ሀገር ‹‹የሚመራው›› ብልጽግና በበርካታ አያዎዎች (Paradoxes) ተሞልቶ መንገዳገዱን እንደ አመራር ጥበብ ወስዶ ማዝገሙን አላቆመም፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ በመንግሥት ሠዋራ ፍላጎት፣ በቀንደኛ ባለሥልጣናቱም ነውረኛ አካሔድ በሀገር ላይ እየደረሰ ያለውን ያገጠጠ አውነት ኹሉ ውጫዊ ለማድረግ የሚሄድበት ርቀት፣ ከቀድሞ ኢሕአዴግ አባላቱን እና መዋቅሩን እንጂ ችግሮችን የመገምገም በጎ ልማዱን ላለመውረሱ ማሳያ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ከአንድ ሳምንት በፊት ተካሒዶ በነበረው የዐዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ም/ቤት ስብሰባ የተስተጋባውን እጅግ አስደንጋጭ ድምጽ ተከትሎ የወሰደው አንድም የዐቋም እርምጃ አለመኖሩ በዓቢይነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡
ይኽ የከተማውን ሕዝብ ‹‹ወክለናል›› ብለው በአዲስ አበባ ም/ቤት ወንበር ከያዙ አባላት አንስቶ ከተማዋን በወሳኝ ኃላፊነት ለመምራት እስከተሰየሙ ባለሥልጣናት ድረስ ተሰምቶ የነበረው ኃላፊነት የጎደለው ንግግር አሳዛኝም አስገራሚም ነው፡፡ በተለይም አንዳንድ የም/ቤት አባላት፣ የከተማዋ ፖሊስ ኮሚሽነር እና ከንቲባዋ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ያነሷቸው እና የሰጧቸው ምላሾች ጸረ ሕዝብ እና ጸረ ኢትዮጵያዊነት የተስተዋለባቸው ከመኾናቸው ጋር ተያይዞ ምንም ሳይባሉ በኃላፊነታቸው መቀጠላቸው አስደናቂ ነው፡፡ በተለይም አንዲት የም/ቤት አባል ‹‹በዓላት ሲመጡ ዐዲስ አበባ እየተሸበረች ነው፡፡ ስለዚህ እኛ እንደ ዐዲስ አበባ በዓል ማክበር አንፈልግም፣ ሰርዙልን›› በማለት የሰነዙሩት በጸረ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት የተሞላ ሐሳብ፣ በምን መመዘኛ እንዲህ ያሉ ግለሰብ የዐዲስ አበባ ሕዝብ ተወካይ ኾነው በም/ቤቱ እንደተሰየሙ ግራ ያጋባል፡፡ከተማዋም ምን ያህል የኖረችባቸውን እና የድምቀቷ ማሳያ የኾኑ ዕሴቶቿን በሚጠየፉ ግለሰቦች አመራርነት ሥር ለመውደቋ ማሳያ ይኾናል፡፡
እንደሚታወቀው በዐዲስ አበባም ይኹን በመላው ኢትዮጵያ ይፋዊ የኾኑ የዐደባባይ በዓላት የመስቀል/ከተራ፣ የጥምቀት፣ ዒድ አል አደሃ፣ ኢሬቻ እና ዓድዋ በዋነኝነት ይጠቀሳሉ፡፡ አንድ ለሕዝብ ጥቅም ‹‹ሕዝብን ወክዬ›› ም/ቤት ‹‹ገብቻለሁ›› ብሎ የሚያምን ሰው ለዘመናት የሕዝብ አብሮነት፣ አንድነት እና ደስታ መገለጫ ኾነው የዘለቁ በዓላትን ‹‹ይሰረዙልን፣ ማክበር አንፈልግም›› ብሎ በዐደባባይ እንዲናገር ያስደፈረው ምን ዐይነት ጤናማ አእምሮ ነው ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡
የም/ቤቱ ውሎ አሳፋሪነት ግን በዚህ ብቻ አያበቃም፡፡ የዜጎችን እንደ ዜጋ ባሻቸው ቦታ የመኖር ሰብዓዊ እና ሕገ መንግሥታዊ መብት ጭምር የደፈጠጡ ድምጾችም ተሰምተው ነበር፡፡ በተለይም በሥም ተለይቶ ከተቀመጠ ክልል የሚመጡ ኢትዮጵያውያን ‹‹መንግሥትን በኃይል ለመቆጣጠር በማሰብ እየፈለሱ ነው›› በሚል ፍረጃ እንዲተላለፍ የተፈለገው መልዕክት እጅግ አደገኛ ነው፡፡ ይኽ በከተማዋ ፖሊስ ኮሚሽር እና ከተማዋን በከንቲባነት በሚመሩት ግለሰብ በይፋ የተነገረን አደገኛ ንግግር ተከትሎ በማኅበራዊ ሚዲያ እና በአንዳንድ ማኅበራዊ አንቂዎች ሰፋ ያለ ትችት እና ነቀፌታን አስተናግዷል፡፡ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)ም ዘለግ ያለ መግለጫ በማውጣት ይኽንን የዘር ማጥፋት የሚመስል ጥሪ ያወጁት ሰው በሕግ እንዲጠየቁ ጠይቋል፡፡
እጅግ አሳዛኙ ነገር የሚመጣው ከዚህ በኋላ ነው፡፡ ይኽንን በከንቲባዋ የተላለፈን አደገኛ እና አንድ ወገን ላይ ያነጣጠረ የጥቃት ጥሪ የሚመስል ንግግር ተከትሎ ማዕከላዊውም ኾነ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው የዐማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አንዳችም ነገር አላለም፡፡ ይኽ የም/ቤት ውሎ ከተካሔደ ከቀናት በኋላ ለስብሰባ የተቀመጠው የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴም በማጠቃለያው ባወጣው መግለጫ ‹‹የሃይማኖት አባቶች፣ ሚዲያዎች፣ አክቲቪስቶችና ምሁራን ያለፉ ቁስሎችን ከሚቀሰቅሱ፣ ጥላቻን ከሚያነግሡ፣ ሕዝብ በጥርጣሬ እንዲተያይ ከሚያደርጉ፣ የሀገርን ሰላምና ደኅንነት አደጋ ላይ ከሚጥሉ ድርጊቶችና ንግግሮች እንዲጠበቁ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ጥሪ ያቀርባል፡፡ የሚመለከታቸው የፍትሕና የጸጥታ አካላትም ይሄን መሰል ንግግሮችንና ተግባራትን በቸልታ እንዳይመለከቱ ያሳስባል›› በሚል ሸፍጥን በተሞላ አንቀጽ በጉያው ኾነው ጥላቻን እና መከፋፈልን የሚነዙ አመራሮችን ያላካተተ እና ተጠያቂ ያላደረገ፣ ብሎም ችግሩን ኹሉ ውጫዊ ያደረገ መግለጫ በመሥጠት የችግሩ ባለቤቶችን አቅፎ እና ደግፎ መቀጠልን ምርው አድርጓል፡፡
በአጠቃላይ በአሁናዊው የኢትዮጵያ ማኅበረ ፖለቲካዊ እውነታ፣ የጠብ፣ የጥላቻ እና ንጹሐን ላይ ለሚደርስ ማንኛውም ግፍ እና በደል ዋነኛ ተጠያቂው መንግሥት እና መንግሥት ብቻ ነው፡፡ ከፍ ሲል ያስቀመጥነው ዐይነት መርዘኛ ንግግርን በሕዝብ ፊት የሚናገሩ አመራሮችን ኃላፊነት ለጎደለው ንግራቸው በይፋ ይቅርታ ከመጠየቅ አንስቶ የእርምት እርምጃ እስካለመውሰድ ድረስ ያሳየው ዳተኝነትም፣ ለጊዜው የቆመ እና ያለ ቢመስለውም፣ ራሱን ከተጠያቂነት ባሸሸ ቁጥር ብዙ ርቀት መጓዝ እንደሚሳነው እርግጠኛ ኾኖ መናገር ይቻላል!
