“ስለ ድርጅቱ በቂ እውቀት ሸምተን ብንወስን መልካም ነው” ኤዶም ዳምጠው

Date:

“በየክፍለ ሀገሩ ሄደን ወጣቶች ላይ ብንሠራ ብዬ የማስባቸው በርካታ ሥራዎች አሉ”

ግዮን መጽሔት :- ኤዶም ለሥራ ያላት ፍቅርና ለውድቀት እጅ አለመስጠቷ፣ በተለይም ለሴቶችና ለወጣቶች ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው፡፡ ከግዮን መጽሔት ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማኅተመወርቅ ጋር በነበራት በዚህ ቆይታም ኤዶም ከቀበና ኪዳነምህረት ካቶሊክ ትምህርት ቤት እስከ ዩኒቨርሲቲ ምረቃ ስለነበራት የትምህርት ጉዞ፣ በሪል ስቴት ገበያ ውስጥ ስላጋጠሟት ተግዳሮቶች፣ ከ850 በላይ ወጣቶችን በነፃ ስላሰለጠነችባቸው መድረኮችና ከትዳርና ከልጆች አስተዳደግ ጋር የሥራ ስኬትን እንዴት ማጣጣም እንደቻለች በዝርዝር ታካፍለናለች፡፡ መልካም ቆይታ! የመጨረሻ ክፍል


ግዮን:- በእናንተ ተቋም ውስጥ ችግሮች እና ተግዳሮት ቢያጋጥሙሽ በምን ዐይነት መልኩ ታልፉታላችሁ?


ኤዶም፡- ቀደም ብዬ እንዳልኩት በተቋማችን የማማከር ሥራዎችን እንሰራ ነበር። በርካታ ድርጅቶችን ስናማክር ነበር። ዋጋ ከማውጣት ጀምሮ እስከ ፍጻሜው ድረስ ሁሉንም ነገር እያንዳንዱ ጉዳይ ላይ ሌላው ቀርቶ ልክ ያልኾኑ ማስታወቂያዎችን ስናይ ሳይቀር እንዲያስተካክሉ እናደርጋቸው ነበር።

እናም ከምናማክራቸው ተቋማት ጋር በመስማማት ነው ጉዳዮችን ለመጨረስ የምንጥረው። ከአንዳንድ ተቋማት ግን ጥሩ ያልኾነ አካሄድና ለውጥ የሌለው ኾኖ ስናገኘው ሥራችንን ልናቆምና ልናቋርጥ እንችላለን።

ይህን ደግሞ እኛ ብቻ ሳንኾን ሌሎች ድርጅቶችም እንዲህ ዐይነት እርምጃዎችን መውሰዳቸው የማይቀር ነው። አሁን ደግሞ የሪል ስቴት ማኅበሩ መምጣቱ እኛ ብዙ ነገሮችን እንድንሰራ ይጠቅመናል።

ግዮን፡- ቤት ለመግዛት ለሚመጡ ሰዎች እንደ ባለሙያ እና በዘርፉ ብዙ እንደቆየ ሰው ምን ትመክሪያቸዋለሽ?

ኤዶም፡- አንዳንድ ነገሮች በደፈናው ነው ትርጉም የሚሰጣቸው። ለምሳሌ በዚህ የሪል ስቴት ልማት ውስጥ በጣም ብዙ ድርጅቶች አግባብነት ባለው መንገድ ቤቶችን ሰርተው ከእነ ካርታው ሁሉን ነገር አሟልተው ለተጠቃሚዎች ያስረክባሉ።

በጣም ጥቂት የኾኑ ድርጅቶች ግን ትንሽ አግባብነት በጎደለው መልኩ ለተጠቃሚ ሊያስተላልፉ ይችላሉ። በእርግጥ ለእንደዚህ ዓይነቱ ኹነቶች የየራሳቸው ምክንያት ሊኖር ይችላል። ነገር ግን ሁሉም ሪል ስቴት አልሚዎች ጥፋተኞች ናቸው ብሎ መደምደም አይቻልም።

እኔ የምለው በግል ደረጃ እንይ ነው። ብዙ አስተያየቶች ስለተሰጡ ያለው የገበያ ሂደት ፈጽሞ እንደጠፋና እንደሌለ ጭምር ነው የሚወራው። አንድ ድርጅት የኾነ ነገር ካደረገ ሌሎች ድርጅቶችንም ተመሳሳይ ድርጊት የፈፀሙ ይመስል ተጠያቂ የማድረግ እና የመጨፍለቅ ነገር አያለሁ።

ስለዚህ ስለ ድርጅቱ በቂ እውቀት ሸምተን ብንወስን መልካም ነው ማለት እፈልጋለሁ። በተቻለ መጠን አቅም ያላቸዉ ስላሉ ከእነርሱ ጋር በመሥራት ውጤታማ እንኾናለን ብዬ አምናለሁ። ለምሳሌ ሕጉ በእኛ ሀገር ገና መጽደቁ ነው።

ስለዚህ ዘርፉ ያለ ሕግ ሲንቀሳቀስ የነበረ ኢንዱስትሪ መኾኑ መዘንጋት የለበትም። ቀደም ሲል ያለ ሕግ መልካም በመሰላቸው ሰርተው ጥሩ ውጤት ያመጡ በጣም በርካታ ተቋማት አሉ። ከዚህ አንፃር ቤታቸውን በጥሩ ሁኔታ ያስረከቡ አሁንም እየሰሩ ያሉ ትላልቅ ድርጅቶች አሉ።

ስለዚህ ሁሉም አንድ ዐይነት ስላልኾነ አብረን ልንሠራ እንዲሁም እንደ ቤት ፈላጊ ደግሞ ልንገዛበት የምንፈልገውን ድርጅት ማጥናት ይኖርብናል። ውላቸው ምን እንደሚመሰል ያከፋፈል ሥርዓታቸው እንዴት እንደኾነ አጠቃላይ የድርጅቱ ነባራዊ ሁኔታ ምን እንደ ኾነ ገምግሞ ለመግዛት መወሰን ይገባል።

አብዛኛው ቤት ፈላጊ ቀነስ ባለ ገንዘብ መግዛት ይፈልጋል። ለምሳሌ ካቦድ ሪል ስቴት አልሚው በአቨሬጅ የቤት ግንባታ ወጪን እንገነዘባለን ከመጠን በታች የመሸጫ ዋጋ ገንዘብ ያመጣ ማንንም አካል አንቀበልም።

ምክንያቱም ከመጠን በታች በኾነ ገንዘብ ቤት ሰርቶ ማስረከብ ስለማይቻል ነው። አልሚው ለንግድ፣ ለመኖሪያ፣ ለቢሮና ለመሳሰሉት ነገሮች የሚኾኑ ግንባታዎችን ለይቶ ማወቅ ይኖርበታል። ቤቱን እንደሰራበት ቁሳቁስና የውድነት ደረጃ አንዱ ከሌለው በተለየ ዋጋ ሊሸጥ ይችላል። ሁሉም ዋጋ የተለያየ ነው። ግን ደግሞ አንድ ቤት ዋጋው አነስተኛ ስለተባለ ብቻ መግዛቱ ኢንቨስትመንቱን አዋጪ አያደርገውም።

ግዮን፡- ከሽያጭ ሠራተኝነት ጀምረሽ ለዚህ ትልቅ ቦታ በቅተሻልና ለሌሎች እህቶቻችን ምን መልእክት ታስተላልፊያለሽ?

ኤዶም፡- በቅርብ ያሉ ሰዎች ስለእኔ ቢናገሩ በጣም ሥራ ወዳድ መኾኔን ይገልፃሉ። ሥራዬን እንደ እረፍት ነው የምቆጥረው። ሥራ ለነገ ማሳደር አልወድም። በዚህ የሥራ ሂደት ውስጥ የቆየሁት 20 ዓመት ነው። ነገር ግን ገና የሚቀጥለውን አሥር እና 15 ዓመታት የተሻለ ሥራ የመስራት ሕልም አለኝ።

ተግዳሮት ሲያጋጥመን ቶሎ ተስፋ መቁረጥ የለብንም። በተለይ ወጣቶች ለዚህ ነገር ተጋላጭ ናቸው። ከዚያ አንፃር ከውድቀታቸው ተምረው ለጠንካራ ሥራ የሚዘጋጁት በጣም ጥቂቶች ብቻ ናቸው። ውድቀትና ተስፋ መቁረጥን ማስወገድ ያስፈልጋል።

ጊዜ ሰጥቶ አንድ ነገር ላይ መቆየት ውጤት ያመጣል ብዬ አምናለሁ። ስለዚህ ተግዳሮት በገጠመኝ ቁጥር እጅ መስጠት የለብንም ብዬ አስባለሁ። ሕይወት መርህ እንዳላት ይታወቃል። ነገር ግን ለሴቶች ደግሞ ከትዳር ጋር በተገናኘ ልጆች ሲመጡ ከፍ ያለ ተግዳሮት አለው።

ለምሳሌ እኔ ራሱ የቤት ሠራተኛ በማይኖረኝ ሰዓት ቤት ልጅ ይዤ የምቀመጥበት ጊዜ አለ። ያም ኾኖ ግን ሁሌም አማራጮችን እፈልጋለሁ። ልጆቼን ይዤ መውጣት ካለብኝም ይዣቸው ልወጣ እችላለሁ።

ግዮን:- የጥንካሬ ምንጭሽ ምንድን ነው? እስቲ ባለቤትሽና ልጆችሽን አስተዋውቂን?

ኤዶም፡- ባለቤቴ አቶ ዮናታን ሽብሬ ይባላል። በሁለቱም ድርጅታችን ላይ አብረን ነው ምንሰራው። ሦስት ልጆች አሉኝ። የመጀመሪያዋ ልጃችን መዳን ዮናታን ትባላለች። አሁን ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነች። ሁለተኛው ልጃችን አምነን ዮናታን ይባላል፣ አሁን አሥር ዓመቱ ነው፡፡ ተማሪ ነው። ትንሹ ደግሞ አብሮን ዮናታን ይባላል፡፡ አሁን ሶስት ዓመቱ ነው፡፡

ለምሳሌ ትዳር ክቡር ነው። ልጆች ክቡር ናቸው። ለእነሱ ጊዜ መሥጠት ያስፈልጋል። ነገር ግን ውስጧ አቅም ያላት ሴት ከትዳር በኋላ ልጆቿን ብቻ በማሳደግ ፍላጎቷን መገደብ የለባትም ብዬ አምናለሁ። እንዲህ ዐይነት ተግዳሮቶችን ማሸነፍ ያስፈልጋል። የእኛ ፍላጎት ከፍ ያለ ከኾነ እግዚአብሔርም በራሱ መንገድ ሁኔታዎችን ያመቻቻል።

ለምሳሌ ካቦድ ላይ አምስት ስድስት የሚኾኑ ሲኒየር ማኔጅመንቶች አሉኝ። ካቦድ የእኔ ብቻ ሳይኾን የሁሉም ነው። እኔ ብኖርም ባልኖርም ማናቸውንም ሥራ ይሠራሉ። ድርጅቱ በፍቃድ ባለቤትነት ደረጃ የእኔ ቢኾንም በጥቅም ግን የጋራችን ነው። ሁላችንም የዚያ ድርጅት ባለቤቶች ነን። ድርጅቱ የሚያገኘውን እድሎች አብረን ነው የምናቅድበት ።

የሥራ አጋሮቼ ከጎኔ ስላሉ ነው እኔንም እንዳላቆም የሚያደርገኝ። ውጪወጥቼ ከ15 ቀን በላይ መቆየት ብፈልግ ድርጅታችን መደበኛ ሥራውን ይቀጥላል። እኔ ስለሌለሁ የሚስተጓጎል ምንም ነገር የለም። መሥራት ለእኔ ትልቅ ብቃት ነው። ቅጥር በነበርኩበት ዘመን የቀሰምኳቸው የሥራ ልምዶች በጣም ጠቅመውኛል። ያ ልምዴ ሕይወቴን መስመር አስይዞታል። ምንም ዓይነት ነገር ቢገጥመኝ እጅ አልሰጥም።

ግዮን፡- የድርጅታችሁ የረጅም ጊዜ እቅድ ምንድነው?

ኤዶም፡- ካቦድ ማርኬቲንግ ሶሉሽን ዋነኛ እቅዱ አሁን ካለበት ሀየበብዙ እጥፍ የተሻለ ሥራ እንዲሠራ እናልማለን። ከሀገር ውስጥ አልፎ ወደ ውጪው የኢንቨስትመንት መስክ እንዲሳተፍ እንሻለን። ድርጅታችን በከተማ ውስጥ ከሁሉም የተሻለና መሪ እንዲኾን እፈልጋለን።

በእርግጥ ይህን ለማድረግ ብዙ ዋጋ እንደሚያስከፍልና እንደሚያደክም እናውቃለን፡፡ በየክፍለ ሀገሩ ሄደን ወጣቶች ላይ ብንሠራ ብዬ የማስባቸው በርካታ ሥራዎች አሉ። እንደ እግዚአብሔር ፍቃድ እንሰራለን። ፖድካስቶችንም ለመስራት እናስባለን። በዶክሳ በኩል ደግሞ ብዙ ማሳካት የምንፈልጋቸው እቅዶች አሉን።

በቅርቡ ለንደን ላይ የሚካሄድ ኤክስፖ አለ። እዚያ ላይ ትልቅ ተሳትፎ እያደረግን እንገኛለን። ሌሎች ቦታዎች ላይም ለመሳተፍ ዝግጁ ነን። ከተመሳሳይ የጎንዮሽ ተቋማትም ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረን እየሠራን እንገኛለን።ሁለቱ ድርጅቶቻችን ተደጋጋፊ ስለኾኑ በቀጣይ ትልቅ እንሥራለን ብዬ እምናለሁ።

ግዮን፡- ቀረ የምትይው ነገር ካለና ማመስገን የምትፈልጊው አካል ካለ?

ኤዶም፡- በቅርቡ የተካሄደውን ኤክስፖ በተመለከተ የሪል ስቴት አልሚዎች ማኅበሩን ማመስገን እፈልጋለሁ። ባለቤቴና ሁሉንም የሥራ አጋሮቼን አመሰግናቸዋለሁ። ዶክሳ እንደድርጅት ከተማችን ውስጥ ሁለት ትልልቅ ሥራዎችን ነው የሰራው።

የሪል ስቴት ማኅበሩ አምኖን ሥራዎችን ስለሰጠን እናመሰግነዋለን። የኢትዮጵያ ሪል ስቴት አልሚዎች ማኅበር የቦርድ አባል ሁሉንም እጅግ አድርጌ ማመስገን እፈልጋለሁ ። ሥራችን በዋናነት የነበረው ከነዚህ የተከበሩ ሰዎች ጋር ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ሪል ስቴት አልሚዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ አለማየሁ ከተማን ከልብ ማመስገን እፈልጋለሁ። በጣም ብዙ ነገር ረድተውናል። በአጠቃላይ የሪልስቴት አልሚዎች ማኅበር ቢሮ ሰራተኞችን ማመስገን እፈልጋለሁ።

ግዮን፡- ስለነበረን ቆይታ በአንባቢያን ስም እናመሠግናለን፡፡

ግዮን መጽሔት ቅጽ 8 ቁጥር 234   2018 ዓ.ም

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

በኢትዮጵያ 50 ሚሊዮን የሚገመቱ ዜጎች የንፁህ መጠጥ ውሃ እንደማያገኙ ተነገረ

በኢትዮጵያ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትን በበቂ ሁኔታ ለማሳካት የሚያስችል...

ገዳ ባንክ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ አተረፍኩ አለ

ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ113 በመቶ እድገት አሳይቷል ...

እስራኤል የኢራን ተደራዳሪዎችን ለመግደል እያሴረች እንደነበር ተዘገበ

አሜሪካና ኢራን ወሳኝ የሆነውን የተኩስ አቁም ስምምነት በደረሱበት እስራኤል...

ከኡጋንዳ ወደ ኢትዮጵያ የመጀመሪያው በፋብሪካ የተቀነባበረ  የበሬ ሥጋ ንግድ ተጀመረ

‘ራንቸርስ ፋይነስት’ የተባለው የኡጋንዳ የግል ሥጋ አቀናባሪ ኩባንያ፣ በየወሩ...