በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር በዋሉት የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) አመራሮችና አባላት ላይ መርማሪ ፖሊስ የጠየቀውን የ14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በመመርመር፣ ፍርድ ቤቱ የ7 ቀን ፈቅዷል።
በዛሬው ዕለት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት የቀረቡት የኢሕአፓ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ይስሐቅ ወልዳይ፣ የፓርቲው አባል አቶ አበበ አካሉ እና ጠበቃ አበራ ንጉሥ ናቸው።
ቀደም ሲል በነበረው ችሎት ፍርድ ቤቱ የድምፅ ቅጂ ማስረጃዎችን ካዳመጠ በኋላ ለፖሊስ የ10 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቅዶ የነበረ ሲሆን፤ መርማሪ ፖሊስ በተሰጠው ጊዜ ውስጥ ያከናወናቸውን ተግባራት እና ቀሪ የምርመራ ሥራዎችን ለችሎቱ አስረድቷል።
የፖሊስ የቴክኒክ ማስረጃዎች፣ የሰው ምስክር ቃል፣ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ቅኝት ጥያቄ፣ እንዲሁም የ5 ባንኮች የገንዘብ እንቅስቃሴ መረጃዎች መሰብሰቡን አስረድቷል።
ተጠርጣሪዎቹ በአርባ ምንጭ ዙሪያና በአዲስ አበባ ከተማ ህገ-ወጥ አደረጃጀቶችን በመፍጠር፣ ከህወሓትና ከሌሎች «ፅንፈኛ ኃይሎች» ጋር በመቀናጀት ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ ተንቀሳቅሰዋል የሚሉ ናቸው።
በተጨማሪም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተከሰቱ ግጭቶች የሰው ሕይወት ማለፉንና የንብረት ውድመት መድረሱን አስረድቷል።
የምስክሮች ቃል መቀበል፣ የኤሌክትሮኒክስ ውጤቶችን ማምጣት፣ እና በጎፋ ዞን የተላከው ቡድን የሚያሰበስባቸውን የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች ማጠናቀቅ እንደሚቀሩት በመግለጽ ተጨማሪ 14 ቀን ጠይቆ ነበር።
የተጠርጣሪዎች ጠበቆች በበኩላቸው ፖሊስ ማስረጃ ለማቅረብ በቂ ጊዜ ነበረው፤ የምርመራ መዝገቡም ቀደም ሲል ከተገለጸው 300 ገጽ ወደ 50-60 ገጽ ዝቅ ማለቱ አዲስ ያገኘው ማስረጃ አለመኖሩን ያሳያል ሲሉ ተከራክረዋል።
በተጨማሪም ማስረጃዎቹ የመንግሥት ተቋማት ዘንድ ስለሆኑ ተጠርጣሪዎቹ በዋስ ቢወጡ የሚያጠፉት ማስረጃ የለም በማለት የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ጠይቀዋል።
ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ከመረመረ በኋላ ለዛሬ ነሐሴ 22 ቀን 2018 ዓ.ም ይዞት በነበረው ቀጠሮ ብይን ሰጥቷል።
በዚህም መሠረት ፍርድ ቤቱ ፖሊስ ከጠየቀው የ14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ውስጥ የ8 ቀን የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል።
ፍርድ ቤቱ ፖሊስ የምርመራ መዝገቡን አጠናቆ ለነሐሴ 28 ቀን 2018 ዓ.ም እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ማስተላለፉን ከጠበቃቸው ከአቶ ሰለሞን ገዛኸኝ ሰምተናል።
ሸገር 102.1
