የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በእነክርስቲያን ታደለ የክስ መዝገብ ላይ “ክሳቸውን ይከላከሉ ወይስ በነፃ ይሰናበቱ?” የሚለውን ዋና ብይን ለመስጠት መደበኛ ቀጠሮ ለመቁረጥ ፈቃደኛ ሳይሆን መቅረቱን የተከሳሾቹ ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
ፍርድ ቤቱ ለብይኑ መደበኛ ቀን ባይቆርጥም፣ ተከሳሾቹ በማረሚያ ቤት እየተፈጸመብን ነው ስላሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ግን የማረሚያ ቤቱ ኃላፊ ማብራሪያ ይዘው እንዲቀርቡ ለሰኔ 16 ቀን 2018 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ጠበቃ ሰለሞን ሰኔ 3 ቀን 2018 ዓ.ም ስለነበረው የችሎት ውሎ እንደተናገሩት፣ ተከሳሾቹ “ፍርድ ቤቱ ለብይኑ ለምንድነው ቀጠሮ የማይሰጠን?” ሲሉ ላቀረቡት ጥያቄ፣ ችሎቱ ሲመልስ “ጉዳዩ ሊያልቅ የተወሰነ ነገር ስለሆነ የቀረው ይሄ ነው የሚባል ቀን አልወስንም” ማለቱን ገልጸዋል።
በመሆኑም ጉዳዩ ሊጠናቀቅ የተቃረበ በመሆኑ፣ ፍርድ ቤቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቱን ለመስማት በሰየመው በዚሁ “በሰኔ 16 ቀን ላይ ዋናው ብይን ሊገለጽ ይችላል፤ ካልሆነ ግን ከዛ በኋላ ባሉት ቀናት ልናሰማ እንችላለን” የሚል ውሳኔ ማስተላለፉን ጠበቃው ጠቅሰዋል።
በዕለቱ ተከሳሾቹ “ጉዳዩን የሚከታተሉ የሚዲያ አካላት እና ቤተሰቦቻችን ቀኑን ቀድመው ማወቅና መስማት ስላለባቸው መደበኛ ቀጠሮ ሊሰጠን ይገባል” የሚል ጠንከር ያለ ጥያቄ ቢያነሱም፣ ችሎቱ ግን ተጨማሪ ቀጠሮ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆን “በሰኔ 16 ወይም ከዚያ በኋላ ብይኑን እናሰማለን” በማለት የዕለቱን ችሎት ማጠናቀቁ ታውቋል።
አዲስ ማለዳ
