የትምህርት ሚኒስቴር አመራሮችና ሠራተኞች የ2019 በጀት ዓመት የመጀመሪያውን ሩብ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ውይይት አካሂደዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት የትምህርት ዘርፉ ሊደርስበት የታሰበውን ግብና የ2019 በጀት ዓመት ቁልፍ የሥራ አቅጣጫዎችን አብራርተዋል።
ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ለአመራሮችና ለሠራተኞች ባስቀመጡት አቅጣጫ፣ በትምህርት ዘርፉ የተጀመሩትን የሪፎርም ሥራዎች በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በጽኑ መሠረት ላይ ለማቆም ከበፊቱ በበለጠ ትጋትና ቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
በተጨማሪም፣ የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎች ከአመራር ለውጥና ሽግግር ጋር ተያይዘው ሳይቋረጡ በተጠናከረ መልኩ መቀጠልና ዘላቂ መሠረት እንዲኖራቸው ማድረግ እንደ ሀገር ልንለማመደው የሚገባ አስፈላጊ የሥራ ባህል መሆኑንም ገልጸዋል።
አያይዘውም በትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታነት አዲስ የተሾሙ አመራሮችም ቀደም ሲልም በዘርፉ የመሪነት ኃላፊነት የነበራቸውና ዘርፉን በሚገባ የሚያውቁ በመሆናቸው፣ ያሉትን ተግዳሮቶች በመሻገርና አሁን ያሉትን እድሎች በአግባቡ በመጠቀም ውጤታማ ሥራ እንደሚያከናውኑ ያላቸውን እምነት ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በመጨረሻም፣ እንደ ሀገር ያሉንን ሀብትና ጸጋዎች በአግባቡ በመጠቀም ለመጪው ትውልድ የተሻለች ሀገር ለማስረከብ በሚደረገው ርብርብ፣ እያንዳንዱ የሚኒስቴሩ ሠራተኛና አመራር የተሰጠውን ኃላፊነት ከበፊቱ በበለጠ ቁርጠኝነት፣ በትጋትና በተነሳሽነት እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
(ጥቅምት 27/2019 ዓ.ም)
