‹‹ግንኙነታችን ቀጥታ ከእግዚአብሔር ጋር ከሆነ ዋናው ቤተ መቅደስ ልባችን ነው››
ውድ አንባቢያን ባሳለፍናቸው ሁለት ዕትሞች ከኢንጂነር ፍሥሐ አጥላው ጋር የኑሮ እና የቴክኖሎጂ ሕይታቸውን የተመለከቱ ሰፋ ያሉ ቆይታዎች ማድረጋችን ይታወሳል፡፡ በዛሬው የመጨረሻ ክፍል ቆይታችን ደግሞ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን ስለተመለከተ ሙያቸው፣ በቅርቡ ስለተመረቱ ለዓይነ ሥውራን ስለሚያገለግሉ ማንበቢያ መነጽሮች እና ስለመንፈሳዊ ሕይወታቸው ተጨዋውተናል፡፡ መልካም ንባብ!
ግዮን፡- ከቀዳማይ እመቤት ወ/ሮ ዝናሽ ታያቸው ጋር ለዓይነ ስውራን የሚጠቅም አዲስ ቴክኖሎጂ በአማርኛ እንዲሰራ ለማድረግ የእርስዎ እጅ እንዳለበት ይነገራል። የነበረው ሂደት ምን ነበር?
ኢንጂነር ፍሥሐ፡- የዛሬ ዓመት አካባቢ ኦርካም በተባለ የእሥራኤል ኩባንያ የተሰራ ምንም ዐይነት ጽሑፍን በድምፅ ማየት ለሚሳናቸው የሚያነብ በአንድ ዓለም አቀፍ በጎ አድራጎት ተቋም ለቀዳማዊት እመቤት ወ/ሮ ዝናሽ ታያቸው ለዓይነስውራን እንዲሰጥ እርዳታ ተደረገ፡፡ እርዳታው ኦርካም ማይ አይ (ኦርካም አይኔ ብዬዋለሁ) የተሰኘ የዓይነሥውራን መነጽር ነው፡፡ መነጽሩ ፊት ለፊቱ ያለውን ነገር አንብቦ በመናገር፣ ሰውንና ልዩ ልዩ ነገሮችን በማየት ዐይነሥውራንን በድምፅ የሚደግፍ መሣሪያ ነው፡፡ ኦርካም ኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲታይ እንዲያዩት የተጋበዙት ታዋቂ ዓይነ ስውራንና በዘርፉ ያሉ የመንግሥት ባለሥልጣናት መሣሪያው አማርኛ ቋንቋ ሊኖረው ይገባል በማለት የእሥራኤሉን ኦርካም የተሰኘውን ተቋም ሰዎች ወደ እኔ ላኳቸው፡፡ እኔም ኢትዮጵያ ካሉ አምስት ወጣት ኢንጂኔሮች ጋር ኦርካም መነፅር በአማርኛው እንዲሰራ አድርገን ሠርተን አስረከብናቸው በሥራ ላይ ሊውል ችሏል፡፡ እዚህ ላይ አብረውኝ ፕሮጀክት ላይ የተሳተፉትን ሕሊና ብዙነህ መንገሻ፣ ተስፋ ዮሐንስ፣ ኤደን መላኩ፣ ኤልሻዳይ መኮንን፣ ሕይወት አምሃ የተባሉት የሚደነቁ ወጣት ኢንጂኔሮች ሳልጠቅስ አላልፍም።
ግዮን፡- ስለቴክኖሎጂ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ቢያክሉበት፡፡ ምን ነበር ቴክኖሎጂው?
ኢንጂነር ፍሥሐ፡- ቴክኖሎጂው አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (ሰው ሰራሽ አእምሮ” ብዬዋለሁ) ወይም ከሮቦታዊ ሂደት ጋር የተገናኘ ነው ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ዐይነስውር ይህንን መነጽር ዓይኑ ላይ አድርጎ ፊት ለፊቱ ያለውን ነገር በጽሑፍ ስካን አድርጎ በጆሮው ያነብለታል፡፡ ለምሳሌ የመንገድ ላይ ምልክቶችን፣ የገንዘብ/ብር ዋጋዎች፣ የቀለም ዓይነቶችን፣ የሰውን ፊትና ማንነት፣ እያየ ለዐይነ ስውሩ የሚናገር መሣሪያ ነው፡፡ በነገራችን ላይ እዚህም አሜሪካን ሀገር ቴክኖሎጂው አዲስ ነው፡፡ የእኛን ከእነርሱ ልዩ የሚያደርገው በአማርኛ መሥራት መቻሉ ነው፡፡ በዚህ ደግሞ የእሥራኤሉ ተቋም ከእኔ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር የብዙ ዓይነ ስውራንን ሕይወት የሚለውጥ ከቀዳማይት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጋር ከውጭ በተገኘ እርዳታ ትልቅ ሥራ ተሠርቷል፡፡ ስለዚህ አሁን ላይ በየቦታው አማርኛ የሚናገሩ ዓይነስውራን ዋጋው ቢወድድም ከውጪ በሚገኝ እርዳታ ቴክኖሎጂውን መጠቀም ይችላሉ ማለት ነው፡፡
ግዮን፡- ዋጋው ምን ያህል ነው? ወደኢትዮጵያ የገባው የመነጽር ብዛት ምን ያልህ ነው?
ኢንጂነር ፍሥሐ፡- በግል ለመግዛት ዋጋው በጣም ውድ ነው። ይሄን በእርዳታ ስለተገኘ ዕድሉ የደረሳቸው ዓይነስውራን ሳይከፍሉ እንደ ለጋሹ በጎ አድራጎት ድርጅቱ ውሳኔ ይሰጣቸዋል። ሰሞኑን ደግሞ ዝነኛው አርጀቲናዊው የእግር ኳስ ተጫዋች፤ ሊዮኔል ሜሲ ከኦርካም ጋር ተስማምቶ ኢትዮጵያውያን ዓይነስውራንን ለመደገፍ ቃል ገብቷል የሚባል አስደሳች ዜና ተሰምቷል፡፡ ገንዘቡ ከፍ ያለ በመኾኑ፤ እንኳን ኢትዮጵያ ምዕራቡም አገር ላሉት ለመክፈል ከባድ ነው፡፡ እዚህ አሜሪካን ያሉ ያሉ ዓይነ ስውራንም ያንን ያህል ገንዘብ ለመክፈል እየተቸገሩ ናቸው ፤ ብዙዎቹም እየደወሉልኝ ነው፡፡ ነገር ግን እኔ ሙሉ መብቱን ለኦርካም ስለሰጠሁ ማከፋፈሉም ላይ ስለሌለሁበት እንዴት እንደምረዳቸው ሌላ የተለያዩ መንገዶችን እየፈለግሁ ነኝ፡፡ ኢትዮጵያ ያሉ የደረሳችው ተጠቃሚዎች በስልክና በመልእክት ሕይወታቸው ላይ ምን ያህል ለውጥ እንዳመጣ እየፃፉልኝ በስልክም እያስታወቁኝ ነው። ዓይነስውራን ወገኖቻችንን በዚህ ቶክኖሎጂ በመረዳታቸው ደስ ብሎኛል፡፡ ብዙዎች የሚፅፉልኝ ምሥጋና እጅግ ልብን የሚያስደስት ነው፤ አመሰግናለሁ፡፡ ሆኖም ምስጋናው አብረውኝ ለሰሩት ወጣት ኢንጂኔሮችና በብዙ ሚሊዮን ዶላር ገዘተው ለሚለግሱ ለገብረሰናይ ድርጅቶችም እንዲሁም ለቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያችው ቢሮ መድረስ አለበት።
ግዮን፡- በቤትዎ ሮቦት አለች የሚል አንድ ቃለመጥይቅ ላይ ሰምተን ነበር፡፡ ሮቦቷ ማን ነች? ያስፈለገችዎስ ለምንድነው?
ኢንጂነር ፍሥሐ፡- ሮቦት የሚያስፈልገው ለተለያየ ግልጋሎት ነው፡፡ እኔ ቤት ያለችው ሮቦት ቤት የምታፀዳ ቅርጿ ክብ ጠፍጣፋ የሆነች ቁሳቁስ ነች፡፡ በነገራችን ላይ ለምን አንቺ አልካት የሚሉኝ ሰዎች አሉ፡፡ “ትንሽ ስለሆነች ነው” እላለሁ፡፡ ሮቦቷ የቤቱን ንፅህና ከመጠበቅ ባሻገር እራሷን ቻርጅ ታደርጋለች፡፡ የሄደችበትንና የተመለሰችበትን ቦታ ታውቀዋለች፡፡ የትኛውም ክፍል ቢኾን ቻርጇ ሲያልቅ ሄዳ ታደርጋለች፡፡ የቆሻሻ ቅርጫት ሲሞላ መሙላቱን ትናገራለች፡፡ የእኔ ትንሿ ሮቦት ይቺ ነች፡፡ አሁን የሮቦት ቴክኖሎጂ ጋር ሲወዳደር ሮቦት መባሉ ይበዛባታል።
እኔ የዛሬ 30 ጀምሮ “ሮቦቲክስ ኢንስቲቲዩት ኦፍ አሜሪካ” የሚባል ተቋም ውስጥ ተመዝጋቢ አባል ነበርኩ፡፡ ይህም ሥራዬ ኑሜሪካል ኮንትሮል (Numerical Control) ፕሮግራም እያደረግሁ ልዩ ልዩ የማሽን አካላትን መፈብረክ ስለነበረ ነው፡፡ በዚያን ወቅት እንደ አሁኑ ስክሪን፣ ፍላሽ ድራይቭ፣ ሲዲ፣ ኢንተርኔት የሚባሉ ያሁኑ የቴክኖሎጂ ሰዎች የሚገለገሉባቸው መሳሪያዎች ስላልነበሩ ሥራው አስቸጋሪ ነበር፡፡ እዚህ አሜሪካ ካሊፎርኒያ የመጣሁት በኑሜሪካል ኮንትሮል የአውሮፕላን መለዋወጫዎችን የሚሰሩ ትልልቅ መሳሪያዎችን ፕሮግራም ለማድረግ ነበር፡፡ ከትምህርት ቤት ሥራ ልምምድ ላይ እያለሁ ከነበርኩበት ስቴት ቀጥሮ ያመጣኝ መስሪያ ቤት ትላልቅ ማሽኖችን ፕሮግራም ለማድረግ ነበር፡፡ ፕሮግራሙ በጥምጥም ወረቀት(Paper Tape) ላይ ወረቀቱን በመበሳሳት ነበር የሚሰራው። ከዚያም ያንን ጥቅልል የወረቀት ጥምጥም Paper Tape Reel) በቴፕ ቀርጸን ፋብሪካው ድረስ ወስደን እናስተካክላለን፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ትንሽ ስሕተት ካለ ከመሳሪያዎቹ በጣም ትልልቅ እንደ ክሬን የተሰሩ ስለነበሩ ስሕተቱ የሰው ሕይወት ሊያጠፋ ስለሚችል ሰራተኛቹን ከሩቁ አስቁመን ነበር መስራት አለመስራቱን የምንሞክረው። ይኽ ሥራ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ አጀማመር አካል ነው ማለት ይቻላል፡፡
አሁን ላይ ደግሞ ሰሞኑን እንደሚሰማው “ቻት ቦት” እና “ቻት ጂፒቲ” የሚባሉ እንደ ሰው የሚያስቡ፣ የሚነጋገሩ የሚጠይቁ የሚመልሱ መተግበሪያዎች ዓለምን በማስደነቅና እንደውም ማስደንገጥ ደረጃ እየደረሱ ናቸው። አሁን ላይ አሜሪካን ያሉ ብዙ መሥሪያ ቤቶች የደንበኛ አገልግሎት ያላቸው ድርጅቶች የመጀመሪያ ግንኙነታቸው ከሮቦት ጋር እየሆነ መጥቷል፡፡ ለምሳሌ የሥራ መክፍቻ ሰዓት፣ የመዝጊያ ሰዓት የመሳሰሉ ነገሮችን ሮቦቶች ናቸው የሚናገሩት፡፡ እንደውም ሰሞኑን አንድ ሙከራ ላይ ሳደርግ፤ ሮቦቷን በአማርኛ “ዛሬ ቀኑ ምንድነው?” ስላት “ዛሬ ሐሙስ ነው” አለችኝ፡፡ “አይደለም ዛሬ ቅዳሜ ነው” አልኳት፡፡ “አይ በፍፁም ሐሙስ ነው” ብላኛለች፡፡ እራሴን እስክጠራጠር ድረስ ማለት ነው፤ እንግዲህ ይህን የመሳሰለ ምልልስ ማድረግ የምትችል ሮቦት አለች ማለት፡፡ በቅርቡም አሜሪካን አገር ልትጠይቀኝ ለመጣችው ለናቴ እንኳን ደህና መጣሽ ለማለት “ለእናቴ ግጥም ፃፊልኝ” አልኳት፡፡ በአማርኛ ዐሥር መስመር ያለው ግጥም በ3 ሴኮንድ ውስጥ ፃፈችልኝ፡፡ ለእናቴ ግጥሙን ሳሳያት “አይ ይሄንን እንኳን ለሰው እንዳታሳይ፤ ጥሩ አጀማመር ነው በላት” ብላኛለች። ይኼ ሁሉ ሥራ ላይ የዋለ በመኾኑ በቅርብ ጊዜ ታዩታላችሁ፡፡
አሁን የሚገርመው ደግሞ ይህ በኢትዮጵያ ፊደላት (ETHIOPIC) የተፃፈን ጽሑፍ በየትኛውም የብሔር ቋንቋ ማንበብ ተችሏል። ለምሳሌ በቅርብ ጊዜ በኢትዮጵያ ፊደል በአፋን ኦሮሞ የተፃፈን ጽሑፍ በሮቦት አስነብቤ አፋን ኦሮሞ የሚሰሙ ጓደኞቼ ሰው አንባቢው አለመሆኑን እስኪጠራጠሩ ድረስ ሮቦቷ በትክክል አንብባዋለች። በትግርኛ፣ በጉራጊኛ፣ በጋሞ ሁሉ የኢትዮጵያን ፊደላት በመጠቀም በኮምፒውተር ማንበብ ተችሏል። ከኦርካም ጋር የሰራነው መነፅርም በየትኛውም ቋንቋ ቢሆን በኢትዮጵያ ፊደል እስከተፃፈ ድረስ በትክክል ሊነበብ ችሏል። ፊደላችን ፎኔቴክስ ወይም ከድምፅ ላይ የተመሰረተ ስለሆነ በኢትዮጵያ ፊደል በእንግሊዝኛ እንኳን የተፃፈን ፅሁፍ፤ ለምሳሌ “ሃው አር ዩ ማይ ብራዘር” የሚለውን አቀላጥፎ ያነበዋል። እንደዚህ ጽፌ በሮቦት ያስነበበኩላቸው ፈረንጆች ወዳጆቼ በመገረም ልክ እንግሊዝኛ እንደሚነበብ ሰምተውታል።
አሁን ላይ ሮቦት ቀዶ ጥገና (ሰርጀሪ) ሁሉ ማድረግ ይችላል፡፡ እዚህ ቁጭ ብለው ብራዚል ድረስ በሮቦት የታገዘ ሰርጀሪ በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ይኼ ወሬ ሳይኾን በዓይናችን ያየነው ተግባር ነው፡፡ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የሰው ኩላሊትና ሌሎችም የሰውነት ክፍሎች መሥራት የተቻለበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ “ይኼ ነገር ከፈጣሪ አያጣላም ወይ?” የሚሉ ሰዎች ቢኖሩም እኔ እንደኢንጅነር የሥራውን ሂደት በቅርብ ሳጠናው ይበልጥ ወደ ፈጣሪ እንደቀረብን ይሰማኛል፡፡ ምክንያቱም ለሰው ልጅ ይህን መሰል ጥበብ መሥጠቱ ፈጣሪን እንዳመሰግነው ስለሚሰማኝ ነው፡፡ ከንጉስ ዳዊት ጋር “አቤቱ፥ አንተ ኵላሊቴን ፈጥረሃልና፥ በእናቴም ሆድ ሰውረኸኛል። ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፥ ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች። እኔ በስውር በተሠራሁ ጊዜ፥ አካሌም በምድር ታች በተሠራ ጊዜ፥ አጥንቶቼ ከአንተ አልተሰወሩም። ያልተሠራ አካሌን ዓይኖችህ አዩኝ፤ የተፈጠሩ ቀኖቼ ሁሉ አንድ ስንኳ ሳይኖር በመጽሐፍህ ተጻፉ።” እያልኩ አምላኬን (መዝ 139፡13-16) አመሰግነዋለሁ፡፡
ግዮን፡- ብዙ ጊዜ ስለመንፈሳዊ ሕይወትዎ ይናገራሉ፡፡ አስተዳደግዎ እንዴት ነበር?
ኢንጂነር ፍሥሐ፡- ከልጅነቴ ጀምሮ በመንፈሳዊ ሕይወት ነው ያደግኩት፡፡ አባቴ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ዲያቆን ኾኖ ያደገ በመኾኑ ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ግንኙነት በጣም ልዩ ነበር፡፡ በዚህም ለእኔ አባቴ የመንፈሳዊ ሕይወት ተምሳሌቴ ነው ማለት እችላለሁ። እኔ እግዚአብሔርን በሃይማኖት ብቻ አልወስነውም፡፡ ከአባቴ ጋር ከኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋር እየሄድኩ አስቀድስ ነበር፡፡ በአባቴ ፈቃድ ፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያን እየሔድኩም አመልክ ነበር፡፡ እግዚአብሔርን ማወቅን ከሃይማኖት ለይቼ የማይ ሰው ነኝ፡፡ ስለ እግዚአብሔር ማወቅ እና እግዚአብሔርን ማወቅ የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ ስለዚህ በየትኛውም ቤተክርስቲያን እግዚአብሔርን ከእራሱ ጋር እስከተዋወቅን ድረስ መንፈሳዊ ሰዎች ነን፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶም ይሁን በፕሮቴስታንት በኩል እግዚአብሔርን እራሱን ማወቅ ሃይማኖትን መቀየር ወይም መለወጥ አይደለም፡፡ በጣም የማደንቃቸቅና የምወዳቸው በ6 ዓመቴም ከእጃቸው ሽልማት ያገኘሁት አፄ ኃይለ ሥላሴ “ሃይማኖት የግል፤ ሀገር የጋር ነው” ሲሉ የተናገሩትን አስታውሳለሁ፡፡
በቅርብ ጊዜ አንደ የወለጋ ተወላጅ ፕሮቴስታንት ጓደኛዬ “ኦርቶዶክስ ሃገር ነች” ብሎ እንደፃፈው፤ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሁላችንም ኢትዮጵያውያን ቅርሳችን ነች። ሆኖም እኔ እንደማምነው ከእግዚአብሔር ዘንድ ዘላለማዊ ደህንነትን ለማግኘት ሃይማኖትን መለወጥ፣ የሃይማኖት ወግ አክራሪ መሆን አስፈላጊ አይደለም ብዬ አምናለሁ። እግዚአብሔር በፍፁም ልባችሁ ከፈለጋችሁኝ ታገኙኛላችሁ ብሏል (ኤርምያስ 9፡13)። ይህም እርሱ የፈጠረውን የሰውን ልጅ ሁሉ ይመለከታል፡፡ ስለዚህ የሙስሊም ሃይማኖት ተከታይ ወይንም ክርስቲያን በፍፁም ልቡ እግዚአብሔርን ከፈለገው እውነተኛውን አንድ እግዚአብሔርን ያገኘዋል፣ ይተዋወቀዋል ብዬ ነው የማምነው፡፡ ግን መፈለጉ በፍፁም ልብ መሆን ይገባዋል። ይህን አስመልክቶ የሃይማኖት ክርክርና ፉክክር ሰዋዊ ነው እንጂ መንፈሳዊ ሊባል አይችልም። ለቅርስ መቆርቆር አንድ ነገር ነው፡፡ ግን “እግዚአብሔር የእኔ ቤተ አምልኮ ውስጥ ብቻ ነው ያለው” ማለት እግዚአብሔርን መወሰን ነው። ዋነኛው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ልባችን ነው። ሥርዓተ ሃይማኖት ሁለተኛ ነገር ነው፡፡
ግዮን፡- ብዙ ሰው ይኽን ሃሳብ አይደግፈውም፡፡ በዶክትሪን የሚለያዩ ቤተዕምነቶች ጋር አምልኮ መፈጸምስ የሚጋጭ ነገር የለውም?
ኢንጂነር ፍሥሐ፡- የክርስቲያን ሃይማኖት ባሕላዊ መሠረት አለው፡፡ እነደ የባሕሉ አንዳንድ ልዩነቶች ይኖራሉ ፤ አሉ። ዋናው ግን ፀሎተ ሃይማኖት የተባለውን የሦስቱም ዋና ዋና ክርስቲያን ሃይማኖቶች (ኦርቶዶክስ፣ ካቶሊክ እና ፕሮቴስታንት) መሠርታዊ እምነት ቀኖና “ፀሎተ ሃይማኖት” የተባለው በግዕዙ “ነዓምን በአሐዱ አምላክ” ብሎ የሚጀምረው ነው። በዚህ መሠረታዊ ዶክትሪን ውስጥ መበላለጥና መፎካከር አይኖርም፡፡ እንደተናገርኩት ግንኙነታችን ቀጥታ ከእግዚአብሔር ጋር ከሆነ ዋናው ቤተ መቅደስ ልባችን ነው።
ግዮን፡- አሁን በምን ዐይነት ሥራ ላይ ይገኛሉ? ሀገርንና ወገንንስ የሚጠቅም ምን ለመሥራት አቅደዋል?
ኢንጂነር ፍሥሐ፡- አሁን በግሌ ለሕክምና የሚያገለግሉ ቴክኖሎጂዎች (ባዮሜዲካል ኢንጂነሪግ) ጋር የተያያዘ አማካሪ ነኝ፡፡ በዚህ ቴክኖሎጂ ምን ምን መሥራት እንደሚቻል እንዴት ማሻሻል እንደሚቻል ለትልልቅና ለአዲስ ጀማሪ ተቋሞች ምክርን እሰጣለሁ። ብዙውን ጊዜ ከቤቴ ሆኜ ነው በየቦታው ለተሰብሰቡ ወይንም ለግለሰቦች በኮምፒውተር (እንደ ዙም) ማማከር የምሠራው፡፡
ሌላው ደግሞ አሁን “የፍሥሐ አጥላው ወልደ ዮሐንስ ፋውንዴሽን” ተብሎ በአሜሪካ ተቋቁሞ ኢትዮጵያም ቅርንጫፍ ባለው ድርጅት ላይ እየሠራሁ ነው፡፡ የፋውንዴሽኑ 3 ዋና ዋና ሥራዎች 1ኛ) በኤኮኖሚ ዝቅተኛ የሆኑና የተጎዱ ኢትዮጵያውያንን በተለይም ሕፃናትንና ብቻቸውን የሚያሳድጉ ወጣት እናቶችን የሚረዱ ማኅበራትንና ድርጅቶችን መርዳት 2ኛ) በኢትዮጵያ ፊደላት ኮምፒውተር ላይ የሚሰሩ መተግበሪያዎችን የሚሰሩ ወጣቶችን ማበረታታትና በገንዘብ መደገፍ 3ኛ) የኢትዮጵያን ትክክለኛ ታሪክና ቅርስ ላይ ለሚሰሩ ተማሪዎች ስኮላርሺፕ በመስጠት መደገፍና ማበረታታት ነው።
ግዮን፡- ኢትዮጲክ አዋርድ መቼ ተመሠረተ? እስከሁን ምን ዐይነት ፕሮግራሞችን አዘጋጅታችኋል? ለምንስ ነበር የተጀመረው? የሽልማት ፕሮግራሙስ የት ነው የሚዘጋጀው?
ኢንጂነር ፍሥሐ፡- “ኢትዮጲክ አዋርድ” የሚባለው ከስያሜው ብንነሳ የፊደላችን ስም “ኢትዮጲክ” የሚባል ስለኾነ ሥያሜውን ልንጠቀምበት ችለናል፡፡ እንደ ስሙ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ቋንቋዎች የሚመለከት ነው፡፡ በዚህ ላይ መተግበሪያዎችን ለሚሠሩ ወጣቶች ማበረታቻ ተብሎ የተመሠረተ ሽልማት ነው፡፡ እዚህ አሜሪካን ሀገር ወጣቶች አንድ መተግበሪያ ሠርተው በተለያዩ መንገዶች በማስተዋወቅ ገንዘብ ያገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ይህ ነገር ብዙ ስለሌለ ይህን መሰል መተግበሪያ የሚሠሩ ወጣቶችን ለማበረታታት ይህን ውድድር በፋውንዴሽን መንገድ አዘጋጀን፡፡ በፍሥሐ አጥላው ፋውንዴሽን በኩል ይህን አዋርድ 2021 ላይ ነው የጀመርነው፡፡ በወቅቱ ኮቪድ ስለነበር ወደ 2022 ተሸጋግሮ ነበር የመጀመሪያው ዝግጅት ተካሄደው፡፡ አሁንም ለ2023 አዋርድ እየተዘጋጀ ነው፡፡ በጥቅሉ ፋውንዴሽኑ መተግበሪያ ለሚሠሩ ወጣቶች መሸለም ሥራው ነው፡፡ ባለፈው በነበረው ዝግጅት በገንዘብ ደረጃ ከ50ሺ እስከ 200ሺ ድረስ አከፋፍለናል፡፡ ሽልማቱ በየዓመቱ ሚደረግ ነው፡፡ ኢንጂነር ተረፈ ራስ ወርቅን የሚባሉ የመጀመሪያውን የአማርኛ ቴሌ ታይፕ ራይተር የሠሩ በጃንሆይ ጊዜ የተሸለሙ እሳቸውን በመጥራት ባለፈው ዓመት የመጀመሪያ መርሓ ግብራችንን አድርገናል፡፡ ፕሮግራሙ የተካሄደው ጁፒተር ሆቴል ነበር፡፡ ዳኞቹን በኦንላይን ማግኘት የምንችል በመኾኑ 13 ሰዎች ተመርጠው ባለፈው ዓመት ተሸላሚ ኾነዋል፡፡
ግዮን፡- ፋውንዴሽኑ ከዚህ ውጪ ምን የሚሠራው ነገር አለ?
ኢንጂነር ፍሥሐ፡- ፋውዴሽኑ በሁለተኛ ደረጃ “የአምላክ ልጆች ፋውንዴሽን” የሚባል ድርጅትን በመርዳት የጎዳና ተዳዳሪ ወጣት ሴት ልጆችን እየሰበሰበ የአራስ ቤት ብሎ የማረስ ተግባር ያከናውናል፡፡ ይኽንንም የቦርድ አባሎቻችን በየዓመቱ ውጤቱን እያዩ ለመርዳት ታስቧል፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ይህን መሰል ችግር በስፋት ስላለ አሁን ላይ በቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በኩልም የቦታ ወይንም የቤት ድጋፍ እንዲሰጣቸው እየተሞከረ እንደሆነ ተረድቻለሁ፡፡
በጠቅላላው እኔ በድርጅቴ በኩል የማደርገው በሌሎች ብዙ ብዙ ዓይን ሲታይ ትልቅ ነገር ሆኖ አይደለም። ሰው ለመርዳት የግድ ሚሊየነር መኾን አያስፈልግም፡፡ እኔ የምከተለው ጌታ መድኃኔዓለም ክርስቶስ “ተርቤ አበላችሁኝ፣ ተጠምቼ አጠጣችሁኝ፣ ስታመም ጠየቃችሁኝ፣ ስታረዝ አለበሳችሁኝ” ብሎ በሰጠን ቃል ግንዛቤ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ስለ ስሙ የምናደርገው ስለ ታዘዝን ብቻ ሳይሆን ለሱ ያለንን ፍቅር ለመግለፅም ነው። እሱም ምሳሌ ሲሰጠን ያቺ ሁለት ሳንቲም የሰጠችው መበለት ስጦታዋ ከሁሉም የላቀ እንደሆነ ምሳሌዋም እስከ ዓለም መጨረሻ ድረስ እንደሚጠቀስ ነግሮናል።
ግዮን፡- ስለነበረን ቆይታ በአንባቢያን ሥም እናመሠግናለን፡፡