በ2017 በጀት ዓመት ኢትዮጵያ ፓርኮቿን ከጎበኙ ቱሪስቶች 32 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘቷን የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን አስታውቋል።
በባለስልጣኑ የዱር እንስሳት አጠቃቀም ዴስክ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ወርቁ ለብስራት ሬዲዮ እንደተናገሩት በበጀት አመቱ 140 ሺህ ቱሪስቶች የጥበቃ ቦታዎችን ጎብኝተዋል።
ከእነዚህም መካከል 90 በመቶዎቹ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች እንደሆኑ የገለፁ ሲሆን የውጪ ሀገራት ቱሪስቶች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ማሽቆልቆሉን ተናግረዋል።
ይህም ሊሆን የቻለው በዋናነት በፀጥታ ችግር መሆኑን የገለፁት አቶ ዳንኤል በተለይም ከዚህ ቀደም ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው የውጪ ቱሪስቶች ይጎበኙ የነበሩት ብሄራዊ ፓርኮች ላይ አሉታዊ ጫናን ፈጥሯል ብለዋል።
በሌላ በኩል የፓርኮች መግቢያ የክፍያ ዋጋ አለመሻሻሉ የተሻለ ገቢ ማግኘት እንዳይቻል ጫናን እንደፈጠረ አቶ ዳንኤል ገልፀው ችግሩን ለመፍታት የክፍያ ተመን ዋጋዎች መስተካከል እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
እድሜው ከ12ት ዓመት በላይ የሆነ አንድ ኢትዮጵያዊ የጥበቃ ቦታዎችን ለመጎብኘት 20 ብር እንዲሁም አንድ የውጪ ዜጋ 90 ብር ብቻ እንዲከፍሉይገደዳሉ።
በእነዚህ ምክንያቶች ሳቢያ በበጀት ዓመቱ ከፓርኮች በተገኘው ገቢ የእቅዱን 50 በመቶ ብቻ መፈፀም እንደተቻለ ተጠቁሟል።
