እስራኤል፤ ወሳኙን የሆርሙዝ ወሽመጥ መተላለፊያን የሚቆጣጠረው የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የባሕር ኃይል አዛዥ የሆኑትን አሊሬዛ ታንጋሲሪን መግደሏን አስታወቀች።
የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር ኢዝራኤል ካትዝ፤ አዛዡ “በሽብር የቦምብ ጥቃቶች እና የሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥን በመዝጋት በቀጥታ ተጠያቂ” ናቸው በማለት ከስሰዋል።
ሚኒስትሩ ጨምረውም ከዋና አዛዡ ባሻገር በርካታ ሌሎች የኢራን “ከፍተኛ የባሕር ኃይል ዕዝ ባለሥልጣናት” በእስራኤል ጥቃት መገደላቸውን አመልክተዋል።
ግድያውን በተመለከተ እስራኤል እስካሁን ማረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ አልሰጠችም።
አሊሬዛ ታንግሲሪ የእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የባህር ኃይል አዛዥ ሆነው የተሾሙት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2018 ነበር።
ከዚያ በፊት እአአ ከ2010 ጀምሮ የአብዮታዊ ዘብ የባህር ኃይል ምክትል አዛዥ በመሆን አገልግለዋል።
እርሳቸው አንደሚገለገሉበት የሚገለጽ የኤክስ አካውንት እአአ ከመጋቢት 10 ጀምሮ የኢራን መገናኛ ብዙኃን በምንጭነት ይጠቀሙበት ነበር።
በዚህ የኤክስ ገጽ ላይ ስለ ሆርሙዝ ወሽመጥ ብዙ ጊዜ አጋርተዋል።
በዚህ ገጽ ላይ “ኢራን ላይ ጥቃት ከሚፈጽሙ ጋር ግንኙነት ያለው ማንኛውም መርከብ የማለፍ መብት የለውም” የሚል መልዕክት ሰፍሯል።
ታንግሲሪ የሚሰማቸውን በመናገር የሚታወቁ ወታደራዊ አዛዥ ሲሆኑ ቀደም ሲል በአሜሪካ እና በእስራኤል ላይ ብዙ መግለጫዎችን ሰጥተዋል።
እአአ በ2019 ኢራን ወደ ውጭ የምትልካቸው የነዳጅ ዘይት ምርቶች ከተስተጓጎሉ የሆርሙዝ ባህር ወሽመጥን እንደሚዘጉ ዝተው ነበር።
