ከአለባቸው ደሳለኝ አበሻ (ለንደን)
ፈጠራ ሲባል በኪነጥበብ መስክ ከሕሊና የሚመነጩ ምናባዊትና ውበትን አጣምረው የሚይዙ ጥበባዊ ሥራዎችን የሚያካትት መሆኑ ይታወቃል፡፡ እነዚህም የጥበብ ውጤቶች ውስጣዊ ስሜትን ሊነኩና ማነትን ሊፈታተኑ የሚችሉ ማኅበረሰባዊ ኃይል ያላቸውና አዳዲስ ሐሳቦችን፣ እምነቶችንና አስተሳስቦችን ሊፈነጥቁ እንደሚችሉ እርግጥ ነው፡፡
ለዚህ ነው የፈጠራ ሰው እራሱ ፍጡር ሆኖ ፈጣሪ ነው የሚባለው፡፡ የተለያዩ ገፀ ባሕሪያትን መስሎ፣ የመሰለውን እንደሆነ ያክል አስመስሎ መተወን በመቻሉ በኢትዮጵያ የፊልም ታሪክ ውስጥ ላስቅመጣቸው የራሱ የሆኑ የትወና አሻራወች በትልቅ ከፍታ ላይ ይገኛል፡፡
ጥበብ የሌሎችን ሕይወት እንደለወጠችው ሁሉ የግሩም ኤርሚያስንም የህይወት ጎዳና መርታ ዛሬ ለደረሰበት ዝና አብቅታዋለች፡፡
ወዳጆቼ፡- የዛሬው የብዕር እንግዳዬ በበርካታ የፊልም አፍቃርያዎች ዘንድ የሚታወቀው ተወዳጁና ሽቅርቅሩ የጥበብ ሰው ግሩም ኤርሚያስ ነው፡፡ ግሩም ኤርሚያስ ከሀያ በላይ በሰራቸው ፊልሞች ብቃት ባለው ትወና ደመቆ ታይቶባቸዋል፡፡ ስለ ፊልም ጥበብና ስለገጠመኞቹ ሲያወጋኝ በሚገርም ሁኔታ እንባዬ እስኪወርድ ድረስ አስቆኛል፡፡ አልፎ አልፎም ስሜቴ እንዳይጎዳ እየተጠነቀቀ አሳዛኝ ገጠመኞቹን ቀዝቃዛ ቢራችንን እየተጎነጨን ጊዜ ወስደን ተጨዋውተናል፡፡ ለዚህ አይደል፣ የጥበብ ሰወች ከሕይወት ያልተነጠሉ ከሰው ልጆች ገጠመኝ ያልተገነጠሉ ከኑሮ ውጣ ውረድ እውነታ ያላፈነገጡ ናቸው የሚባለው?!
ግሩም ኤርሚያስ ለምን የፊልም ሞያ እንደመረጠ አሁን ለደረሰበት የዝና ከፍታ ስንት እርከኖችን እንደወጣ በኔ ጠያቂነት በሱ መላሽነት የህይወት ጉዞውን ዳሰሳ አድርጌ ለናንተ ወዳጆቼ ጣፋጭ ታሪክ ይዤ ቀርቢያለሁ፡፡
ግሩሜ ድብቅ ሳይሆን ግልፅ ሰው ነው፡፡ ለማቀርባቸው ጥያቄዎቼ እውነቱን ሳይደብቅ በግልፅ አጫውቶኛል፡፡ ወደ ትወና የገባውም ሙያው በጣም ስለሚያስደስተው የተለያዩ ታሪኮችንና ገጸ ባህሪያቸውን መጫወት የበለጠ ደስተኛ ያደርጉት ስለነበረ መሆኑን ነግሮኛል።
‹‹ትወና የሙያ መንገዴን እንደከፈተለተልኝ የተረዳሁት ከሞያው ጋር ያስተሳሰረኝ የጋራ የህይወት ጉዞ እንዳለን ያወኩት ተዋናይ መሆን እንዳለብኝ ስወስን ነው›› ይላል፡፡ ‹‹ተዋናይ ለመሆን ስወስን ቤተሰቦቼ ድጋፍ ስለአደረጉልኝ ብዙም ችግር አልገጠመኝም። ለትወና የሚረዳኝን ትምህርቴን በሆሊላንድ ትምህርት ቤት ገብቼ ስከታተል በጣም ጥሩ ልምዶችን ቀስምኩ፡፡ የዝግጅት፣ ትወና እንዲሁም የጽሑፍ ፊልም ትምህርቶቼን ስጨርስ ፕሮፌሽናል የትወና ጉዞዬን ጀመርኩ፡፡›› ሲልም ይቀጥላል፡፡
‹‹በዚህ ወቅት የተገነዘብኩት ቢኖር ከካሜራው ጀርባ ያሉ ብዙ ሰዎች አብረውኝ እንደሚሰሩ ስመለከት ሁልግዜም ከካሜራ ፊት መሆን ያስደስተኝ ጀመር። ሙያው ብዙ ጫና ያለበት በመሆኑ ጥሩ የሕይወት ሚዛን አስፈላጊ ነው፡፡ ለምን ብትል ፊልም ላይ ትክክለኛ ሆኖ ለመጫወት ከፍተኛ ልምምድና ጥረትን ይጠይቃል፡፡ ከሀያ በላይ ፊልሞችን ሰሰራ የተለያዩ ባህሪዎችን ወክዬ ነው የተጫወትኩት፡፡ አንዳንዶቹ አስቂኝ ሌሎቹ ደግሞ አሳዛኞች ነበሩ፡፡ ከቤተሰባቼ ጋር ከማሳልፈው የበለጠ በልምምድ ላይ የማጠፋው ጊዜ ይበልጣል፡፡ ለሰራሗቸውም ሥራዎች ከተለያዩ ድርጅቶች “ምርጥ ተዋናይ” ተብዬ ተሸልሜያለሁ። የክብርና እውቅና፣ የምስጋና ሽልማቶችም ተበርክተውልኛል›› ይላል፡፡
ግሩም ኤርሚያስ የራሱ የሆነ ጠንካራ ስብዕናና እምቅ ችሎታ እንዳለው ለማወቅ ጊዜ አልፈጀብኝም፡፡ በትዕግስት ሲያዳምጠኝ ተሰጥኦና ማገናዘብ ብቻም ሳይሆን መልካም ስነ-ምግባሩ ሚዛኑን ከፍ ያደርግዋል፡፡ ሐሳቤን ለመግለፅ ብዕሬን ያስጨበጠኝ ይህው የጥበብ ሰው ነው ፤ ግሩም ኤርሚያስ፡፡
በጥቅምት ወር 2024 ለአንድ አይነት የፕሮጀክት ስራ ተጋብዘን፣ እሱ ከአዲስ አበባ እኔ ከለንደን ተነስተን የአለም ቱሪስት በሚጎርፍባት ትንሿ ሐገር ማልታ ላይ በታሪክ አጋጣሚ ተገናኘን፡፡ ከግሩም ኤርሚያስ ጋር በነበርን የሶስት ቀን ቆይታ በሜዲትራኒን ባህር ተከባ ስለምትገኘው ትንሿ ደሴት ማልታ በጉብኝት ወቅት ስላየነው ታሪካዊ የማልታ ፊልም ስቱዲዮ ብዙ ሐሳቦችን እያነሳሳን ተጨዋውተናል፡፡ በተለይ የፊልም ኢንዱስትሪያቸውን ለማዘመንና አለም አቀፍ የፊልም ሞያተኞች ትኩረት ለመሳብ የጥንታዊ ሮማን ኢንፖየር ህንፃን ከነፍርስራሹ በስቱዲዮ ቅርፅ ገንብተው ያደረጉት ፈጠራ አስደንቆናል፡፡
በአንፃሩ ደግሞ ባለቤት አልባው ኢትዮጵያ ፊልም ኢንዱስትሪ የሚጓዘውን የኤሊ እርምጃን እያነፃፀርን መስራት እየቻልን ባለመስራታችን ተቆጭተናል፡፡ አሁን ባለው ይዘት ለመቀጠል ዋስትና የሌለውን የኢትዮጵያ ፊልም ኢንዱስትሪን ባስብን ጌዜ አለማንሳቱን መርጠን ወደ ግል ጉዳያችን ገብተን ጨዋታ ጀመርን፡፡
ከላይ እንደገለፅኩላችሁ ተዋናይ ግሩም ኤርሚያስ ከሐያ በላይ የሚቆጠሩ ፊልሞችን ተጫውቷል፡፡ ነገር ግን ሙሉ በሙሉ ሁሉንም ፊልሞቹን ለማየት እድል አልገጠመኝም፡፡ በኔ ምርጫ ግን የሰላ አንደበት “ድንቅ ብቃቱን” ተመልክቼ የሰጠሁት ደረጃ ‹‹አፊኒ›› በተሰኜው ፊልም ውስጥ የተወነውን ፈታኝ ባሕሪ ከተመለከትኩ በሗላ ነው፡፡
የማልታ ፊልም ፌስቲቫል ላይ ቀርቦ የተመለከትኩት ‹‹አፊኒ›› የተሰኜው ፊልም የሲዳማ ሕዝብ ለዘመናት ጠብቆና ተንከባክቦ ያቆየው የራሱ የሆነ የግጭት አፈታት ዘዴን የሚያሳይ ሲሆን ቀጥተኛው የአማርኛ ትርጉሙም ‹‹ሰማችሁ ወይ!!›› እንደ ማለት ነው፡፡ በአካል ተገኝቼ እንዳየሁት ለንደንና ማልታ ላይ ፊልሙ በጣም ጥሩ ተቀባይነት አግኝቷል።
አፊኒ እርቅን ለመፍጠር በአደባባይ ሸንጎ የሚካሒያድ የሲዳማ ባህላዊ ሕገ ደንብ ነው፡፡ በሲዳማ ባህል አንድ ሰው ቢበደልም ለታላላቆቹ ‹‹አፊኒ (ሰምታችሗል)››በማለት ሳያሳውቅ እርምጃ የወሰደ እንደሆነ ከባድ ቅጣት ይጣልበታል፡፡ በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት እንዲያጣና ማኅበራዊ እንቅስቃሴው ላይ ያለውን ሥልጣንና ተሳትፎ እንዲነሳ የሚደነግግ ሕግ ይወሰናል፡፡ እንዳይሸጥና፣ እንዳይገበያይ፣ ልጆቹን እንዳይድር፣ እቁብ እንዳይገባ፣ እሳት እንኳን ከጎረቤት እንዳይጭር ማኅበራዊ እገዳ ይጣልበታል፡፡
ይህ ሁሉ ታሪክ የታጨቀበትን ፊልም በመሪ ተዋናይነት የሰራው የጥበብ ሰው ግሩም ኤርሚያስ ነው እንግዲህ ታሪኩን ያጫወተኝ፡፡
ግሩሜ ይቀጥላል፡-
‹‹ከላይ በዝርዝር እንዳስረዳውህ፣ ልሰራ የተዘጋጀሁት ፊልም ይህንን ይመስላል፡፡ ፊልሙ ልቦለድ ሳይሆን የአንድ ታላቅ ማህበረሰብ ታሪክና ባህል ጠንቅቆ የሚያስረዳ የሲዳማ ሕዝብ ቅርስ ነው፡፡ ታዲያ ይህን ታላቅ ታሪካዊ ኃላፊነት እንድወጣ ዳይሪክተሩ ታሪኩ መኮነን (ዘታሪያን) ሲመርጠኝ ትልቅ ተስፋና እምነት ጥሎብኝ ነው፡፡ ብታምንም ባታምንም አለቤ! ሌሊቱን ሙሉ እንቅልፍ አልተኛሁም፡፡ የተውኔቱ ጽሑፍ በእጄ ከገባበት ቀን ጀምሮ የተሰጠኝን ገፀ ባሕሪ ማንነት፣ ያለበትን ሁኔታ ከሌሎቹ ገፀ ባህሪያት ጋር ያለውን ግንኙነት ሌት ከቀን ማጥናቴን ቀጠልኩ፡፡ ዳይሬክተሩን በትወናዬ እስከማሳምን ድረስ መለማመድ ነበረኝ።
‹‹ቀጥዬ ያደረኩት ቅድመ ዝግጅት የሲዳማን ባሕልና ታሪክ እያነበብኩም እየጠየኩም የማኅበረሰቡን ስሜቶች በደንብ ማጥናት ነበረብኝ፡፡ እንደቤተሰብ ተሳስበው በፍቅር የሚኖሩ ህዝቦች ፍቅራቸውን የሚሸረሽር ሰይጣን በመሐከላቸው ሲገባ ጦር ተማዘው እርስ በእርስ እንዳይጠፋፉ የሚከለክል የሚያስቀና እድሜ ጠገብ የሕግ ሥርዓታቸው አስደመመኝ፡፡ ቀጥሎ የሚቀረኝ በአካልና በሥነ ልቦና እራሴን ማዘጋጄት ነበረብኝ፡፡ የቃኜሗቸውን አካባቢዎች፣ ያስተዋልኩትን የህብረተሰብ የአኗኗር ዘይቤ፣ የባህል አልባሶቶቻቸውን፣ ንግግሮቻቸውን፣ ሙዚቃወቻቸውን፣ ጭፈራዎቹን፣ የጦር ስልቶቻቸውን፣ ፈረስ ግልቢያን ጨምሮ ከተሰጠኝ ባህሪ ጋር እንዴት አድርጌ በጥበብ እያዋዛሁ መጫወት እንዳለብኝ ረጅም ጊዜ ወስጄ ለሦስት ወር ተለማመድኩ፡፡
‹‹የወከልኩት ባህሪ በጣም ፈታኝ የሚያደርገው ፊልሙ በደስታና በፍቅር፣ በጥላቻና በሐዘን በቀልና ግድያንም ይጨምራል፡፡ ለዚህ ፊልም ሲባል ሲዳምኛ ቋንቋ በአማርኛ ዘዬ መማር ነበረብኝ። የሻቦላ ፍልሚያን የባህል ጭፈራን ግብርናንና ባህላዊ ቤት አሰራርን ተለማመድኩ፡፡ ለምን መሰለህ አለቤ፣ አድካሚ ልምምዶች ለምንወክላቸው ገፀ ባህሪያት ይበልጥ ሥራህ እየገዘፉ እንዲሂድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያደርጉ አስቀድሜ እራሴን አሳምኜዋለሁ፡፡ ለሶስት ወር ልምምድ ከአደረኩ በሗላ አራት ወር የፈጀውን ቀረፃ ጀመርን፤ እስክንጨርስ ድረስ በዚያች የገጠር መንደር መንፈሴ እንደተሟሟቀ ነበር የጨረስኩት፡፡
‹‹ፊልሙን እንደተመለከትከው ማህበረሰባቸውን ለመጠበቅ ባሕላቸውንና ማንነታቸውን ለመከላከል ‹አፊኒ› (ሰምታችሗል) የሚል ባህላዊ የሕግ ሥርዓት አቁመው በሐገር ሽማግሌዎች ፍትህ ይጠይቃሉ፡፡ ባሕልና ወግ ልማድ እንዳይጣስ፣ በፍቅርና በይቅርታ የኑሮ ዘይቤው እንዲቀጥል የሲዳማ ‹አፊኒ› ሸንጎው ሙግት የገጠሙትን ባላንጣዎች እንዳይካረሩ በመገስፅ በይቅርታ ችግሮቻቸውን እንዲፈቱ ይወተውታል። ይህንን የሽማግሌዎች ውሳኔ ካልተቀበሉ በሲዳማ ባህል እንደ ትልቅ ነውር ተቆጥሮ ያስወግዛል፡፡ በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት እንዲያጣና ማኅበራዊ እንቅስቃሴው ላይ ያለውን ሥልጣንና ተሳትፎ እንዲገደብ ይደነግጋል፡፡
‹‹ስለዚህ የኔ የሙያ ኃላፊነት የተሰጠኝን ገፀ ባህሪ ወክዬ የሲዳማ ቅርስ የሆነውን ባሕላዊ የፍትህ ሥርዓትን መልዕክቱ ሳይዛነፍ የተመልካቾቼን ስሜት ሊኮረኩሩና ሕሊናቸው ውስጥ ሊቀሩ የሚችሉ ትዝታዎችን ማስቀመጥ ነው፡፡ በእኔ እምነት አፊኒ እንደማንኛውም ማኅበራዊ ሕግ በትምህርት ፖሊሲ ተቀርፆ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ጥናትና ምርምር ሊደረግበት የሚገባ ሐገር በቀል የፍትህ ሥርዓት ነው። ቅንነት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ሁሉ በቀልና ቂም አቁመው፣ መከባባር ሰፍኖ፣ መደማመጥን ባህል አድርገው ዝቅ ብለው በትህትና ይቅርታ የሚጠያየቁበት ልባዊ ውሳኔ ያስፈልጋል፡፡ ትውልድን በተግባር በናሙናዊነት ለመቅረፅ በአፊኒ ሕግ ውስጥ ሁላችንም በክብር አለን።
‹‹በመጨረሻም ይህንን ፊልም ጀምረን እስክንጨርስ ድረስ የሲዳማ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ላደረገልን ትብብር ምስጋና ማቅረብ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ተቀብለው ላስተናገዱን ፍቅር ለሆኑት ለሲዳማ ሕዝብ አብረውኝ በተወኑት ሙያተኞች ሥም ከፍ ያለ ምስጋናዬ ይድረስልኝ፡፡››
አፊኒ ፤ ሠምታችሗል!
———-
ቅጽ 6 ግዮን ቁጥር 217 ጥቅምት 16 ቀን 2017 ዓ.ም
