መንደርደሪያ
ትምህርት በዓለም ላይ በየዘርፉ የሠለጠነ የሰው ኃይል በማቅረብ በኩል ትልቅ ሚና ካላቸው ዘርፎች መካከል ዋነኛው ነው፡፡ የሀገራት እድገት የሚወሰነውም በዚሁ የተማረ ኃይል ለሀገሩ በሚሰጠው ሁለገብ ግልጋሎት ላይ ተመሥርቶ ነው፡፡ በእውቀት የበለጸገ ዜጋ እስከሌለ ድረስ ሀገርን ማሳደግ የሚለው ዲስኩር ከንቱ ምኞት ብቻ ይኾናል፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚኾነው ደግሞ አሁን ላይ የአደጉ ሀገራት የደረሱበት ደረጃ ለመድረስ የሔዱበት የትምህርት ሥርዓት ነው፡፡ ሀገራት ለማደግ በዕውቀት የታነጸና የበቃ ዜጋ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ከዚህ አንጻር በሀገራችን ትምህርትን ለሁለንተናዊ ዕድገት ለመጠቀም በማሰብ በጣም አርፍደንም ቢኾን በአጼ ምንሊክ ዘመነ መንግሥት ዘመናዊ የትምህርት መሠረተ ልማት እንደተቋም ሊዘረጋ ችሏል፡፡ ከዚያን ዘመን ጀምሮ ትምህርት በሀገራችን ብዙ እየተባለለት እስካለንበት ዘመን ደርሷል፡፡ በተለይም ከነገሥታቱ መውደቅ በኋላ የሀገራችን ሥርዓተ ማኅበር በተቀየረ ቁጥር መንግሥታቱን እየመሰለና በየጊዜው የፖሊሲ ለውጥ እየተደረገበት በትውልዱ ላይ አሻራውን እያሳረፈ ቀጥሏል፡፡
የትምህርት ከዐውድ ውጪ መዋል
ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ደግሞ ትምህርት በሀገራችን ከሀገራዊ እድገት መሣሪያነቱ ይልቅ የፖለቲካ ትግል መሣሪያ አድርጎ መጠቀም እየጎለበተ የመጣ ጉዳይ ኾኗል፡፡ የሀገራችን የትምህርት ሥርዓት የሚጎድሉት ነገሮች እንዳሉ ኾነው፣ ከዐውዱ ውጪ ለፖለቲካ መታገያነት ሲውል ደግሞ ሥልጡን ዜጋ የመፍጠሩ ነገር ዝንጋኤ ውስጥ ይወድቃል፡፡ ለዚህም ይመስላል ያለፉትን ሠላሳ ዓመታት በርካታ ዲግሪ ያላቸው ዜጎች ቢፈሩም ሀገሪቱ ካላንዳች ለውጥ ወደነውጥ መንደር እየተንደረደረች የገባችው፡፡ ከጅምሩ የህወሓት ታጋዮች፣ የኦነግ ታጋዮች፣ የሻዕቢያ ታጋዮች፣ እና ሌሎችም ለትግል የተነሱት ከትላልቆቹ የትምህርት ተቋሞቻችን ነው፡፡
ኋላ ላይም አሸናፊ ኃይሎች መንግሥት ኾነው ሲመጡ በትምህርት ሥርዓቱ ላይ የራሳቸውን የፖለቲካ ሰይፍ አሳርፈውበታል፡፡ ይህ ደግሞ እንደሀገር በትምህርት ሥርዓቱ ላይ የራሱ ቀውስና ውድቀት አሳርፎበት አልፏል፡፡ በሀገራችን ያለው የትምህርት ፍትሐዊነትም ሚዛን እንዲያጣ ኾኗል፡፡ ‹‹ትምህርት ለሁሉም›› የሚለው ትልቁ ተቋምም እንዳለው ትምህርትን ለሁሉም ለማድረስ ሲታትር ጥራቱን ወደጎን ገፍቶት ለረጅም ዓመታት በቁጥር ላይ የተመሠረተ የመማር ማስተማር ሂደትን ሲከተል ቆይቷል፡፡ ይህ በመኾኑም አሁን ላይ በመምህርና በተማሪ መካከል ያለው የእውቀት ልዩነት ከቀድሞው ይልቅ እየጠበበ እንዲመጣ ያስቻለው ይመስላል፡፡ ይህ ችግር እየሰፋ በመሔዱ ደግሞ የፈተና ኩረጃና ስርቆት የተለመደ እየኾነ መጣ፡፡ በተማሪዎች ዘንድም የመማር፣ የመመራመር፣ ተግቶ የማንበብ ፍላጎት መቀነስ ከጊዜ ወደጊዜ አየለ፡፡ ይህም በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ የራሱ ተጽዕኖ ያለው ሲኾን በተለይም ፈጠራና ልህቀትን በማቀጨጭ በኩል ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡
መንግሥት ለትምህርት ጥራት የሰጠው ትኩረት
የትምህርት ጥራት ችግርን ከመሠረቱ ለመፍታት በሚል መንግሥት የጥገናዊ ለውጥ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ ያን ለማድረግም ከፖሊሲ ለውጥ አንስቶ ልዩ ልዩ ሥራዎችን በመተግበር ላይ ነው፡፡ ይህ ሲኾን ደግሞ ከመሠረቱ ተናግቶ የነበረውና በጽኑ መሠረት ላይ ያልቆመው የትምህርት ሥርዓታችን ልዩ ልዩ እክሎች ገጥመውታል፡፡ ለምሳሌ መንግሥት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከሠራው የሪፎርም ሥራ ውስጥ አንዱ የፈተና አስተዳደር ሥርዓትን በተለይም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ ፈተናን እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድህረ ምረቃ ፈተና ላይ ትኩረት ያደረገ ሥራው አንዱና ዋናው ነው፡፡ መንግሥት በዚህ ዙሪያ በወሰደው እርምጃ የትምህርት ዘርፉ ከፍተኛ ምስቅልቅልና መቃወሶች ገጥመውታል፡፡ በተለይም ያለፉትን ሁለትና ሦስት ዓመታት በርካታ ተማሪዎች ለፈተና ቢቀመጡም ውጤት ማምጣት የቻሉት በጣም ጥቂቶቹ ብቻ ነበሩ፡፡
ለምሳሌ ያለፉትን ሦስት ዓመታት ለ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ብሔራዊ ፈተና ከተቀመጡ ተማሪዎች ውስጥ ተሳክቶላቸው ከ50 በመቶ በላይ ውጤት አምጥተው ወደከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግባት የቻሉት 11.9 በመቶ ያህሉ ብቻ ነበሩ፡፡ ይህም ማለት በ2014 ዓ.ም 30,034 ተማሪ ወይም አጠቃላይ ከተፈተኑት ውስጥ 3.3 በመቶ፣ በ2015 ዓ.ም 27,267 ተማሪ ወይም አጠቃላይ ከተፈተኑት ውስጥ 3.2 በመቶ፣ በ2016 ዓ.ም 36,409 ተማሪ ወይም አጠቃላይ ከተፈተኑት ውስጥ 5.4 በመቶ ብቻ ናቸው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ባለፉት ሦስት ዓመታት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች መውደቃቸውን መገመት አያዳግትም፡፡
በሌላ በኩል እንደሚታወቀው አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት በቅድመ አንደኛ፣ አንደኛና መካከለኛ ደረጃዎች በ2015 ዓ.ም የትምህርት ዘመን፣ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ደግሞ በ2016 ዓ.ም ሙሉ ትግበራ ሲያደርግ ቆይቷል። በዚህ መሠረትም የሥርዓተ-ትምህርት ማዕቀፍና መርሃ ትምህርት እጥረቱ እንደተጠበቀ ኾኖ በትምህርት ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ ከቅድመ አንደኛ ደረጃ እስከ 8ኛ ክፍል ያለው የመማሪያና ማስተማሪያ መጻሕፍት በክልሎች በመርሃ ትምህርቱ መሠረት ተዘጋጅቶ ለማሰራጨት ተሞክሯል፡፡ ከዚህ አንጻር ባለፈው ዓመት ሕዳር 2016 ዓ.ም ላይ ትምህርት ሚኒስቴር በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት መሠረት የተዘጋጁ ከ10 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ መጻሕፍት ለክልሎች መከፋፈላቸውን ጠቁሞ ነበር፡፡
በወቅቱ እነዚህ መጽሐፍቶች 40 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላር ወጥቶባቸው እንደታተሙም ገልጿል። ኾኖም ትምህርት ሚኒስትር በዓመቱ መጀመሪያ ሩብ ዓመት ላይ ይህን ቢልም በሀገሪቱ ላይ ያለው የመማሪያ መጽሐፍት እጥረት ሊቀረፍ አልቻለም፡፡ ይህ በመኾኑም በተለይም አንዳንድ ክልሎች ከከተሞቻቸው በስተቀር በአዲሱ የሥርዓተ ትምህርት መጽሐፍት ሳያስተምሩ ዓመቱን ጨርሰው ወደሌላኛው የትምህርት ዘመን ተሸጋግረዋል፡፡ የትምህርት መሣሪያዎች ማምረቻ ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተውም ከ87 በመቶ በላይ የሚኾኑት ተማሪዎችና ትምህርት ቤቶች የተቀየሩት የመማሪያ መጽሐፍት አልደረሳቸውም፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ መንግሥት መጽሐፍቱን ማሰራጨት ባለመቻሉና መጽሐፍቱን ለማሳተም በገጠመው የገንዘብ እጥረት ሳቢያ እንደኾነ በተለያየ መንገድ ተገልጿል፡፡
የኾኖ ኾኖ በአጠቃላይ አሁን ላይ በመንግሥት በኩል ለትምህርት ምን ያህል ትኩረት ተሰጥቷል ሲባል ሌላ ጥያቄ የሚያስነሳ ኾኖ ይታያል፡፡ አሁን ላይ በሀገራችን ከአጠቃላይ ሕዝቡ ግማሽ የሚኾነው ሕዝብ የትምህርት ማኅበረሰቡ አካል ነው፡፡ ይህ በኾነበት ሁኔታ መንግሥት ለትምህርት የሰጠው ትኩረት ከበጀት ምደባ ጀምሮ እጅግ ዝቅተኛ የሚባል ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይህም ሲባል ለትምህርት ጥራት ሲባል መንግሥት እየወሰደ ባለው እርምጃ ብዙዎች ወደአልተፈለገ አቅጣጫ እንዲያመሩ ይመስላል፡፡ ቀደም ሲል የነበረው መንግሥት ከትምህርት ጥራት ይልቅ የተማረ ሰው ብዛት ላይ ትኩረት በማድረጉ ከፍ ሲል ያየናቸው ቀውሶች ሊከሰቱ ችለዋል፡፡ የአሁኑ መንግሥት ደግሞ ለትምህርት ጥራት ሲል እየሄደበት ባለው መንገድ አብዛኛው የትምህርት ማኅበረሰብ ተስፋ እየቆረጠ ያለ ይመስላል፡፡ አሁን ላይ ከ12ኛ ክፍል የወደቁ ተማሪዎች ወደ ስደትና በየጎጡ ወደሚገኙ ታጣቂ ኃይሎች በመጉረፍ ላይ እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች ያለው የሰላም መናጋት እየተባባሰ ሲመጣ ከመጀመሪያ ደረጃ እስከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ድረስ የትምህርቱ መሠረተ ልማቱ እክል ያጋጠመው ይመስላል፡፡ በርካታ ዩንቨርሲቲዎች በበጀት እጥረት ምክንያት የምገባ ፕሮግራማቸውን ለማቋረጥ በመንገታገት ላይ ይገኛሉ፡፡ በተለይም መንግሥት ባለፈው ዓመት ህዳር 2016 ዓ.ም ላይ በቀጣይ ሁለት ዓመታት በተልዕኮና ትኩረት መስካቸው የተለዩ 9 ዩኒቨርስቲዎችን ወደ ራስ ገዝ ደረጃ ለማሻገር እንደሚሠራ መግለጹ በተቋማቱ ላይ ራሱን የቻለ መደናገጥ ውስጥ ሳይፈጥርባቸው አልቀረም፡፡
በሌላ በኩል አሁን ላይ የተማሪዎች መውደቅና የፈተናው መብዛት በትምህርት ማኅበረሰቡ ላይ ከፍተኛ ተስፋ መቁረጥን ያስከተለ ይመስላል፡፡ ለምሳሌ አንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ስለትምሕርት ሲናገሩ ድግሪ አለመያዝ ምንም ማለት እንዳልኾነና ዓለም ላይ ትላልቅ ለውጦችን ያመጡ ሰዎች ተዓምራዊ ለውጡን ያመጡት ያለድግሪ ባላቸው የሀሳብ ምጥቀት መነሾ ብቻ መኾኑን አንስተዋል፡፡ ምንም እንኳን እርሳቸው ይኽን ያሉት ‹‹ትምህርት ጠቃሚ አይደለም›› የሚል መልዕክት ለማሻገር ባይኾንም፣ ጥቃቅን ጉዳዮች ሳይቀር የፖለቲካ መጠቀሚያ በሚኾኑበት በብዙዎች ዘንድ ግን አሉታዊ ተጽዕኖ በሚፈጥር መንገድ ጉዳዩ እንደተቀነቀነ አይካድም፡፡
የትምህርት ፖሊሲው በተማሪዎች ላይ የደቀነው ሥጋት
በተለይም በአዲሱ የትምህርት ፖሊሲ መሠረት የመውደቂያው እርከን መብዛቱ ማኅበረሰቡ በትምህርት ልማቱ ላይ ተስፋ እንዲያጣ ትልቅ ድርሻ አለው፡፡ ቀደም ባለው የትምህርት ሥርዓት ውስጥ የትምህርት ማኅበረሰቡ የፈተና ሥጋት የነበረው የ10ኛ እና የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ብቻ ነበር፡፡ አሁን ላይ ግን ሥጋቱ በእጥፍ ጨምሯል፡፡ ይኸውም አንድ ተማሪ ከስድስተኛ ክፍል ጀምሮ ዩኒቨርሲቲ እስኪገባ ድረስ ቢያንስ ሦስት ወሳኝ ፈተናዎች ይገጥሙታል፡፡ የመጀመሪያው የስድስተኛ ክፍል ሚኒስትሪ ፈተና ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ለምሳሌ ባሳለፍነው ዓመት 2016 ዓ.ም ላይ አማራ ክልልን ብቻ ማሳያ አድርገን ብናቀርበው ፈተናውን ከወሰዱት 132 ሺህ 225 የ6ኛ ክፍል ተማሪዎች 97 ሺህ 859 (74.1 በመቶ) ተማሪዎች 50% ውጤት አምጥተዋል። በተመሳሳይ ፈተናውን ከወሰዱት 150 ሺህ 928 የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች 84 ሺህ 522(56 በመቶ) ተማሪዎች 50% ውጤት አስመዝግበዋል። ከዚህ አንጻር ከስድስተኛ ክፍል ተማሪዎች 26 በመቶ ተማሪዎች ሲወድቁ ከስምንተኛ ክፍል ደግሞ 44 በመቶ የሚኾኑት መውደቃቸውን እንረዳለን፡፡
የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ከተማሪው ውጭ ማን ላይ ምን ተሠራ?
እንደ አጠቃላይ መንግሥት በትምህርት ጥራት ዙሪያ በሠራው ሥራ በተማሪዎች ላይ ከፖሊሲ ለውጡ ጀምሮ ከፍ ሲል እንደታየው የተለያዩ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ ከእነዚህ አንዱ ከላይ እንደተጠቀሰው ተማሪዎችን በየደረጃው መፈተን ማለትም 6ኛ ክፍል፣ 8ኛ ክፍል፣ 12ኛ ክፍል፣ ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና፣ የቅድመ ምረቃ ፈተና፣ ድህረ ምረቃ ወይም የመውጫ ፈተና አዘጋጅቶ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እየሠራ ይገኛል፡፡ ይህ ማለት በሂደቱ ላይ የሚነሳው ትችት እንዳለ ኾኖ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በተማሪው በኩል ምን ያህል እንደሄደ ማሳያ ነው፡፡
በሌላ በኩል ግን መምህሩንና በመማር ማስተማር ዙሪያ ያለውን ሙያተኛ ማኅበረሰብ ለማሻሻል እዚህ ግባ የሚባል ሥራ ሲያከናውን አይታይም፡፡ ይህም ማለት የዘርፉ አካላት በየዓመቱ ክረምት ላይ ከሚሰጣቸው ልዩ ልዩ የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና ውጭ ተጨባጭ ለውጥ በሚያመጣ መልክ በሙያተኞች ላይ ሲሠራ አይስተዋልም፡፡ በተለይም በመምህራን ዙሪያ መንግሥት ሲሠራ የሚስተዋለው የመምህራንን ኢኮኖሚ ለማሻሻል ሲጥር እንጂ የተሻለ ተማሪ ያፈሩ ዘንድ የማሻሻያ ዕውቀት ግንባታ ሲያደረግባቸው አይስተዋልም፡፡ ከዚህ አንፃር በተለይም በቀድሞው እንደ ደቡብ ክልል ያሉ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የትምህርት ማስረጃ የሌላቸው መምህራን ጨምሮ በርካታ የመንግሥት መዋቅር ውስጥ የሚሠሩ አካላት እንዳሉ የተለያዩ ወቅቶች ላይ ይፋ ሲደረግ ቆይቷል፡፡ ስለዚህ መንግሥት ስለትምህርት ጥራት ሲሠራ በተማሪዎች ዙሪያ እያደረገ ያለውን ጥብቅ ቁጥጥር መምህራንን ጨምሮ በትምህርት ሙያተኞች ዙሪያም ከፍ ያለ ሥራ ማከናወን ይጠበቅበታል፡፡
መደምደሚያ
የሀገራችን የትምህርት ሥርዓት ስብራት የጀመረው አሁን ሳይኾን ከረጅም ዓመታት በፊት መኾኑ ይታወቃል፡፡ ለዚህም ነው በየተቋማቱ ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ይዘው ሠራተኛ የኾኑ ዜጎች የበዙት፡፡ ይህ ችግር በትክክል ከተጤነ በስውር የሚካሄድ ሀገር የማፍረስ፣ ትውልድ የማምከን ጽዩፍ ተግባር ነው፡፡ ከዚህ አኳያ መንግሥት በመማር ማስተማሩ ጥላ ሥር የተወሸቀ የሐሰተኛ ትምህርት ማስረጃ ባለቤቶች ተምረናል ባይ ዜጎችን አበጥሮ መለየት ይጠበቅበታል፡፡ አሁን ባለንበት ኢኮኖሚያዊ ቀውስ፣ ፖለቲካዊ አለመረጋጋትና ማኅበራዊ ፍርሰት ዐቢይ መነሻው ላለፉት 30 እና 40 ዓመታት የተከልነው የሥርዓት ትምህርት ፖሊሲ ዝንፈት አተገባበርና ኢፍትሐዊ ፍሰት ነው ቢባል ስሕተት አይኾንም፡፡
ለትምህርት ጥራት እንቅፋት ከኾኑ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ኩረጃ መኾኑ ተደጋግሞ ሲነገር ነበር፡፡ ኩረጃን ለማስቀረት በተማሪው በኩል የተሄደበት ርቀት እንደተጠበቀ ኾኖ በቀረው የትምህርት ማኅበረሰብ በኩል ግን አንዳች በግልፅ የተከናወነ ተግባር አይታይም፡፡ ከዚህ አንፃር ለምሳሌ አንድ መምህር ተማሪዎች እንዲኮራረጁ ከፈቀደ ከፍ ያለ ቅጣት ሊጣልበት ይገባል፡፡ በተመሳሳይ በዚህ ድርጊት ላይ የተሳተፉ ማናቸውም አካለትም እንዲሁ ከባድ የሥነ ምግባር እርምጃ እንዲጠብቃቸው ቢሠራ መልካም ይኾናል፡፡ በእርግጥ በዚህ ዙሪያ ጥፋት የሠሩ አካላት ላይ እርምጃ ሲወሰድ በቅርቡ ታይቷል፡፡ ለምሳሌ ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ በመውጫ ፈተና ኩረጃና ሌሎች የፈተና ስነምግባር ጥሰት የፈጸሙ 114 ተፈታኞች ውጤት ሙሉ በሙሉ መሰረዙ አይዘነጋም፡፡
በአጠቃላይ በትምህርት መሠረተ ልማት ዙሪያ የሚከናወነው ተግባር በላቀና ፍትሐዊ በኾነ መልኩ መተግበር ይኖርበታል፡፡ ይህ ሲባል ግን የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እየተኬደበት ያለው መንገድ በእንከን የተሞላ ብቻ ነው ማለት አይደልም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የኢፌድሪ ትምህርት ሚኒስተር አሳየ ባለው የመልካም አስተዳደር አፈፃፀም ሂደት ዙሪያ ሽልማት አበርክቶለታል፡፡ የሽልማቱ በረከቱ ምንም እንኳን የሚጋነን ባይኾንም ‹‹ከዝንጀሮ ቆንጆ›› እንዲሉ ተቋሙ ከሌሎች አቻ ተቋማት አንፃር የተሸለ አፈፃፀም በማሳየቱ የሚገባው መኾኑ አያጠያይቅም፡፡ ይህ የአፈፃፀም ግምገማ ዝም ብሎ የተካሄደ ሳይኾን ከሌሎች 15 መስሪያ ቤቶች ጋር በ88 የመመዘኛ መስፈርቶች በማወዳደር የመጣ ውጤት መኾኑን በወቅቱ ሽልማቱን ያዘጋጀው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ገልፆ ነበር፡፡
ከዚህ አንፃር የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እንደቀድሞው የትምህርት ሥርዓት አሰስ ገሠሰሱን ከክፍል ክፍል ላለማሳለፍ ተጥሯል፡፡ ኾኖም ግን ችግሩን ለመቅረፍ በተማሪው በኩል በተሄደበት ርቀት ልክ በቀሪው የትምህርት ማኅበረሰብ ዙሪያም ሊኬድበት ይገባል፡፡ ይህ አሠራር የአፈፃፀም እንከኖችን በማስወገድ ከተሠራበት በቀጣይ ዓመታት የተሻለች ሀገር መገንባት ያስችል ይኾናል፡፡
ሰላም!
———-
ቅጽ 6 ግዮን ቁጥር 217 ጥቅምት 16 ቀን 2017 ዓ.ም
