መንግሥት በ‹‹ቁጭ በሉ›› አካሔድ የሚያድነው ሃገር አይኖርም!

Date:

በኢትዮጵያ ግራ ዘመሙ ኃይል የሃገረ መንግሥቱን ሕልውና መበየን የሚያስችለውን ሥልጣን ከተቆናጠጠበት ጊዜ አንስቶ ማኅበረ ፖለቲካዊ ተቃርኖዎች ይበልጥ እየተወሳሰቡ መጥተዋል፡፡ በተለይም በሃያ ሰባት ዓመቱ የህወሓት/ኢሕአዴግ አገዛዝ ዘመን እነኚህ ነገ ከነግ ወዲያ እየፈረጠሙ ወደ መጠፋፋት የሚያደርሱ ፖለቲካዊ ችግሮች በሀቀኛ ምክክር እና ድርድር ይፈቱ ዘንድ ተደጋግሞ ቢጠየቅም ጆሮ ዳባ በመባሉ የኋላ ኋላ ልንወጣው ያልቻልነውን ዋጋ እያስከፈለን ይገኛል፡፡ በዛሬ ተጨባጭ ሁኔታችን በእነኚህ ጽንፍ እየረገጡ በመጡ የፖለቲካ አመለካከቶች ሳቢያ በገዛ ሀገሩ ላይ የመኖር ኅላዌውን ያልተነጠቀ ዜጋን ማግኘትም ይቸግራል፡፡ ያም ኾኖ በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እየገፋ በነበረው ሕዝባዊ አመጻ ወደ ሥልጣን ሲመጡ እንዲህ ያለው ያልተፈታ እና ያደረ ማኅበረ ፖለቲካዊ ተቃርኖ አንዳች የሚያሽር መፍትሔ ያገኛል የሚለው የአብዛኛው የፖለቲካ ማኅበረሰብ ተስፋ ነበር፡፡

እጅግ አሳዛኝ ሊባል በሚችል መልኩ የኾነው ግን ከዚህ በተቃራኒው ነው፡፡ ለችግሮቹ ሀቀኛ እና ዘላቂ መፍትሔ ለመሥጠት ከመጨከን ይልቅ አደንዛዥ እና አዘናጊ የቃላት እንክብሎችን በመሥጠት፣ ዕለት ዕለት የነበረው ፖለቲካዊ መተጋገል ወደ ለየለት ጥላቻ እና መጠፋፋት እንዲያመራ ጠ/ሚኒስትሩ እና መንግሥታቸው መንገድ ጠርጓል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን አንዳች ፖለቲካዊ ጠባይ እያደር እንዲገነግንም ምክንያት ኾነዋል፡፡ ይኸውም በኢትዮጵያችን ተጨባጭ ሁኔታ የሰላማዊ ትግል አርበኞች እና የሐሳብ ትግል አቀንቃኞች የማይሰሙበት፤ ነፍጥ የታጠቁ፣ የሰው እና የንብረት ውድመት የሚፈጥሩ ቡድኖች ደግሞ የተሻለ በጠረጴዛ ዙርያ የመነጋገር ዕድል ያላቸው አካላት የመኾናቸው ጥሬ እውነት ነው፡፡

መጽሔታችን ከወራት በፊት፣ በኢትዮጵያ ማኅበረ ፖለቲካዊ ስንክሳሮች ዙርያ ሐሳብን ማዕከል ያደረጉ ትግሎችን የሚያካሒዱ ወገኖችን እየገፉ በአንጻሩ ነፍጥ ላነገቡ አካላት የተሻለ ቦታ ለመሥጠት እየታዩ ያሉ አዝማሚያዎች በሒደት ፖለቲካዊ ዓላማን ለማሳካት ‹‹ሰው መግደል እና ንብረት ማጥፋት ኹነኛ መንገድ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል›› ስትል ሥጋቷን አጋርታ ነበር፡፡ አሳዛኙ ጉዳይ ግን የተባለው እየኾነ ከመሔዱ በላይ መንግሥት ተመሳሳይ ለሚባሉ ‹‹እንቅፋቶቹ›› ሳይቀር የሚሰጠው ምላሽ አሁንም ፍጹም እየተለያየ መሔዱ ነው፡፡ ጥያቄዎች ሁሉ ያለ ደም መፋሰስ በንግግር እና በድርድር መፈታት አለባቸው የሚለውን የብዙኃን የሐሳብ ፖለቲካ አቀንቃኞች ጥያቄ፣ በአንድ በኩል ‹‹ህወሓት›› እና ‹‹ኦነግ ሸኔ››ን ከመሰሉ የመንግሥትንም ኾነ የሕዝብን ሕልውና ፍጹም አደጋ ላይ ከጣሉ ኃይሎች ጋር ለመነጋገር አረንጓዴ መብራት እያሳዩ፣ በሌላ በኩል ደግሞ እስካሁን የቱንም ዐይነት በሀገረ መንግሥቱ ኅላዌ ላይ አደጋን ሲጋርጥ ካላየነው ‹‹ፋኖ›› ጋር ለመነጋገር አለመፈለግ የእንቆቅልሹን ጥልቀት እንድንመረምር ይገፋናል፡፡

በሌሎች አካባቢዎች ላለፉት ዐራት እና አምስት ዓመታት ተራዛሚ ግጭት ውስጥ ያስገባውን የተሳሳተ ስሌት ከማረም ይልቅ አሁንም በሳምንታት እና በወራት ዘመቻ ‹‹እደመስሳለሁ›› ብሎ የማርያም መንገድ ላለመሥጠት በመንግሥት በኩል የታየው እልህ የተሞላበት እንቅስቃሴ፣ አሁን ላይ በሰፊው የዐማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች መከላከያ ሰራዊቱ የማይገባ ዋጋ እንዲከፍል፣ የመንግሥት አመራሮች ዕለት በዕለት እየተገደሉ እንዲሔዱ ከማድረግ የዘለለ ያመጣው አንዳች ውጤት ባይኖርም፣ ከሦስት ወራት በኋላም መንግሥት ጉዳዩን በፖለቲካዊ ውይይት እልባት ለመሥጠት ከመሞከር ይልቅ ጉልበትን የመጀመርያም የመጨረሻም አማራጩ አድርጎ ለመቀጠል መፈለጉ ብዙ የሚያመራምር ነው፡፡ መንግሥት በየጊዜው ምንም ዐይነት እርባና ሳይኖራቸው ፖለቲካዊ መጠቀሚያ የኾኑ እንደ ‹‹ማንነት እና ወሰን ኮሚሽን›› ያሉ ተቋትን በዐዋጅ መሥርቶ ያለ ዐዋጅ እያፈረሰ፣ በሌላ በኩል ወሣኝ ብሔራዊ ምክክር የሚፈልጉትን የዐዲስ አበባ እና የዙርያዋን ወሰን ጉዳይ በገዛ ውሳኔው መልስ እየሰጠ፣ በመጪው ዓመት ወደ ሥራው ይገባል የሚባለውን ‹‹ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን›› ሚና እያሳጣ ሤረኛ አካሔድ እየሔደ ነው፡፡ እንዲህ ባለው የለየለት የ‹‹ቁጭ በሉ›› መንገድ የሚያቆያትም ኾነ የሚያግባባት ሀገር እንደሌለች በእርግጠኝነት ስሜት ለመናገር የተለየ የፖለቲካ ጠቢብ መኾንን አይጠይቅም፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ አደረሳችሁ፤ አደረሰን

ሰማያት ተከፈቱ ፣ ምስጢርም ተገለጠ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘመዷ ቅድስት...

አባቴ ለእኔ አባት ብቻ አልነበረም፤ ለእናቴ ታማኝ ባል፣ ለሁላችንም ደግሞ የደስታ ምንጭ ነበር

"አባዬ… ዛሬ ላለሁበት ማንነት መሰረት የሆንከኝ አንተ ነህ!" ​የአርቲስት...

የአንበሶቹ ትንሳኤ፦ የዳካር እንባ እና የቴራንጋ ድል

​በዳካር ሰማይ ስር ዛሬ ጨረቃ አልወጣችም፤ ይልቁንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ...

የጥምቀት በዓል በመላ ሀገሪቱ በድምቀት እየተከበረ ነው

የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት...