ማኅበራዊ ተሳትፏችን ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል!

Date:

ኢትዮጵያውያን ለረጅም ጊዜያት ከምንታወቅበት በርካታ የወል ማንነት ውስጥ አንዱ እርስ በእርሳችን ያለን ማኅበራዊ መተጋገዝና ተሳትፏችን ነው፡፡ የምንታወቅበት የራሳችን የኾነ ማኅበራዊ ማንነት ያለን ሕዝቦች ነን፡፡ የዳበረ እሴትን ካካበቱ ሀገራት መካከልም ግንባር ቀደም ከሚባሉት ውስጥ ነን፡፡ የመረዳዳት፣ የመተሳሰብ፣ የመተጋገዝ፣ ሰው አክባሪነት፣ ሩሕሩሕነትና አዛኝነትም ከመገለጫዎቻችን ውስጥ ተጠቃሾቹ ናቸው፡፡ በእምነት እሴትም የበለጸግን ሕዝቦች ነን፡፡ ሀገራችን ለዘመናት ሲወርድ ሲወራረድ የመጣ ራሱን የቻለ ማኅበራዊ ስሪትም አላት፡፡ በተለይ እሴቶቿ በአንድ በኩል ሀገር ሲገነቡ በሌላ በኩል የሕዝቡን ሥነ ልቦናዊ ውቅር አንፀዋል፡፡ ማኅበራዊ ስሪታችን ኢትዮጵያዊ ሥነ ምግባር ከዓለም በተለየ መልኩ እንዲገነባም ከፍተኛ ሚናን ተጫውቷል፡፡ ይሉኝታና ነግ-በኔን የመሳሰሉ እራስን በሌላው ቦታ አስቀምጦ የማየት አስተሳሰቦች የኢትዮጵያውያን ስብዕና እንዲኾኑ አስችሏል፡፡ እንግዳ ተቀባይነት፣ እርዳታ የሚያሻቸው ሰዎችን ያለ ጥርጥር በቀናነት መርዳትም አንዱ በዘመናት በተገነባው እሴታችን ምክንያት የመጣ የማንነታችን መገለጫ ነው፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ይህ ማንነታችን እየተሸረሸረ የመጣ ይመስላል፡፡ እንደሕዝብ ፖለቲካዊ የጥላቻ ሰንኮፎቻችን ወደ ማኅበራዊና ማንነታዊ ስብዕናችን ተሸጋግረው እየረበሹን ሳይመጡ አልቀረም፡፡ በመኾኑም ለዚህ ማኅበራዊ ልሽቀት እየዳረገን የመጣው ምንድነው የሚለውን ቆም ብሎ ማየት ያስፈልጋል፡፡ የእምነት ተቋማትና ልዩ ልዩ ሀገር በቀል ትውፊታዊ ማኅበራትም በዚህ ዙሪያ በጥልቀት መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተለይም በዓመት ከአምስት ጊዜ በላይ የምናከብራቸው ሃይማኖታዊ በዓላት የማኅበራዊ መስተጋብሮቻችን መገለጫዎቻችን ናቸው፡፡ ምንም እንኳን ማኅበራዊ ተሳትፎ ዕለት በዕለት የሚገለጽ ሂደት ቢኾንም ሃይማኖታዊ እና ሀገራዊ በዓላት ደግሞ ተሳትፎዎቻችን ይበልጥ የሚገለጡበት ነው፡፡ ጎረቤት ከጎረቤቱ ዘመድ ከዘመዱ የሚደጋገፍበት ነው፡፡ መጪው አዲስ ዓመትም ይህ ማኅበራዊ አንድነታችን የሚታይበት ነው፡፡ ያለው ለሌለው የሚያካፍልበት እርስ በእርስ ተደጋግፎ ያለፈውን ዘመን ሸኝቶ ለአዲሱ ዘመን እራሱን በመልካም ምኞት አንጾ የሚገለጽበት ነው፡፡ በቅርቡ በተለያዩ አካባቢዎች የታዩትን ድንገቴ አደጋዎች ተከትሎ የታየው ማኅበራዊ መረባረብ በሁሉም ዘርፍ ላይ የተሳትፎ አድማሱን አስፍቶ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

“ቴዲ አፍሮ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ቀይሮታል!” — ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ

በ"ወቸው ጉድ" ፖድካስት ላይ እንግዳ ሆነው የቀረቡት ፕሮፌሰር ብርሃኑ...

የኢራን ጦር የሆርሙዝ ወሽመጥን በድጋሚ መዝጋቱን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ

የኢራን መገናኛ ብዙኃን የአገሪቱ ጦር የሆርሙዝ ወሽመጥን ዳግም መቆጣጠር...

ዋን ፕላኔት ኢንተርናሽናል ስኩል 20ኛ ዓመት ክብረ በዓል

ዋን ፕላኔት ኢንተርናሽናል ስኩል 20ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን አስመልክቶ...

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለ20 አትሌቶች  የማስጠንቀቂያ አውጥቷል

በውድድሩ ላይ ያልተገኛችሁ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ይመለከታል የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዓለምአቀፍ...