‹‹ሀገራዊ ችግሮቻችን ሀገራዊ መፍትሔ ለመስጠት እንጥራለን››

Date:

‹‹ትልቅ ሀገር ይዘን ትንሽ አንኾንም›› ጳጉሜን

ዘላለም ጌታነህ

በቅርቡ በአዲስ አበባ የኅብረት ሥራ ኤጀንሲ አስፈላጊውን መሥፈርት አሟልቶ በገንዘብ ቁጠባ እና ብድር ዘርፍ የፋይናንስና ተዛማጅ የኾኑ አገልግሎቶችን እየሰጠ የሚገኘው ‹‹ጳጉሜን የገንዘብ ቁጠባና ብድር›› መሥራችና ባለራዕይ የዛሬው የመጽሔታችን እንግዳ ነው፡፡ ሥሙ ዘላለም ጌታነህ ይባላል፡፡ ስለማኅበሩ አመሠራረት፣ ዓላማ እና የአገልግሎት ስፋት የሚከተለውን ቆይታ አድርገናል፡፡ እነኾ!      

ግዮን፡- በቅድሚያ እንግዳችን ለመኾን ፍቃደኛ በመኾንህ እናመሰግናለን፡፡ ራስህን ለአንባቢያን ብታስተዋውቅልን?

ዘላለም፡- እኔም አመሠግናለሁ፡፡ ሥሜ ዘላለም ጌታነህ ይባላል፡፡ ከ‹‹ጳጉሜን የገንዘብ ቁጠባና ብድር›› መሥራቾች አንዱ ነኝ፡፡ የተቋሙን ራዕይ፣ ዓላማና ጥቅሞች ከመቅረጽ ጀምሮ የተሳተፍኩም ሲኾን፣ መሥራችና ባለራዕይ ኾኜ በማገልገል ላይ እገኛለሁ፡፡

ግዮን፡- ‹‹ጳጉሜን የገንዘብ ቁጠባና ብድር›› መቼ ተመሠረተ? ዓላማውስ ምን ነበር?

ዘላለም፡- ጳጉሜ የተመሠረተው ከሁለት ዓመት በላይ የፈጀ ሒደትን ካለፈ በኋላ ነው፡፡ ይፋዊ በኾነ መንገድ የተመሠረተው ደግሞ ታኅሣሥ 23 ቀን 2015 ዓ.ም ነው፡፡ የብድር እና ቁጠባ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ለመመሥረት ከብሔራዊ ባንክና ከአዲስ አበባ ሕብረት ሥራ ማኅበራት ኤጀንሲ ዕውቅናና ፈቃድ ለማግኘት ራሱን የቻለ ሂደት ይጠይቃል፡፡ ለመመሥረትም ቢያንስ 150 ሰው ሼር (ዕጣ) መግዛት ነበረበትና በዚህ ሒደትም 283 ወንዶች፣ 73 ሴቶችና በ47 ከ18 ዓመት በታች ልጆችን በድምሩ 329 መሥራች ይዘን ዕውቅና አግኝተናል፡፡ መሥርተን ሕጋዊ ፈቃድ ካገኘን ደግሞ አምስት ወር ኾኖናል፡፡ ሥራችንንም የቁጠባ አገልግሎቶችን በመሥራት ጀምረናል፡፡

ግዮን፡- ከ18 ዓመት በታች የኾኑ ልጆች በተቋማችሁ ውስጥ የመሥራችነት ተሳትፎ አላቸው?

ዘላለም፡- ልጆችን መሥራቾች ለማድረግ ያሰብነው ‹‹ጳጉሜ›› ማለት የኢትዮጵያ 13ኛ ወር በመኾኑ ነው፡፡ ጳጉሜ ከወሮች ሁሉ 6 ቀን ወይም 5 ቀን ብቻ የምታካትት ትንሽዋ ወር ናት፡፡ ነገር ግን ትንሽ ብትኾንም ዋጋ ተሰጥቷት ወር ኾና ትቆጠራለች፡፡ የብድርና ቁጠባው ዋና ዓላማም ብድርና ቁጣባን ማስተዋወቅ እና ባሕል ማድረግ ነው፡፡ ልጆች የዛሬ አበባዎች የነገ ፍሬዎች ናቸውና ያገኟትን ሳንቲም አምጥተው እኛ ጋር እንዲቆጥቡ ከማድረግ አንስቶ ከ18 ዓመት በላይ ከኾናቸው ደግሞ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ዕድል እንዲመቻችላቸው ለማድረግ በልዩ ሁኔታ እየሠራን ነው፡፡ ይኼ ቁጥር እስከ ሰኔ 30 ያለ ቁጥር ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ጨምሯል፡፡ ልጆች ደግሞ ከአበባ አየሆሽና ከቡሄ ጀምሮ የሚያገኙትን ገንዘብ በቁጠባ መልኩ እንዲያስቀምጡ የተሻለ ወለድ አዘጋጅተናል፡፡ ልጆችን ከማበረታታት አንፃር በየሥማቸው ደብተር አዘጋጅተን እስካሁን ቁጠባ ያደረጉ ልጆች 47 ደርሰዋል፡፡

ግዮን፡- ተቋሙ ሀገር አቀፍ ነው ወይስ አዲስ አበባ ላይ ብቻ ያተኮረ?

ዘላለም፡- ጳጉሜ የተመሠረተው በአዋጅ ቁጥር 985/2009 ዓ.ም በወጣው አዋጅ መሠረት ነው፡፡ በአዲስ አበባ ሕብረት ሥራ ማኅበር ኤጄንሲ ሥር የተመሠረተ ነው፡፡ ስለዚህ ለጊዜው አገልግሎት የሚሰጠው በአዲስ አበባ ብቻ ነው፡፡ በቀጣይ ደግሞ እንደፈጣሪ ፈቃድ ሀገር አቀፍ ለማድረግ እናስባለን፡፡

ግዮን፡- የጳጉሜ አባል ለመኾን የሚያስፈልጉት መሥፈርቶች ምንምን ናቸው?

ዘላለም፡- ጳጉሜ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ማኅበር አባል ለመኾን የሚያስፈልገው በመጀመሪያ በኅብረት ሥራ ማኅበር መርኅ የሚያምን መኾን አለበት፡፡ በቁጠባ ባሕልን ‹‹ባሕል›› አድርጎ ከእኛ ጋር መሥራት የሚፈልግ ሰው ሁሉ አባል መኾን ይችላል፡፡ ከዚህ ውጪ ደግሞ እያንዳንዱ አባል መኾን የሚፈልግ ሰው አክሲዮን መግዛት ይጠበቅበታል፡፡ በትንሹ ሦስት እጣ መግዛት ይጠበቅበታል፡፡ አንድ እጣ አንድ ሺህ ብር ነው፡፡ ይኼንን ክፍያ ሼር በመግዛት የአገልግሎት ክፍያ ወይም መመዝገቢያ አንድ ሺህ ብር መክፈል ይኖርበታል፡፡ ከዚያ ቁጠባ ለአዋቂዎች 500 ብር፣ ለልጆች መቶ ብር ለመክፈል ዝግጁ የኾነ ሁሉ ከእኛ ጋር አብሮ መሥራት ይችላል፡፡

ግዮን፡- ከጳጉሜ ብድር ለመውሰድ የሚያስችሉ መሥፈርቶች ምንምን ናቸው?

ዘላለም፡- ከጳጉሜ ብድር ለመውሰድ የመጀመሪያው መሥፈርት ሼር መግዛት ነው፡፡ ከዚያ በተከታታይ እስከ ስድስት ወር ቁጠባ መክፈል፡፡ ይኼ ደግሞ ሁለት ዓይነት ቁጠባ አለው፡፡ መደበኛ ቁጠባ የሚባለው ለልጆች መቶ ብር ለአዋቂዎች 500 ብር መቆጠብ ነው፡፡ በመሠረቱ ጳጉሜ ወደ 10 የሚጠጉ የቁጠባ ዘርፎች አመቻችቷል፡፡ እነዚያ ዘርፎች ከብድር በተጨማሪ አዳዲስ ዘርፎች ናቸው፡፡ የቁጠባ ዐይነቶች ሊለያዩ የሚችሉ ዘርፎች ናቸው፡፡ እንደ ድርጅቱ የተለያየ ባሕሪ ቢኖራቸውም የመጀመሪያው የቁጠባ ዓይነት መደበኛ ቁጠባ የሚባለው ሲኾን ለማኅበራዊ አገልግሎት፣ ለሕክምና፣ ለትምህርትና ለመሳሰሉት ነው፡፡ ሁለተኛው ቁጠባ ደግሞ የፍላጎት ቁጠባ ነው፡፡ ቆጣቢው በፈለገው ሰዓት ብር ሲያገኝ የሚያስቀምጥበት ሂደት ነው፡፡ ሦስተኛው ቁጠባ የልጆች ቁጠባ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ የንግድ ፈቃድ ላላቸውና ንግድ ማስፋፊያ እንዲሁም ለንግድ መጀመሪያ አገልግሎት የሚውል የቁጠባ ዓይነት ነው፡፡ ሌላው የቤት መግዣ ወይም የቤት ማደሻ ቁጠባ ነው፡፡ ይኼ የቤት ቁጠባ ይባላል፡፡ የመኪና ቁጠባ የሚባልም አለ፡፡ ይኼ ለቤት መኪናና ለንግድ መኪና አገልግሎት የሚውል የቁጠባ ዓይነት ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ የጊዜ ገደብ ቁጠባ የሚባል አለ፡፡ ወለድ አልባ ቁጠባ፣ የክብረ በዓላት ቁጠባ እና የቡድን ቁጠባ የሚባሉ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውጭ እኛን ለየት የሚያደርገን ሌላ ቦታ ላይ በብዛት የማይሠራበት የቡድን ቁጠባ የሚባለው መኖሩ ነው፡፡ ይኼ የሚያገለግለው በዋናነት ስፖርተኞችን ለመገደገፍ ታስቦ የተሠራ በመኾኑ ነው፡፡ የኢትዮጵያን እግር ኳስ በፋይናንስ የምንደግፍበት አማራጭ ነው፡፡ ለምሳሌ የቡና እና ጊዮርጊስን እንዲሁም አዲስ አበባ ያሉ ማናቸውም የስፖርት ክለብና በቡድን ለታቀፉ ደጋፊዎች አገልግሎት የሚሰጥ ዘርፍ ነው፡፡ ሌላው ብዙ ልተለመደው የቁጠባ ዓይነት ደግሞ ወለድ አልባ ቁጠባ ነው፡፡ ይኼ እንደሚታወቀው በዋናነት ባንኮች አካባቢ ያለ ሥራ ነው፡፡ የክብረ በዓላት ቁጠባም እንዲሁ ከሌሎች ይለየናል፡፡ ማንኛውም ሰው ለሚያከብረው በዓል የሚቆጥበው ነው፡፡ ለጥምቀት ብሎ አንድ ሰው መቆጠብ ከፈለገ ከመስከረም ጀምሮ ሊቆጥብ ይችላል፡፡ ሙስሊሙም እንዲሁ ለሂጅራ ቀድሞ የሚቆጥብበት አሠራር ነው፡፡

ግዮን፡- አንድ የተቋማችሁ አባል ገንዘብ በቆጠበ ቁጥር የሚያገኘው ነገር ምንድነው?

ዘላለም፡- ገንዘብ ማስቀመጥ የሚችሉት ባለ አክሲዮኖችና መሥራቾች ብቻ ናቸው፡፡ ነገር ግን አባል ያልኾኑም ሼር መግዛት ይችላሉ፡፡ በዚህም ዓመቱ መጨረሻ ላይ የትርፍ ክፍፍል መውሰድ ይችላሉ፡፡ በየዓመቱ የትርፍ ክፍፍል ይሠጣል፡፡ ከዚያ ውጪ እኛ ጋር ለሚያስቀምጠው ወለድ እናስባለን፡፡ ለምሳሌ ለልጆች 8% ወለድ እናስገባለን፡፡ ለአዋቂዎአች ደግሞ ከ7% ጀምሮ እናስቀምጣል፡፡ በዝግ አካውንት ገንዘብ የሚያስቀምጡ ሰዎች ካሉ ደግሞ ጠቀም ያለ ወለድ የሚሰጥበት ሒደት አለ፡፡

ግዮን፡- ጳጉሜ ከሌሎች የብድር ተቋማት ምን ትምህርት ወስዷል? ምንስ አዲስ ነገር ይዞ መጥቷል?

ዘላለም፡- ጳጉሜ ከሥሙም እንደምናየው መሸጋገሪያ ድልድይ ማለት ነው፡፡ ጳጉሜ አሮጌው አልፎ አዲሱን የሚያገናኝ ነው፡፡ እኛ ሀገራዊ የኾኑ ችግሮቻችን ሀገራዊ የኾነ መፍትሔ በመስጠት ለመፍታት እንጥራለን፡፡ እኛ ከብድርና ቁጠባ አገልግሎት በተጨማሪ የምክክር አገልግሎት አለን፡፡ አባላትም ብድር ከመውሰዳቸው በፊት የምክክር አገልግሎት ያካሂዳሉ፡፡ ለምሳሌ ንግድ ያላቸው ግለሰቦች ንግዳቸው ይታይና የሚያስፋፉበት ሁኔታ ላይ ምክክር ይካሄዳል፡፡ ከሌሎች የብድርና ቁጠባ ተቋማት ጳጉሜ በዚህ ይለያል፡፡ ከዚህ ውጭ ብድና ቁጠባዎች ራሳቸውን የቻለ አዋጅ አላቸው፡፡ 985/2009 የሚለው አዋጅ ሁሉንም የብድርና ቁጠባ ተቋማት የሚያስተዳድር ነው፡፡ በዚያ መሠረት ማኅበረሰቡን እናገለግላለን፡፡ እኛ ከሌሎቹ በተሻለ ቀልጣፋ የኾነ የብድር አገልግሎት እንሰጣለን፡፡ ለምሳሌ ብድር ለመስጠት ከ50 ሺህ እስከ 3 ሚሊዮን ብር እንሰጣለን ብለን አስበናል፡፡ ይህን ከአንድ ወር ጀምሮ ለቆጠቡ ሰዎች ብድር እንሰጣለን፡፡ ከዚህ ውጪ እርስ በእርስ እንዲዋዋሱ እናደርጋለን፡፡ የጳጉሜ አባል የኾነ ለጓደኛው መዋስ ይችላል፡፡ በአነስተኛ ደሞዝም ዋስትና እንሰጣለን፡፡ አራት ዓይነት የብድር አገልግሎት እንሰጣለን፡፡ የመጀመሪያው መደበኛ የማኅበራዊ አገልግሎት ብድር ነው፡፡ በጣም አስቸኳይ ለኾኑ ጉዳዮች ለሕክምና፣ ለኮንዶሚኒየም ክፍያ? ለድንገተኛ ድግስ ወዘተ የሚኾን የቆጠበውን አራት ዕጥፍ ብድር እንሰጣለን፡፡

ለምሳሌ 100 ሺህ ብር ለቆጠበ 400 ሺህ ብር እናበድራለን፡፡ የዚህ ጣሪያው እስከ 500 ሺህ ብር ድረስ ነው፡፡ ሁለተኛው የብድር ዓይነት ንግድ ፈቃድ የሚሰጥና እስከ 700 ሺህ ብር ድረስ የሚሰጥ ነው፡፡ ከ3 ወር እስከ 6 ወር ለቆጠቡ ሰዎች ንግድ ፈቃድ ላላቸውም እንሰጣለን፡፡ ሦስተኛው የብድር ዓይነት መኪና መግዛት ለሚፈልጉ ሰዎች የሚሠጥ ብድር ነው፡፡ ከእኛ ጋር አብረው የሚሰሩ መኪና አቅራቢ ድርጅቶች ጋር በመሥራት አገልግሎቱን እንሰጣለን፡፡ የመጨረሻው የብድር ዓይነት ለቤት መግዣ የሚውል እስከ 3 ሚሊዮን የሚደረግ ብድር ነው፡፡

ግዮን፡- ብድር ማግኘት የሚፈልግ ቆጣቢ የሚከተለው የአቆጣጠብ ስልት አለ?

ዘላለም፡- ብድር ለመውሰድ ራሱን የቻለ የብድር መመሪያ አለን፡፡ ራሱን የቻለ የብድር ክፍል አለ፡፡ እያንዳንዱ ብድር ፈላጊ፣ አባል በመኾን ወርሃዊ ቁጠባውን አከታትሎ መክፈል ይኖርበታል፡፡ ለምሳሌ መቶ ሺህ ብር የሚፈልግ ሰው በሦስት ወር ውስጥ ይኼን ገንዘብ መቆጠብ ይጠበቅበታል፡፡ ከዚህ በታች ቆጥቦ መስጠት የሚቻለው አስቸኳይ የኾነ የቤተሠብ ጉዳይ ካለበት፣ ለምሳሌ ሕክምና እና ሕይወቱን የሚያዘባ ነገር ካጋጠመው በኮሚቴ ታይቶ ይወሰናል፡፡ በዚህ ውስጥ ማኅበራዊና የግልግል ኮሚቴ የሚባል አለ፡፡ ተበዳሪው ያጋጠመውን ችግር አስረድቶ ብድር ይመቻችለታል፡፡ ይኼ የተተቋመውን የአባላቱንና የመሥራቾቹን ችግር ለመቅረፍ ስለኾነ አንዳንድ ጊዜ በኮሜቴ ታይቶ አንድ ወር የቆጠበ በአንድ ዓመት የሚመልስበት ሁኔታ እናመቻቻለን፡፡

ግዮን፤- ተቋማችሁ በአዲስ አበባ ምን ያህል ቅርንጫፍ አለው?

ዘላለም፡- ተቋማችን የተሟላ ሥራ ከጀመረ 6 ወር ኾኖታል፡፡ ሁለተኛ ቅርጫፍ ለመክፈት የቤት ኪራይና ውሎችን እየጨረስን ነው፡፡ ቁጥር 2 ብለን ስቴዲየም ጋር ልንከፍት ነው፡፡ በዋናነት ግን ማኅበራዊ ሚዲያውን በደንብ እየተጠቀምንበት ነው፡፡ ከቢሮ ውጭ ሁሉንም ነገር እያደረግን ነው፡፡ የራሳችን የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ አለን፡፡ ሰው ያለበት ቦታ ኾኖ በፈለገው አፕ (መተግበሪያ) ሞባይል ባንኪንግ እየተጠቀመ ያስገባል፡፡ ደረሰኝ እያስቆረጥን እንሰጣለን፡፡ ደንበኛው ቢሮ በመጣ ጊዜ ደረሰኝና አስፈላጊውን ነገር ጨርሶ ይሄዳል፡፡

ግዮን፡- ከምን ያህል ባንኮች ጋር ትሠራላችሁ?

ዘላለም፡- አሁን በጋራ የምንሠራው ከአራት ባንኮች ጋር ነው፡፡ በአሐዱ ባንክ፣ አዋሽ ባንክ፣ ወጋገን ባንክ እና ንግድ ባንክ አካውንቶች ከፍተን እየተጠቀምን ነው፡፡ በቀጣይ ደግሞ ለመቆጣጠርና ለማስተዳደር እንደተመቸን በየቀኑ ከ100 ብር ጀምሮ ሰው ሲያስገባ የራሱ የሆነ ተግዳሮቶች እንዳይኖረው ከእነዚህ ባንኮች ጋር ሥራ ጀምረናል፡፡ ለምሳሌ ከአሐዱ ባንክ ጋር ተፈራርመናል፡፡ ከአቅማችን በላይ ብድር ከተጠየቅን አሐዱ ባንክ እንዲያበድርልን ተስማምተናል፡፡ በተጨማሪ ደግሞ ከአዲስ አበባ ኅብረት ሥራ ዩኒየን ጋርም አብረን እንሠራለን፡፡ በርካታ የእኛ ዐይነት ተቋማትን ይዞ የሚሠራ በመኾኑ እኛም አክሲዮን ገዝተን የዚያ አባል ኾነናል፡፡ ይኼን ያደረግነው ተቋማችን የራሱ የኾነ የገቢ ምንጭ እንዲኖረው በማሰብ ነው፡፡ ስለዚህ ከአራት ባንኮች እና ከአንድ የኅብረት ሥራ ማኅበር ጋር በጋራ እየሠራን እንገኛለን ማለት ነው፡፡

ግዮን፡- ተቋማችሁ ምን ዓይነት የሥራ ዘርፍ ላይ የተሠማሩ ሰዎችን ያበረታታል?

ዘላለም፡- የአባሎቻችን ዘርፍ የተገደበ አይደለም፡፡ ማንኛውም ቆጥቦ መለወጥ የሚፈልግ ሰው አባል መኾንና ከእኛ ጋር መሥራት ይችላል፡፡ እኛ ትኩረት አድርገን የምንሠራው ከፍ ሲል እንዳልኩት የቡድን ቁጠባው ላይ ነው፡፡ በተጨማሪም ማኅበረሰባዊ ቁጠባ ላይ በስፋት እንሠራለን፡፡ ዓረብ ሀገር የሚኖሩ እህቶቻችን አባሎቻችን እንዲኾኑ እንሠራለን፡፡ እነርሱ ከዐረብ ሀገር ሲመለሱ ንግድ ማስጀመሪያ እንዲኾናቸው ለማድረግ በስፋት እየሠራን ነው፡፡ ቤት መግዛትም ከፈለጉ አሁኑኑ ቆጥበው በማንኛውም ጊዜ ያለ ወረፋ ያስተናግዳል፡፡ ነገር ግን መሥፈርቱን በትንሹ ያሟሉ መኾን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ትራንስፖርት ላይ የሚሠሩትን አካላት ታላሚ አድርገን እንሠራለን፡፡ ከኢትዮጵያ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማኅበር፣ ከታክስ ሹፌሮች ማኅበር እና መሰሎቻቸው ጋር ከሚያገኙት ላይ ትንሽ እየቆጠቡ አብረውን እንዲሠሩ እንጥራለን፡፡

ግዮን፡- በቅርቡ ስለጠራችሁት ጠቅላላ ጉባኤ የምትለው ነገር አለ?

ዘላለም፡- ለእሑድ ነሐሴ 21 ቀን 2015 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባኤ ጠርተናል፡፡ ጉባኤው ግዮን ሆቴል 3፡00 ሰዓት ጀምሮ የሚካሄድ ነው፡፡ ለጠቅላላ ጉባኤው የተጠሩት በመጀመሪያ መሥራች አባሎች ናቸው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ዘርፉን የሚደግፉ እና አብረውን የሚሠሩ ናቸው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ የመንግሥት አካላት ተገኝተው የ2015 ዓ.ም አፈፃፀማችን እንዲገመግሙ እንዲሁም የ2016 እቅዳችንን እንዲያዩ ተጋብዘዋል፡፡ ከዚህ ውጪ ሼር ሰርተፍኬት የሰጡትን ሼር እንሰጣለን፡፡ በዕለቱ ተቋሙ እዚህ እንዲደርስ ለረዱን ሁሉ የምሥጋና ፕሮግራምም አዘጋጅተናል፡፡

ግዮን፤- በመጨረሻ ማስተላለፍ የምትፈልገው መልዕክት ካለ እና ማመስገን የምትፈልገው አካል ካለ እድሉን ልስጥህ?

ዘላለም፡- መሪቃላችን ‹‹ትልቅ ሀገር ይዘን ትንሽ አንኾንም›› የሚል ነው፡፡ እኛ እያሰብን ያለነው በብድርና ቁጠባ ኢትዮጵያን ማሳደግ እና ማስጠራት ነው፡፡ ራዕያችን ከሚቀጥሉት ዐሥር ዓመታት በኋላ በ2025 የኢትዮጵያ ኩራት የኾነ የብድርና ቁጠባ ተቋም መኾን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኩራት ስንኾን ራሱን የቻለ ለማኅበረሰቡ የሚጠቅም ተቋም መኾን ነው፡፡ ሌትም ቀንም ሠርተን ማገልገል የምንችልበት እንዲኾን መሻት ነው፡፡ መቆጠብ እራሱን የቻለ ባሕልና ለውጥ አምጭ እንዲኾን እንሠራለን፡፡ ስለዚህ ‹‹ትልቅ ሀገር ይዘን ትንሽ አንሆንም›› ሰንል የ5 ሺህ ዘመን ታሪክ አለን ብለን ስለምናስብ ነው፡፡ ከኖኅ እስከ ብልፅግና ኢትዮጵያ 5 ሺህ ዘመን አላት፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር ናት፡፡ ታላላቅ ግዛት የነበራት ሀገር ነች ፤ ኢትዮጵያ፡፡ የሰው ዘር መገኛ ኾነን ከአንድ ድንጋይ ሕንፃ የሰራን ኾነን ሳለን አሁን ላይ ያንን ከፍታ ማሳየት ባለመቻላችን ነው ‹‹ትልቅ ሀገር ይዘን ትንሽ አንሆንም›› የሚል መሪቃል ይዘን የተነሳነው፡፡ ሰው 5 ሳንቲም ቆጥቦ ትልቅ ይኾናል፡፡ ሰው የሚፈለገውን ማድረግ የሚችለው በቁጠባ ባሕል ነው፡፡ በፋይናንስ ዘርፍ የኢትዮጵያ ኩራት እንኾናለን ብለን ነው የምናስበው፡፡

ሌላው መልዕክቴ በመጪው አዲስ ዓመት በርካታ የምንሠራቸው ሥራዎች ይኖራሉ፡፡ ሎጎአችን ከአደይ አበባ የመጣ ነው፡፡ ያ ማለት ልምላሜና ተስፋን የሚያሳይ ነው፡፡ መደቡ ቢጫ መኾኑ የፍቅርና የተስፋ ምልክት ነው፡፡ እኛ ሀገራችን ሰላም እንድትሆን እንመኛለን፡፡ ኢትዮጵያ አደይ አበባ ብቸኛ አብቃይ ሀገር ናት፡፡ ያ ደግሞ ከጳጉሜ ጀምሮ አዲስ ዓመት መውጫ ነውና እኛም አዳዲስ ነገሮች የምናመጣበት፣ ለሀገራችን ተስፋ የምንኾንበት ነው፡፡

ጳጉሜን ከምሥረታው ጀምሮ እዚህ እስኪደርስ አብረውኝ የደከሙ ሌት ተቀን የለፉ፣ ከብዙዎቹ በጥቂቱ አማረ መንግሥቱ፣ መኮንን ኤፍሬም፣ ቢንያም ታደሠ፣ ጥሩየ ከበደ፣ ጥላሁን ግዛው፣ የሺጥላ አማረ፣ ታምራት ደጀኔ፣ ኢ/ር ዘውዱ፣ ቁምነገር እና ዐቢይ አሠፋን ሳላመሠግን ባልፍ ንፋግነት ስለሚሆን ከልብ አመሠግናለሁ ፤ ክበሩልኝ። ሌሎችንም ሥማችሁን ሳልጠቅስ የዘነጋኋችሁ ካላችሁ ምሥጋናዬ ይድረሳችሁ፡፡ በመጨረሻም ከምሥረታው አንስቶ ዛሬ ድረስ ቢሮ በመሥጠት፣ በእውቀትም፣ በሞራልም ጭምር የነበረውን ሒደት ከመጀመሪያ ራዕዬን፣ ሐሳቤን እና ዓላማዬን ተረድተው ‹‹በርታ፣ ሁሌም ከጎንህ ነኝ›› ብለው የጳጉሜን የጀርባ አጥንት ለኾኑኝ አቶ ሙሉጌታ መኮንን መለሠ እና ጠቅላላ ሰራተኞቻቸውን አመስግኑልኝ። እድሜ ከጤና ጋር ይስጥልኝ ክፋ አይንካችሁ። ግዮን፡- ስለነበረን ቆይታ በአንባቢያን ሥም እናመሰግናለን፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የአርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ስርዓተ ቀብር ተፈጸመ

የአርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ስርዓተ ቀብር በመንበረ ጸባኦት ቅድስት...

በእስር ላይ የሚገኙት መምህርት መስከረም ዓይናቸው በጽኑ መታመሙን ጠበቃቸው ገለጹ

ከሁለት ዓመት በላይ በእስር ላይ የሚገኙት መምህርት መስከረም አበራ...

ንግድ ባንክ “ስታርፔይ” የተሰኘ አዲስ መተግበሪያ ይፋ አደረገ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል ባንክ ሥርዓቱን ይበልጥ ዘመናዊና ቀልጣፋ...

በኢትዮጵያ በካንሰር ከሚያዙ ሕፃናት መካከል 75 በመቶ የሚሆኑት ህክምና አያገኙም

በኢትዮጵያ በየዓመቱ በካንሰር ከሚጠቁ ከ6 ሺህ እስከ 8 ሺህ...