
የአሜሪካ ጦር በዚህ ሳምንት መጨረሻ በኢራን ላይ አዲስ ጥቃት ለመክፈት እየተዘጋጀ መሆኑን ስማቸውን ያልጠቀሷቸውን ምንጮች ዋቢ አድርገው የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።
ለሲቢኤስ መረጃ የሰጡ ምንጮች ጥቃቱ የኢራን የኃይል መሠረተ ልማቶች ላይ ሊያተኩር እንደሚችል ጠቅሰው፤ ነገር ግን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ይሁንታ መስጠት አለባቸው ብለዋል።
የእስራኤል ጦር ከረዥም ጊዜ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ በጥቃቱ ላይ ሊሳተፍ እንደሚችል አክሲዮስ ዘግቧል።
አርብ ዕለት በካምፕ ዴቪድ ለጋዜጠኞች ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ፕሬዚዳንት ትራምፕ “ክፉኛ እንደበድባቸዋለን” ብለዋል።
“የሆነ ጊዜ ‘ከዚህ በላይ መቀበል አንችልም’ ማለት መቻል አለባቸው” ሲሉም አክለዋል።
በዓለም አቀፉ ሕግ መሠረት ሰላማዊ ዜጎች የሚጠቀሙበትን መሠረተ ልማት ማጥቃት የጦር ወንጀል ነው።
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እዝራኤል ካትዝ ማክሰኞ ዕለት “የኢራንን የኤነርጂ ተቋማት ለመደብደብ በጣም እንፈልጋለን” ብለው ነበር።
ቻናል 14 ከተባለ የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን ጋር በነበራቸው ቆይታ “[ኢራን] ጎረቤት አገራት ላይ ጥቃት ልትፈጽም እና ዓለም አቀፍ ቀውስ ሊከሰት ይችላል በሚል ስጋት አሜሪካ እስካሁን ይሁንታዋን አልሰጠችም” ሲሉ መናገራቸውን ዘ ታይምስ ኦፍ እስራኤል ዘግቧል።
“እኛን በሚመለከት ግን [ኢራንን] አርባ ዓመት ወደ ኋላ ለመመለስ ተዘጋጅተናል” ብለዋል።
የፔንታጎን ቃል አቀባይ ሺን ፓርኔል በየትኞቹ ዒላማዎች ላይ ጥቃት እንደሚፈጸም ከመናገር ተቆጥበዋል።
ፓርኔል ለሲቢኤስ ኒውስ በሰጡት መግለጫ “የጦር መሥሪያ ቤቱ ምን ጊዜም የፕሬዚዳንቱን ትዕዛዝ በመጣበት ቅጽበት ለመፈጸም በተጠንቀቅ ነው ያለው” ብለዋል።
አንድ የኢራን ባለሥልጣን በመሠረተ ልማቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት “የእብደት” ምልክት ነው በማለት አገራቸው የአጸፋ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆኗን መናገራቸውን አል-ጃዚራ ዘግቧል።
ባለሥልጣኑ አክለውም የኢራን ምላሽ “የጽዮናዊያን መንግሥት ወሳኝ መሠረተ ልማቶችን እና በቀጣናው የሚገኙ የአሜሪካ የኤነርጂ ተቋማትን” እንደሚያካትት ተናግረዋል።
