ጠበቃ መሠረት ሥዩም
ግዮን መጽሔት :- ባለፈው ከማኩታ የሕግ አገልግሎት መሥራችና ማኔጂንግ ፓርትነር ከኾነችው መሠረት ሥዩም ጋር በልጅነት ሕይወቷና ወደ ጥብቅና ሙያ ለመግባት ምክንያት በኾኗት ጉዳዮች ዙርያ እንዲሁም በዘርፉ እስካሁን የተጓዘችባቸውን መንገዶች በተመለከተ ሰፋ ያለ ቆይታ ማድረጋችን ይታወሳል፡፡ በዚህኛዉ ክፍል ደግሞ፣ ስለሕግ ተቋሟ አሁናዊ እንቅስቃሴና ቀጣይ መዳረሻ ተከታዩን ቆይታ አድርገናል፡፡ መልካም ንባብ!
ግዮን፡- በቅርቡ የኢትዮጵያ ጠበቆች ማኅበር ፕሬዝዳንት ምርጫ ሲከናወን ተወዳዳሪ ነበርሽ፡፡ ሒደቱ ምን ይመስል ነበር?
መሠረት፡- ጥሩ የምርጫ ተሞክሮ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ የምርጫ ሂደትን በጤናማ ሁኔታ ማከናወን የሚበረታታ ጉዳይ ነው፡፡ ተመራጮች ራሳቸውን ለማስተዋወቅ የሄዱበት መንገድ ብዙ ትምህርት የሚወሰድበት ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
ግዮን፡- የጠበቆች ማኅበርን በተመለከተ ብትመረጪ ያዘጋጀሻቸው ዕቅዶች ነበሩ?
መሠረት፡- ምላሼ አዎ ነው፡፡ በመሠረታዊነት አራት ነጥቦች ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ ጠበቃ ከፍርድ ቤት የዘለለ ጠንካራ ሚና አለው፡፡ በመሆኑም ይህንን ሚና ለመወጣት የሚያስችል የሙያዊ እውቀት እና ልምድ ግንባታ ወሳኝ በመሆኑ የሙያ ማኅበረሰቡን በዕውቀት ለማበልፀግ የሚያስችል አሰራር መዘርጋት፤
- የሙያ ልማድን ማጎልበት የሚያስችል አሰራር መዘርጋት፤
- በቴክኖሎጅ የተደገፈ አሰራርን ለማስረፅ እንዲቻል ባለሙያውን በቴክኖሎጅ ማበልፀግ፤
- በሙያያዊ ሥነምግባር የታነፀ ባለሙያ እና ጠንካራ የሙያ ማኅበረሰብ በማፍራት የሙያውን ተፈላጊነት መጨመር፤
- ከሕግ ምሁራን እና የሕግ ትምህርት ቤቶች ጋር በመተሳሰር ከትምህርት ቤት ጀምሮ ብቁ የሆኑ ባለሙያዎችን ማፍራት፤
- በዋናነት ባለሙያው በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከሀገር ውጭም ሙያውን ማበርከት የሚችል ብቁ እንዲሆን መሥራት ከእቅዶቼ መካከል ነበሩ፡፡
ግዮን፡- የፍትሕ ሚኒስቴር ከቻይና መንግሥት ጋር በመተባበር በኤአይ ቴክኖሎጂ ዙሪያ እየሠራ ያለው ምንድን ነው?
መሠረት፡- ዘመኑ በጣም የፍጥነትና የሩጫ በመኾኑ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የታገዘ አገልገሎት መሥጠት ሥራን ውጤታማ ያደርጋል፡፡ ይህን ማድረግ ለደንበኛውም ምቹ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ አገልገሎት ለማግኘት አራት ሰዓት የሚያስፈለግ ከኾነ በኤአይ በመታገዝ ደንበኛው ሳይጉላላ በደቂቃዎች ውስጥ ጉዳዩን ፈጽሞ ይሄዳል፤ ግን ደግሞ በጣም ጥንቃቄ ይፈልጋል፡፡ ቀጠሮ ለማግኘት፣ ከባለሙያዎች ጋር በቀላሉ ለመገናኘትና ሌሎች ቁልፍ መረጃዎችን ለማግኘት በግልጽነትና በተጠያቂነት ለመሥራት ቴክኖሎጂው ያስፈልጋል፡፡ ይህ ደግሞ የአገልግሎት አሰጣጡን ከማሳለጡ በላይ ደንበኛው በአንድ ቦታ ኾኖ አስፈላጊውን አገልገሎት አግኝቶ እንዲመለስ ያስችለዋል፡፡ ትኩረት ሰጥተው ሌሎችም አካላት እየሰሩበት ነው፡፡
ግዮን፡- አንቺ በዚህ ዙሪያ ያበረከትሽው ነገር ምንድን ናቸው?
መሠረት፡- ከቻይናው ካምፓኒ ጋር በጋራ ሰርተን ነው ያበለጸግነው፡፡ ወደ አገልግሎት ማስገባት የእኛ ሥራ ነው፡፡ አጠቃላይ ሥራው የሚከናወነውም ከእኛ ተቋም ጋር በጋራ ነው፡፡
ግዮን፡- ከመቶ በላይ በሚኾኑ አገራት በተውጣጡ ባለሙያዎች የተመሰረተው ማኅበር አባል ለመሆን ሥራውን እንዴት ተወጣሽው?
መሠረት፡- በምሥረታ ሂደቱ ላይ ተነሳሽነቱን የወሰደው ሚስተር ሻንት ይባላል፡፡ የማኅበር ምሥረታውን ሀሳብ አንስቶ በጣም ትልቅ ሥራ የሠራው ይህ ግለሰብ ነው፡፡ ኑሮው ካሊፎርኒያ ሲኾን መነሻው ቻይና ቤጂንግ ነው፡፡ በጣም በርካታ ሰዎችን ያውቃል፡፡
ትልቅ ዕውቀት ያለው ሰው ሲኾን በርካታ ዩኒቨርሲቲዎችም አስተምሯል፡፡ ይህ ሰው እኛን በመጋበዝ ከኢትዮጵያና ከሌሎች ሃገራትም የሙከራ ናሙናዎች በመሰብሰብ እኔም የተሣተፍኩበት አራት መቶ አባላት ያለው ማኅበርን ለመመሥረት በቅተናል፡፡
ግዮን፡ የተቋሙ ሥም ምንድንነው? ምን ምን ሥራዎችን ይሠራል?
መሠረት፡- ኤል ዲ ሌጋል አሊያንስ (LD Legal Alliance) የሚባል ነው፡፡ ሥልጠናዎችና ትምህርትም ይሰጣል፣ አሁን ደግሞ የግልግል ተቋም ሆንግ ኮንግ ላይ ተመዘግቦ ሥልጠናዎቹ በኦንላይንም በአካልም ይሰጣሉ፡፡
ግዮን፡- የዚህ ማህበር የወደፊት የሥራ ዕቅድ ምንድን ነው?
መሠረት፡- በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደቻምበር ያገለግላል፡፡ ተቋሙ የባለሙያዎች ስብስብ ነው፡፡ ይህ ተቋም አማራጭ የግልግል ተቋም የሚባል ማዕከል እያቋቋመ ነው፡፡ ለማቋቋሚያ የሚያስፈልገው ማንኛውም ሰነድ ተፈርሞ አልቋል፡፡ ስለዚህ አገልግሎት ሲጀምር በርካታ የሚዳኙ ተቋማት ይኖራሉ፡፡ በመኾኑም የአጋርነቱ አባላት በዳኝነት፣ በአስፈጻሚነት፣ በአማካሪነትና መሰል ሂደቶች የመሳተፍ እድሎች ይኖራቸዋል፡፡ በዚህም የዕውቀት ልውውጦች፣ ሴሚናሮች፣ ዓመታዊ ስበሰባዎችና መሰል ነገሮችም ተጠናክረው ይቀጥላሉ፡፡ ይህ ኹነት ደግሞ ዘርፉን በከፍተኛ ሁኔታ በሁሉ ነገር ያደገ እንዲኾን ያደርገዋል፡፡
ግዮን፡- ይኽ ተቋም በሀገሮች መካከል በሚፈጠር አለመግባባትና ፀብ ዙሪያ ይሠራል?
መሠረት፡- አሁን ባለው ሁኔታ እንዲህ ያሉ ጉዳዮች ላይ አይገባም፡፡ በተቋማት እና በግለሰቦች መካከል የሚፈጠሩ ችግሮችን በመፍታት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ነገር ግን እየተቋቋመ ያለው የፍትሕ ማዕከላችን ሲያልቅ እንዲህ ዓይነት ጉዳዮችንም የሚመለከት ይኾናል፡፡
ግዮን፡- ተቋማችሁ ወደፊት ሀገራትንም አባል ያደርጋል?
መሠረት፡- ተቋሙ ከተመሠረተ በኋላ በተለያየ ሀገራት ላይ ቅርንጫፍ ሊከፍት ይችላል፡፡ በዚህም ለመዳኘት ፍላጎት ያላቸው አካላትን የመዳኘት ሥራ ይሠራል፡፡
ግዮን፡-ሁሉም መንግሥታዊ ይሁን ግላዊ ተቋማት የግድ የሕግ ባለሙያ ወይም የሕግ አማካሪ ያስፈልጋቸዋል? ብዙ ጊዜ በሕግ የማይቋቋሙ ተቋማት ላይ ችግሮች እንመለከታለን?!
መሠረት፡- በማስፈለግ ደረጃ ማናቸው የመንግስትም ይሁን የግል ተቋማት የህግ ባለሙያ እገዛ ያስፈልጋቸዋል በአስገዳጅ ሁኔታ ህግ በጠበቃ ታግዞ መቅረብን የሚያስገድድ ህግ የለንም በአንዳንድ ሀገሮች ግን የተለያዩ ጉዳዮች አስገዳጅ የሚሆንበት ሀገር አለ ፡፡ ለምሳሌ አሜሪካን ሀገር ቤት በመግዛት እና በመሸጥ ሂደት ውስጥ የጠበቃ መኖር አስገዳጅ የሆነበት ሁኔታ አለ፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥም ችግሮች ከመጡ በኋላ ብቻ ሳይሆን ችግሮች እንዳይፈጠሩ በባለሙያ መታገዝ በደንብ መለመድ አስፈላጊ ነው፡፡ በሂደትም በአንዳንድ አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች አስገዳጅ እየሆነ የሚሄድበት ሂደት መፈጠሩ አይቀርም የጠበቆች ማህበር በቅርብ የተቋቋመ እንደመሆኑ እያደገ እና እየጠነከረ የሚሄድ ማህበር ነው፡ የማህበሩ መጠንከር የሙያውን ተፈላጊነት ከፍ ያደርገዋል፡፡
ግዮን፡- በGMN ቴሌቭዥን ላይ የሚሠራጭ ሕግን የተመለከተ ፕሮግራምም ነበረሽ? ጣቢያውንስ ለምን መረጥሽው?
መሠረት፡- ይህን የቴሌቭዥን ጣቢያ የመረጥኩበት ምክንያት በመላው ዓለም ስለሚታይ ነው፡፡ ውጭ ሀገር ያሉ ሰዎችም በሚመቻቸው ሰዓት የሚተላለፍ ነው፡፡ በዚህ ፕሮግራም ላይ ከስድስት ዓመት በላይ አገልግያለሁ፡፡ ዓላማዬም በትውውቅና በመተማመን ሕግን ሳያውቁ ጥቅማቸውን ሊያጡ ለሚችሉ ሰዎች ግንዛቤ መፍጠር ነው፡፡ እኔ በሥራ ሕይወቴ ሁሉንም ነገር በገንዘብ መሥራት አለብኝ ብዬ አላስብም፡፡ ለማኅበረሰቡ አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለብኝ ይሰማኛል፡፡ የትም ጋር ብትደርስ እንጀራ በወርቅ አትበላም፣ እንጀራ በወጥ ነው የምትበላው፡፡ አቀራረቡ ይለያያል እንጂ፡፡ ስለዚህ ሕብረተሰቡን በነጻ ለማገልገልና ስለ ሕግ ያለውን ግንዛቤና ንቃተ ሕሊና ለማሳደግ በሚል ነው የሠራሁት፡፡ ደግሞም ብዙ ሰው ተጠቅሞበታል፡፡ ይህ ፕሮግራም በኮቪድ ወቅት ትንሽ ክፍተት ነበረው ፤ አሁን ግን ዳግም ወደ አየር ተመልሷል፡፡
ግዮን፡- ፕሮግራሙ መቼና በምን ሰዓት ይተላለፋል?
መሠረት፡- ዘወትር ቅዳሜ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ነው የሚተላለፈው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዳዲስ ሕጎች ላይ ተመሥርቶ ከዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች (በተለይም ከዳያስፖራዎች) ጋር በተያያዘ ነው እየሠራ የሚገኘው፡፡ ዲያስፖራው ወደ ሀገር ቤት እንዲገባ እንፈልጋለን፡፡
እዚህ ያለው ሕብረተሰብም ስለሕግ እውቀት እንዲኖረው እንፈልጋለን፡፡ ስለዚህ እውቀት መፍጠሩ ላይ ትኩረት አድርገን በመሠራት ላይ እንገኛለን፡፡ በዚህም ብዙ ሰው ቢሰማው ተጠቃሚ ይኾናል ብዬ አስባለሁ፡፡
ግዮን፡- ፍትሕን ከመንፈሳዊና ዓለማዊ ብያኔ ጋር አያይዘሽ የያዝሽውን መረዳት ንገሪን እስቲ?
መሠረት፡- ፍትሕ ማለት እኩልነት ብቻ ሳይኾን ተጠያቂነትም ነው፡፡ ፍትሕ ውስብሰብ ጽንሰ ሐሳብ ነው፡፡ ፖለቲካዊና ተፈጥሮአዊ ጽንሰ ሐሳቦችን በውስጡ ይዟል፡፡ ጠቅለል ሲደረግ ግን፣ ፍትሕ አንድ ሰው ተገቢን ነገር እንዲያገኝ የሚያደርግ፣ ተጠያቂነትን የሚያሰፍን፣ የሀብት ክፍፍልን በፍትሓዊነት የሚያረጋግጥ፣ በሰዎች መካከል የአኗኗርን መስመር ሚዛናዊ የሚያደርግ ትልቅ ጽንሠ ሀሳብ ነው ማለት ይቻላል፡፡
በሌላ በኩል ፍትሕን በመንፈሳዊ ዓይናችን ስንመለከተው ብዙ ጊዜ ‹‹እንዲደረግብህ የማትፈልገውን በሌላው ላይ አታድርግ›› የሚለውን መንፈሳዊ ሐረግ የሚወክል ነው፡፡
ያለአግባብ ላለማጣት ያለሞገደኝነት ማግኘት ያስፈልጋል፡፡ ‹‹አትስረቅ፣ አትዋሽ፣ የሌላውን አትመኝ›› የሚሉትን መንፈሳዊ ሕግጋት የሚያስጠብቅ ነው – ፍትሕ ማለት፡፡ በዚህ ሕግ ሁሉም ኃይማኖቶች ይመራሉ፤ ይስማሙበታል፡፡
ግዮን፡- የኢትዮጵያ የፍትሕ ሥርዓት ምን ደረጃ ደርሶ ማየት ትፈልጊያለሽ?
መሠረት፡- በሀገራችን ተገልጋይ ሕግ አክብሮ፣ የሕግ የበላይነትን ድንጋጌዎችም አምኖ ሲኖር ብመለከት ደስ ይለኛል፡፡ ‹‹በሕግ አምላክ›› ሲባል ለግድያ የወለወለውንና የደገነውን መሣሪያ ዘቅዝቆ ሲመለስ ባይ እጅግ ደስ ይለኛል፡፡
በዚህ በዘመናዊ ዓለምና አስተሳሰብ ደግሞ አዕምሮአዊ የአስተሳሰብ ብቃቱ በሕግ አክባሪነት ታንጾ ባይ ይበልጡኑ ደስ ይለኛል፡፡ በተመሳሳይ ሕግ አስፈጻሚው አካልም በሀቅ፣ በእውቀትና በልምድ ላይ የተመሠረተ ፍትሕ ሲሰጥ ማየት ያስደስተኛል፡፡
ሕግ አስከባሪው ሕግን ሲያስከብር ሕግን መሠረት ባደረገ አግባብ እንዲኾን እፈልጋለሁ፡፡ ሕጎቻችንም ደግሞ እንደ ሀገር ዜጋው የሚያምነባቸው ደጋግሞ የማይጥሳቸው የተረጋጋ ሕግ ያለን እንድንኾንና በሕግ የፀናች፣ የሕግ የበላይነትም የሚከበርባት አልፎም ሌሎች ሀገሮች በምሳሌነት የሚያነሷት ሀገር እንድትኖረን እመኛለሁ፡፡ አሜሪካ፣ ሲንጋፖር፣ ወዘተ፣… ተብሎ እንደሚጠራው ሁሉ ኢትዮጵያም በዚህ ምሳሌነት የምትጠቀስ እንድትኾን እመኛለሁ፡፡ በእርግጥ ኢትዮጵያ ጠንካራ የሕግ አገር ናት፡፡ ጠንካራ ሕጎች አሏት፡፡ አተገባበሩም በደንብ እየተፈተሸ ያድጋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ነገር ግን ገና ብዙ መስተካከል ያለባቸው ነገሮች አሉ፡፡ እነሱ ውጤት ላይ ደርሰው ማየት ውስጤ ይናፍቃል፡፡
ግዮን፡- አንዳንድ ባለሙያዎች ፍትሕ የዳኞች ውሳኔ ተግባር ብቻ ሳይኾን የአቃቢ ሕግና የፖሊስ፣ እንዲሁም የዘርፉ ተዋናዮችም ጥምረት ውጤት ነው ይላሉ፤ አንቺ በዚህ ዙሪያ ምን ትያለሽ?
መሠረት፡-እኔም የምለው እንዲሁ ነው እንደውም በፍትሕ መስፈን ወይም መጓደል ዙሪያ ከተጠቀሱት አካላት በላይ ማኅብረሰብና የአስተዳደር አካላትም ይመለከታቸዋል ባይ ነኝ፡፡ የአስተዳደር መሥሪያ ቤቶች ተገልጋዮችን በእኩል ደረጃ በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በፍጥነት ማስተናገድ አለባቸው፡፡ የማኅበረሰቡ አዕምሮ ውስጥ የሕግ መከበር ትልቅ ቦታ ሊኖረው ይገባል፡፡ ይኽ ሲኾን ዐቃቤ ሕጉም ክስ ሲመሠርት እውነት ላይ ተመሥርቶ ይኾናል፡፡ ፖሊስም ምርመራውን ሲያካሂድ ማስረጃ ላይ ተመሥርቶ ይኾናል፡፡ ጠበቃውም ሲከራከር ሕጉን አውቆ በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመሥርቶ በግልጽነት ይኾናል፡፡ እነዚህ ሒደቶች ከተሟሉ ዳኛው እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ሲፈጠሩለት ለሥራው በእጅጉ ስለሚያግዘው በግልፅነትና በተቀላጠፈ አሠራር የተዋጣለት ፍርድ እየፈረደ የሕግ የበላይነትን ያረጋግጣል፡፡ ዳኛውን ማገዝ፣ ፍርድ ቤቱን ማገዝ ተገቢ ነው፡፡
ግዮን፡- ኢትዮጵያ እንደሀገር የፍትሕ ሥርዓታቸው ካደጉ ሀገራት ምን ትማር ትያለሽ?
መሠረት፡- በዚህ ዙሪያ ማለት የምችለው የሀገራችን የፍትሕ ሥርዓት የዳኞች ነፃነትን መጠበቅና የዘመኑ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም አለብን ነው፡፡ ግልጽነት ላይ ትኩረት መሥጠት ያስፈልጋል፡፡
በማኅበረሰቡና በፍትሕ አካላት መካከል መከባበርና መተማመን የሚፈጥርን የሥርዓት ግንባታ ማጎልበት እንዲሁም የሕግ አካላትን በዕውቀት ማላቅና በቴክኖሎጂ ማሳደግ በተጨማሪም የዘርፉን ሙያተኞች በሥነ ምግባር ማነፅ ይጠበቃል፡፡
ማስታወሻ- ውድ አንባቢያን፣ ከጠበቃ መሠረት ሥዩም ጋር ያደረግነው ቆይታ በዚህ አልተጠናቀቀም፡፡ ቀሪ የሙያና የሕይወቷን እንቅስቃሴዎችና ተሞክሮዎች በተመለከተ ያደረግነውን ቆይታ ይዘን የምንመለስ ይኾናል፡፡
