የኢትየጵያ አርቲፊሺያል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት አምስት ሀገርኛ ቋንቋዎችን የማሽን ቋንቋ ማድረጉን ለአሐዱ አስታውቋዋል።
ይህም ተቋሙ በመረጃ ወይም በዳታ ላይ የተመሰረቱ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂዎችን በማልማት ጥቅም ላይ ለማዋል እየሰራ ያለው ሥራ አካል መሆኑን፤ የኢንስቲትዩቱ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ተስፋዬ ዘውዴ ገልጸዋል።
በዚህም መሠረት ማሽኖች 5 የኢትዮጵያ ቋንቋዎችን ማለትም አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ሶማሊኛ፣ ትግርኛ እና አፋርኛን ማወቅ እንዲችሉ መደረጉን አንስተው፤ “በዚህም የተለያዩ ዘርፎች ላይ በእነዚህ ቋንቋዎች አገልግሎት መስጠት እንዲቻል ሆኗል” ብለዋል።
እነዚህ አምስት ቋንቋዎች የማሽን ቋንቋ በመሆናቸው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ስማርት ኮድ ሲስተም ከዓመት በፊት ሥራ መጀመሩን እንዲሁም፤ የፌደራል ፓሊስ ጥቆማ መስጫ መተግበሪያ (EFP APP) እንግሊዝኛ ቋንቋን ጨምሮ በተለያዩ የቋንቋ አማራጮች እንዲቀርቡ ማስቻሉን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
ማሽንን ቋንቋ ማስተማር ከረጅም ዓመታት በፊት የነበረ መሆኑን ያስታወሱት ዳይሬክተሩ፤ “በተደራጀ እና ደርዝ ባለው መረጃ መሠረት ማሽን ቋንቋን እንዲማር ይደረጋል” ብለዋል።
ይህም በተለያዩ የቋንቋ አማራጮች ለሚቀርበለት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እና ይዘቶችን ለመፍጠር የሚያግዝ መሆኑን አብራርተዋል።
” ‘ማሽንን ማስተማር’ ማለት የሰውን ልጅ የንግግር ችሎታ፣ ቋንቋን እንዲሁም በትምህርትና በሥራ የተገኙ ክህሎቶችን የማስተማር ሂደት ነው” ሲሉም ገልጸዋል።
ኢንስቲትዩቱ በተመረጡ ችግር ፈቺ የምርምር ሂደቶች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ የገለጹም ሲሆን፤ እንዲሁም በተፈጥሮ ቋንቋ ቅንብር፣ ማሽን በማስተማር፣ የሰው ሰራሽ አስተውሎትና ሮቦቲክስ ላይ እና ኮምፒውተር ቪዥን በተሰኙ አምስት ፕሮግራሞች ላይ ምርትና አገልግሎቶችን በማውጣት አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን አንስተዋል።
(አሐዱ ሬዲዮ)
