል።
በተመሳሳይ የጃፓኑ ኤር ላይንስ ደግሞ ከቶኪዮ ወደ ዶሃ የሚያደርገውን በረራ መሰረዙን አሳውቋል፡፡
ከግጭቱ መባባስ ወዲህ በመካከለኛው ምስራቅ በየቀኑ ከ3,000 በላይ በረራዎች መሰረዛቸውን ፍላይት-ራዳር 24 ይፋ ያደረገው መረጃ ይጠቁማል፡፡
እስራኤል የመጀመሪያውን ጥቃት በኢራን ላይ ከፈጸመች በኋላ ከመደበኛ የተሳፋሪዎች በረራ በተጨማሪ የንግድ አውሮፕላኖች ከመብረር ተቆጥበዋል።
በዚህም በቀን 1,400 የሚጠጉ በረራዎች በቱርክ ወይም በሳውዲ አረቢያ በኩል እንዲጓዙ ተገደዋል፡፡
ኩዌት፣ባህሬን፣ ሶሪያ፣ሊባኖስ፣እና ኢራን የአየር ክልላቸውን የዘጉ ሀገራት ሲሆኑ ኢራቅ እና ዮርዳኖስ በተደጋጋሚ የአየር ክልላቸውን ሲዘጉ እና ሲከፍቱ የነበሩ ሀገራት ናቸው፡፡
እስራኤል የአየር ክልሏን ለቅድመ ጥንቃቄ በሚል በቀዳሚነት የዘጋች ሀገር ናት፡፡
በርካታ አየር መንገዶችም የበረራ መስመራቸውን ለመቀየር የተገደዱ ሲሆን ከእነዛም መካከል ሉፍታንሳ፣ ኤር ፍራንስ፣ ብሪቲሽ ኤር ዌይስ፣ ኤር ኢንዲያ፣ ሲንጋፖር ኤርላይንስ እና የተለያዩ የአሜሪካ አየር መንገዶች ይገኙበታል፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ እስከ 820 በረራዎች መሰረዛቸውን የፍላይት አዌር (Flight Aware) መረጃ ያሳያል።
አየር መንገዶቹ የግጭት ሰለባ በሆኑ ሀገራት የሚያደርጉትን በረራዎች ላለመሰረዝ አማራጭ መንገዶች እየተጠቀሙ ይገኛሉ፡፡
አውሮፕላኖቹ የሚያደርጉት ረጅም በረራዎች በርካታ ነዳጅ እንዲጠቀሙ ያደርጋቸዋል።
ይህ ደግሞ የነዳጅ ዋጋ እየጨመረ ባለበት ወቅት ለአየር መንገዶቹ ተጨማሪ ወጪ ያስከትላል።
የመብረሪያ መንገዳቸውን የቀየሩ አየር መንገዶች አዲስ የአየር ክልሎችን በመጠቀማቸው ተጨማሪ ክፍያዎችን እንዲከፍሉ ይገደዳሉ፡፡
የአየር መንገዶቹ የሚያጋጥማቸውን ከፍተኛ ወጪ ለመሸፈን የቲኬት ዋጋዎችን ከፍ ሊያደርጉ እንደሚችሉ የዘርፉ ባለሙያዎች ሀሳባቸውን እየሰጡ ይገኛሉ፡፡
በመካከለኛው ምስራቅ ያለው ግጭት የአየር መንገዶችን በረራዎች አቅጣጫ እንዲቀይሩ በማስገደድ ለአደጋ ተጋላጭ የሚሆኑበትን እድል እያባባሱ ይገኛል።
ቀድሞውንም በሩሲያ-ዩክሬን ግጭት ምክንያት ወደ መካከለኛው ምስራቅ የተዘዋወሩትን በረራዎች አሁን ደግሞ በእስራኤል እና ኢራን ጦርነት ምክንያት ወደ ሌሎች አየር ማረፊያዎች ፊታቸውን ማዞራቸውን ተከትሎ ከፍተኛ ጫናን በአየር መንገዶቹ ላይ እየፈጠሩ ይገኛሉ ተብሏል፡፡
በ-ሀሴት ሀይሉ
