በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና በተመዘገበው ውጤት “በአብዛኛው ደስተኞች ነን” ሲሉ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተናገሩ። ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ከተፈታኝ ተማሪዎች መካከል 87.2 በመቶው ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚያሳልፋቸው ውጤት ማምጣት ሳይችሉ በቀሩበት እና 565 ትምህርት ቤቶች አንድም ተማሪ አለማሳለፋቸውን ካስታወቁ በኋላ ነው።
ፕሮፌሰር ብርሃኑ የትምህርት ሚኒስትርነት ኃላፊነት ከተረከቡ ወዲህ ለአምስተኛ ጊዜ የተካሄደውን የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና ውጤት ያሳወቁት ትላንት ቅዳሜ ነሐሴ 16፤ 2018 ዓ.ም ነው። ይህን ሀገር አቀፍ ፈተና ለመውሰድ በአጠቃላይ ተመዝግበው ከነበሩ ተማሪዎች ውስጥ 13,750 ያህሉ አለመፈተናቸው በትላንቱ የሚኒስትሩ መግለጫ ይፋ ተደርጓል።
ባለፈው ሰኔ ወር መጨረሻ በበይነ መረብ፣ በሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ ደግሞ በወረቀት አማካኝነት የተሰጠውን ፈተና የወሰዱ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ብዛት 550,210 ነው። ከእነዚህ ተፈታኞች መካከል ወደ ዩኒቨርሲቲ ማሳለፍ የሚያስችለውን 50 በመቶ እና ከዚያ በላይ ውጤት ያስመዘገቡት 70,544 ተማሪዎች መሆናቸውን ፕሮፌሰር ብርሃኑ ተናግረዋል።

በዚህ መሰረት ዘንድሮ ለዩኒቨርሲቲ ያለፉ ተማሪዎች ምጣኔ 12.8 በመቶ ሆኗል። ፕሮፌሰር ብርሃኑ የትምህርት ሚኒስትርነት ኃላፊነትን ከተረከቡ ካለፈው አምስት ዓመት ወዲህ፤ ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚያልፉ ተማሪዎች ምጣኔ 15 በመቶ እንኳ መሻገር አልቻለም።
እርሳቸው ወደ ሚኒስትርነት በመጡበት በ2014 ዓ.ም ከ50 በመቶ በላይ የፈተና ውጤት ማስመዘገብ የቻሉ ተማሪዎች ብዛት 3.2 በመቶ ነበር። በቀጣዩ ዓመት አሃዙ ይበልጡኑ ወደ ታች አሽቆልቁሎ 2.9 በመቶ ተፈታኞች ብቻ ወደ ዩኒቨርሲቲ አልፈዋል።
በ2016 ዓ.ም. 5.2 በመቶ የነበረው 12ኛ ክፍልን ያለፉ ተማሪዎች ብዛት፤ በ2017 ዓ.ም. ወደ 8.9 በመቶ ከፍ ብሏል። ዘንድሮ ያለፉት ተማሪዎች ብዛት አምና ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በ3.9 በመቶ ያህል ጭማሪ ቢያሳይም፤ የትምህርት ሚኒስትሩ በግብነት ያስቀመጡትን 15 በመቶ ምጣኔን ሳያሳካ ቀርቷል።

የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከሚወስዱ ተማሪዎች መካከል ከ15 እስከ 20 በመቶ ያሉትን ወደ ዩኒቨርሲቲ እንዲያልፉ ማድረግ የሚቻል ከሆነ “በጣም ትልቅ” ውጤት እንደሆነ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ባለፈው ህዳር ወር ለፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ተናግረው ነበር። የትምህርት ሚኒስትሩ ይህንኑ አባባላቸውን በትላንቱ ጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይም አስተጋብተውታል።
“ትልቅ” በሚባሉ ሀገራት የሚገኙ ተማሪዎች እንኳ የሚያስመዝግቡት ውጤት “ወደ 23 በመቶ አካባቢ” መሆኑን የትምህርት ሚኒስትሩ በዚሁ መግለጫቸው ላይ ጠቁመዋል። ብዙ ሀገራት “ከ15 እስከ 20 በመቶ ባለው range ውስጥ ናቸው” ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ “እና እኛ ተስፋ የምናደርገው፤ በቀጣዩ ሁለት፣ ሶስት ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ እዚያ ቦታ ላይ ለመድረስ ነው” ሲሉ ግባቸውን አስታውቀዋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ግባቸው ይህ መሆኑን ቢናገሩም፤ እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ በትላንቱ መግለጫቸውም መቶ በመቶ ተማሪዎችን ማሳለፍ የቻሉ ትምህርት ቤቶችን ጉዳይ አንስተዋል። በ2018 ዓ.ም. የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ካስፈተኗቸው ተማሪዎች መካከል ሁሉንም ያሳለፉ ትምህርት ቤቶች ብዛት 88 መድረሱን ፕሮፌሰር ብርሃኑ ገልጸዋል።

ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ውጤት ያስመዘገቡ ትምህርት ቤቶች ብዛት 62 ብቻ ነበር። በዘንድሮው ፈተና ሁሉንም ተማሪዎቻቸውን ካሳለፉ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 42 በመቶው ያህሉ የሚገኙት በኦሮሚያ ክልል ነው። ከእነዚህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 27 በመቶው በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ናቸው።
የ12ኛ ክፍል ተማሪዎቻቸውን ካስፈተኑ ትምህርት ቤቶች መካከል ዘንድሮ ምንም ተማሪ ለዩኒቨርሲቲ ያላሳለፉት ወደ 565 ዝቅ ማለቱን ፕሮፌሰር ብርሃኑ በበጎ ጎኑ አንስተዋል። ባለፈው ዓመት አንድም ተማሪ ለዩኒቨርሲቲ ማሳለፍ ያልቻሉ ትምህርት ቤቶች ብዛት 1,232 ነበር።
በ156 ትምህርት ቤቶቹ የሚገኙ አንዳቸውም ተማሪዎች ያላለፉለት የኦሮሚያ ክልል በዘንድሮው ውጤት የመጀመሪያውን ደረጃ ይዟል። የአማራ ክልል በ98፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በ86፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በ69፣ የትግራይ ክልል በ48 ትምህርት ቤቶች ከሁለተኛ እስከ አምስተኛ ድረስ ባሉት ደረጃዎች ላይ ተቀምጠዋል።

የ2018 ዓ.ም. የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና እነዚህን መሰል አሳሳቢ ውጤቶችን የያዘ ቢሆንም፤ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ግን “በውጤቱ በአብዛኛው ደስተኞች ነን” ሲሉ ተደምጠዋል። “የዘንድሮ ውጤት አምና ከነበረው ጥሩ በሚባል ደረጃ ተሻሽሏል” ያሉት ሚኒስትሩ፤ ይህም መስሪያ ቤታቸው እየሰራ ያለው “ሪፎርም” “ውጤት የሚያመጣ” እንደሆነ አመላካች መሆኑን አስረድተዋል።
“ዝም ብሎ የማለፍ ቁጥር መጨመር ብቻ ሳይሆን በትክክል ተምረው ያለፉ ተማሪዎች ቁጥር እየጨመረ፤ ያ ደግሞ የዩኒቨርሲቲዎችን የትምህርት ጥራት significantly እየጨመረ እንደሆነ ነው የምንገነዘበው” ሲሉ ፕሮፌሰር ብርሃኑ በትላንቱ መግለጫቸው ላይ አጽንኦት ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
