የደቡብ አፍሪካው ግዙፍ ባንክ አብሳ ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት የቁጥጥር ማዕቀፎች እንዲላሉ ጠየቀ

Date:

የደቡብ አፍሪካው ግዙፍ የፋይናንስ ተቋም አብሳ ባንክ ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የባንክ ዘርፉን ይበልጥ ነፃ ካደረገ እና የቁጥጥር ማዕቀፎቹን ካላላላ ወደ ሀገሪቱ የፋይናንስ አገልግሎት ገበያ ለመግባት እቅድ እንዳለው አስታወቀ።

ባንኩ እስካሁን የተከናወኑት የባንክ ዘርፍ ሪፎርሞች የሚያበረታቱ ቢሆኑም፣ አሁንም ድረስ ጥብቅ ቁጥጥር በሚደረግበት ገበያ ውስጥ የረጅም ጊዜ የንግድ ቁርጠኝነት ለመውሰድ በቂ እንዳልሆኑ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እ.አ.አ በመጋቢት 2025 የውጭ ሀገር ተቋማት እና ዜጎች በአገር ውስጥ ባንኮች ላይ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚፈቅድ የባንክ ስራ አዋጅ ቁጥር 1360/2017 ማውጣቱ ይታወሳል።

ይሁን እንጂ ሕጉ የውጭ ተቋማት የባለቤትነት ድርሻ ከ40 በመቶ፣ የውጭ ዜጎች ደግሞ ከ49 በመቶ እንዳይበልጥ ገደብ ጥሏል።

ወደ ገበያው ለመግባት ፍላጎት ያላቸው እንደ አብሳ ያሉ ተቋማት ግን የዘርፉን ከፍተኛ የካፒታል ፍላጎትና የስጋት መጠን ግምት ውስጥ ሲያስገቡ፣ የተቀመጠው የባለቤትነት ገደብ “አዳጋች” መሆኑን ገልጸዋል።

የአብሳ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኬኒ ፊላ እንደተናገሩት “በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ በቅርበት እየተከታተልን ነው፤ የመጀመሪያዎቹ ጥቂት አስፈላጊ እርምጃዎች ተወስደዋል ብለን እናስባለን። ነገር ግን ከባንክ ጋር በተያያዘ የቁጥጥር አካባቢው ይበልጥ ክፍት እንዲሆን እንፈልጋለን” ብለዋል።

አክለውም የረጅም ጊዜ ውሳኔ ለማሳለፍ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ሲፈጠር ወደ ገበያው ለመግባት እንደሚወስኑ አረጋግጠዋል።

አብሳ ይህንን አስተያየት የሰጠው በኬንያ ገበያ ውስጥ አዳዲስ ባንኮችን በመግዛት ይበልጥ ለመስፋፋት በንቃት እየተንቀሳቀሰ ባለበት ወቅት ነው። ይህ የባንኮች ውህደትና ግዥ እንቅስቃሴ ሌሎች አህጉራዊ አበዳሪዎችንም እየሳበ ይገኛል።

ለአብነት ያህል የናይጄሪያው ዜኒት ባንክ ፓራማውንት ባንክን እየገዛ ሲሆን፣ የደቡብ አፍሪካው ኔድባንክ ደግሞ በኤን.ሲ.ቢ.ኤ ባንክ ውስጥ የ66 በመቶ ድርሻ ለመግዛት ተስማምቷል።

አብሳ በአሁኑ ወቅት በኬንያ የ4.29 ቢሊዮን ዶላር የሀብት መጠን ያለዉ ቅርንጫፍ እንዳለዉ ይነገራል። የኬንያን በአንጻራዊነት ክፍት የሆነ የቁጥጥር ሁኔታ በመጠቀም በምሥራቅ አፍሪካ ያለውን አሻራ ለማስፋት ማቀዱን ገልጿል።

በኬንያ የባንኮች ውህደትና ግዥ እንዲፋጠን ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ የካፒታል መስፈርት መጨመር ነው። እ.አ.አ የ2024 የንግድ ሕጎች ማሻሻያ አዋጅ ባንኮች በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ ዝቅተኛ የካፒታል መጠናቸውን ከ7.75 ሚሊዮን ዶላር ወደ 77.52 ሚሊዮን ዶላር እንዲያሳድጉ ደንግጓል።

ይህ ተለዋዋጭ ሁኔታ በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት የፋይናንስ ዘርፍ ላይ ትልልቅ ለውጦች እንደሚመጡ ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል። አብሳ ባንክም ይህንን ምቹ አጋጣሚ ለመጠቀም የቁጥጥር አካባቢው “ለዛ ምቹና አዎንታዊ” መሆን እንዳለበት አጽንኦት ሰጥቷል።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

እግዚአብሔር የሰጠኝን ተልዕኮዎች ፈጽሜያለሁ የአዛዥነት ዘመኔ እያበቃ ነው

የኡጋንዳ የመከላከያ ኃይሎች አዛዥ (CDF) ጄነራል ሙሁዚ ካይኔሩጋባ ከወታደራዊ...

አሐዱ ባንክ 1ነጥብ 07 ቢሊዮን ብር አተረፈ

ባንኩ በተጠናቀቀው የሂሳብ ዓመት ከ3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር...

በጋምቤላ ከምሽት አንድ ሰዓት በኋላ ነዋሪዎች እንዳይንቀሳቀሱ ተከለከለ

ከጋምቤላ ክልል ዋና ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኘው ጋምቤላ...

ፍልውሃ እና ሶደሬ!

ከሐዉለት አህመድ በቀደም ከብዙ ዓመታት በኋላ የፍልውሃ አገልግሎት ድርጅት ሔጄ...