አርሶ አደሮች ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ማግኘት ችለዋል

Date:

በኢትዮጵያ በተዘረጋው ብሔራዊ የገጠር መሬት መረጃ ስርዓት አማካኝነት አርሶ አደሮች ከፋይናንስ ተቋማት ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ማግኘት መቻላቸው ተገልጿል።

ይህ የተገለጸው የግብርና ሚኒስቴር “በኃላፊነት የሚመራና ፈጠራን ያካተተ የመሬት አስተዳደር ፕሮጀክት” ከአለም አቀፍ የከፊል ደረቃማ አካባቢዎች የሰብል ምርምር ተቋም ጋር በመተባበር፣ የመሬት ይዞታ መብትን መሰረት ያደረገ የብድር ዋስትና ስርዓትን ይበልጥ የሚያቀላጥፍ አዲስ የዲጂታል ውሳኔ ድጋፍ ሰጪ መሳሪያ ይፋ ባደረጉበት መድረክ ላይ ነው።

በግብርና ሚኒስቴር የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ሻንቆ ቴሶ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ የእርሻ መሬት ወደ ብሔራዊ የመረጃ ስርዓት መግባቱ አርሶ አደሮች በቀላሉ የባንክ ብድር እንዲያገኙና ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ ሰፊ እድል ፈጥሯል።

አሰራሩ እስካሁን በ568 ወረዳዎች ተግባራዊ መደረጉን የጠቀሱት አቶ ሻንቆ፣ ከፋይናንስ አቅርቦት ባለፈ በአርሶ አደሮች መካከል ይነሱ የነበሩ የድንበር ይገባኛል ውዝግቦችን በዘላቂነት ለመፍታት ማስቻሉንም አስረድተዋል።

በመድረኩ የተዋወቀው አዲሱ ዲጂታል መሳሪያም ባንኮች ለመሬት ይዞታዎች የሚሰጡትን የብድር ዋስትና ሂደት ይበልጥ ፈጣንና አስተማማኝ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑ ተመላክቷል።

የፕሮጀክቱ ዋና የቴክኒክ አማካሪ ፓውል ዴ ዊት በበኩላቸው፣ ፕሮጀክቱ ላለፉት 15 ዓመታት የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ምዝገባን፣ የመረጃ አያያዝንና የማዳበሪያ ስርጭትን በማዘመን ላይ ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ የገጠር መሬት መረጃ አያያዝን ወደ ዘመናዊ ዲጂታል ስርዓት በማሸጋገር ረገድ ውጤታማ ተሞክሮ እንዳላት የገለጹት አማካሪው፣ በቀጣይም ስርዓቱን ይበልጥ ለማዘመን ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

የግብርና ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች፣ የባንክ ተወካዮችና ባለድርሻ አካላት በተሳተፉበት በዚህ መድረክ፣ በብድር አሰጣጥ ሂደት ያጋጠሙ ማነቆዎችን በመለየት ዘላቂ መፍትሔ በሚሰጥባቸው ጉዳዮች ላይ ምክክር ስለመደረጉ ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

በአዲስ አበባ የታክስ ዕዳ ምህረት አሰጣጥን የሚያስተዳድር አዲስ ረቂቅ መመሪያ ወጣ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስ ቢሮ፣ በተለያዩ ከግብር ከፋዮች...

እግዚአብሔር የሰጠኝን ተልዕኮዎች ፈጽሜያለሁ የአዛዥነት ዘመኔ እያበቃ ነው

የኡጋንዳ የመከላከያ ኃይሎች አዛዥ (CDF) ጄነራል ሙሁዚ ካይኔሩጋባ ከወታደራዊ...

አሐዱ ባንክ 1ነጥብ 07 ቢሊዮን ብር አተረፈ

ባንኩ በተጠናቀቀው የሂሳብ ዓመት ከ3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር...

በጋምቤላ ከምሽት አንድ ሰዓት በኋላ ነዋሪዎች እንዳይንቀሳቀሱ ተከለከለ

ከጋምቤላ ክልል ዋና ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኘው ጋምቤላ...