በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ መሠረታዊ የሆኑ የሕግ ጥሠቶች መፈጸማቸውን ቦርዱ አስታወቀ

Date:

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደ/ብ/ብ/ሕ ክልል በሚገኙ ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች ላይ ሕዝበ ውሣኔ በሚካሄድባቸው በአንዳንድ ምርጫ ጣቢያዎች ላይ የተፈጸሙ የሕግ ጥሠቶችን እና የወሰዳቸው የዕርምት ዕርምጃዎች በዛሬው ዕለት ይፋ አድርጓል። ቦርዱ ለሕዝበ ውሣኔው የምርጫ ጣቢያዎችን በማቋቋም የመራጮች ምዝገባ እያከናወነ እንደሚገኝ የሚታወቅ ሲሆን፤ ይህንንም የምዝገባ ሂደት ለመከታተትልና ለመቆጣጠር ከቦርዱ የኦፕሬሽን ሥራ ክፍል የተዋቀረ ቡድን ከታሕሳስ 16 – ታሕሳስ 18 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ የክትትል ሥራ ማድረጉን አስታውቋል። በዚህም የክትትል ሥራ፤ በዎላይታ እና በጎፋ ዞኖች በሚገኙ አንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ መሠረታዊ የሆኑ የሕግ ጥሠቶች መፈጸማቸውን ማረጋገጡን ገልጿል። ቦርዱም የቀረበለትን ሪፖርት ተመልክቶ በተጠቃሾቹ ጣቢያዎች ላይ የተደረገው ምዝገባ እንዲሠረዝ፣ የመራጮች ምዝገባ ሂደቱም ሙሉ በሙሉ እንዲቆምና እንዲሁም የጣቢያዎቹ ሠራተኞች ከኃላፊነታቸው እንዲነሡ፣ በተጨማሪም ሁሉም የምርጫ ጣቢያው ሠራተኞች እና ግብር-አበሮቻቸው በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በኩል የወንጀል ምርመራ እንዲደረግባቸው  የወሠነ ሲሆን፤ የመራጮች ምዝገባውም አዲስ ሠራተኞች ተመልምለው  በድጋሚ እንዲደረግ መመሪያ መስጠቱንም አስታውቋል። በቀጣይም ቦርዱ ምዝገባውን ለማከናወን እና ያለፉትን የምዝገባ ቀናት ለማካካስ የሚያስፈልጉትን ተጨማሪ ቀናት እና ምዝገባው እንደገና የሚጀመርበትን ቀን እንደሚያሳውቅ የገለጸ ሲሆን፤ የሕግ ጥሠቶች የተፈጸሙባቸው ጣቢያዎች እና የተፈጸሙ ሕገ-ወጥ ተግባራት ዝርዝር አስታውቋል።

በዚህም መሠረት:-

1. በዎላይታ ዞን ዱቦ ምርጫ ጣቢያ ማንቴ ዱቦ የተፈጸመው ጥሠት፦ መሰለ ኤሊያስ ከሚባል ግለሰብ ሥም ዝርዝር በመቀበል በመራጮች መዝገብ ላይ መመዝገብ፣ በተጨማሪም የቦርዱ ሠራተኛ ላልሆነ ወልዴ ወራጆ ለተባለ ግለሰብ ቁልፍ በመስጠት ምዝገባውን እንዲያከናውኑ ማድረግ፣

2. በዎላይታ ዞን ዶላ ምርጫ ጣቢያ ሦስት ንዑስ ጣቢያ የተፈጸመው ጥሠት፦ አርጃ አሊሶ ከሚባል ግለሰብ ሥም ዝርዝር በመቀበል በመራጮች መዝገብ ላይ መመዝገብ፣

3. በዎላይታ ዞን ወርሙማ ምርጫ ጣቢያ ቤታሎ ለ የተፈጸመው ጥሠት፦ ግለሰቦች ፊርማ ሳይፈርሙ የመራጭነት ካርድ እንዲወስዱ ማድረግ፣

4. በዎላይታ ዞን ጫማ ሄምቤቾ ምርጫ ጣቢያ አምስት የተፈጸመው ጥሠት፦ በመዝገቡ ላይ ላልፈረሙ ግለሰቦች ካርድ መስጠት፣

5. በዎላይታ ዞን ወርሙማ ምርጫ ጣቢያ ወርሙማ ሀ የተፈጸመው ጥሠት፦ ግለሰቦች በግንባር ምርጫ ጣቢያ ሳይቀርቡ እና ሳይፈርሙ መራጮች መዝገብ ላይ መመዝገብ፣

6. በዎላይታ ዞን ማንቴ ጌራራ ምርጫ ጣቢያ ማንቴ ጌራራ ሦስት የተፈጸመው ጥሠት፦ ግለሰቦች በግንባር ምርጫ ጣቢያ ሳይቀርቡ እና ሳይፈርሙ መራጮች መዝገብ ላይ መመዝገብ፣

7. በዎላይታ ዞን ቶሜ ጌሬራ ምርጫ ጣቢያ ቶሜ ጌሬራ አራት የተፈጸመው ጥሠት፦ ግለሰቦች በግንባር ምርጫ ጣቢያ ሳይቀርቡ እና ሳይፈርሙ መራጮች መዝገብ ላይ መመዝገብ

8. በዎላይታ ዞን ዋጭጋ ቡሻ ምርጫ ጣቢያ ዋጭጋ ቡሻ 02 የተፈጸመው ጥሠት፦ የመራጮች ፊርማ ሳይፈርሙ ግለሰቦች እንዲመዘገቡ እና ካርድ እንዲወስዱ ማድረግ

9. ጎፋ ዞን ጃዉላ ጎሬ አዳ ምርጫ ጣቢያ የተፈጸመው ጥሠት፦ ተመሳሳይ የሆነ ወይንም በአንድ ሰው የተፈረመ በሚመስል ፊርማ ከአንድ በላይ ካርዶችን ወጪ ማድረግ፣

10. ጎፋ ዞን ጃዉላ ውጋ መሸተላ ምርጫ ጣቢያ ሀ የተፈጸመው ጥሠት፦ ግለሰቦች የመራጮች መዝገብ ላይ ሳይፈርሙ የምርጫ ካርድ እንዲወስዱ ማድረጋቸው ይጠቀሳሉ እንደሚጠቀሱ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

ስለሆነም ቦርዱ በቀጣይም የክትትል ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጸ ሲሆን፤ ማንኛውም ተመሳሳይ ተግባራት ሲከናወኑ ያየ ግለሰብ በነፃ ስልክ መስመር 778 ላይ ደውሎ ጥቆማውን ማቅረብ እንደሚችልም አስታውቋል።

ቀዳሚ ጽሑፍ
ቀጣይ ጥሑፍ

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የአርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ስርዓተ ቀብር ተፈጸመ

የአርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ስርዓተ ቀብር በመንበረ ጸባኦት ቅድስት...

በእስር ላይ የሚገኙት መምህርት መስከረም ዓይናቸው በጽኑ መታመሙን ጠበቃቸው ገለጹ

ከሁለት ዓመት በላይ በእስር ላይ የሚገኙት መምህርት መስከረም አበራ...

ንግድ ባንክ “ስታርፔይ” የተሰኘ አዲስ መተግበሪያ ይፋ አደረገ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል ባንክ ሥርዓቱን ይበልጥ ዘመናዊና ቀልጣፋ...

በኢትዮጵያ በካንሰር ከሚያዙ ሕፃናት መካከል 75 በመቶ የሚሆኑት ህክምና አያገኙም

በኢትዮጵያ በየዓመቱ በካንሰር ከሚጠቁ ከ6 ሺህ እስከ 8 ሺህ...