ብልጽግና ወይስ ሕልውና?

Date:

ዶ/ር ይርጋ ገላው

በዚህች ጽሑፍ ላይ የማተኩረው በአማራ ማንነታቸው ምክንያት ሰብዐዊ መብታቸው የሚጣስ ሰዎች ላይ ያሉ እሳቤወችን ለመሞገት ነው። በግሌ የብሔርተኝነትንም ይሁን የአሃዳዊ አንድነትን ፖለቲካ የምቃወምባቸው ብዙ ምክንያቶች አሉኝ። የሃገራችንን የፖለቲካ፣ የማኅበራዊና የኢኮኖሚያዊ ስሪት የማየው በገጠርና በከተማ የሕይወት ተቃርኖ ላይ የተመሰረተ ሃገርበቀል የልሂቃን ቅኝ አገዛዝ እንደሆነ አድርጌ ነው። ይህንን ሃሳቤን ኔቲቭ ኮሎኒያሊዝም (Native Colonialism) በተሰኘ መጽሃፍ ጽፌአለሁ፣ በልዩ ልዩ መገናኛ ብዙሃኖችም ምልከታየን ለማጋራት ሞክሬአለሁ፤ ወደፊትም የምለው ይኖረኛል። አሁን የማተኩረው ግን በዚህ ላይ አይደለም። አሁን የማተኩረው በማንንት ላይ የሚደርሰው ጥቃት የፖለቲካ ጉዳይ ብቻ ተደርጎ በመታየቱ በጥቃቱ ሰለባወች ላይ ብቻ ሳይሆን በመላ ሃገሪቱ ላይ ብሔርተኝነትን ሽፋን ያደረገ ወንጀልና አፓርታይድን የሚመስል የአድልወ ስርአት እየፈጠረ መሆኑን ለማሳየት ነው።

በዚህ ጽሑፍ ላይ በምሳሌነት የማነሳውን በአማራ ማንነት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በሌሎች ማንነቶች ላይ ከሚደርሰው ጥቃት ለየት የሚያደርገው ጉዳይ አለ። አማራ የሕዝብ መጠሪያ ብቻ አይደለም። ወደኋላ አካባቢ እንደማሳየው፣ ላለፉት 30 አመታት አማራነት የተወሳሰበ ትርጉም ያለው ማንነት እንዲሆን ተደርጓል። ጉራጌም ይሁን ኦሮሞ፣ ትግሬም ይሁን አማራ፣ ገበሬም ይሁን ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ቄስም ይሁን ሼክ፣ ኦህዴድም ይሁን ብዐዴን፣ ኢዜማም ይሁን ባልደራስ፣ የኦሮሞን ወይም የትግራይን የብሔር ትርክት ከተቃወመ፣ የኢትዮጵያዊነት ወይም የአንድነት ፖለቲካ አራማጅ ከሆነ ወይም የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ከሆነ ‘ዐማራ” የሚለው ስያሜ እንደየሁኔታው ሊጫንበት ይችላል። ለምሳሌ ፕሮፌሰር አሰፋ ጃለታ በሕዳር ወር በጻፉት ጽሁፍ ላይ በአማራ ልሂቃን ተጽዕኖ ይመራሉ ብለው የዘረዘሯቸው የፖለቲካ ሃይሎች ኦህዴድን፣ ኢዜማን፣ ባልደራስን፣ አብንንና የአማራ መንግስትን ያጠቃልላሉ። ይህ የሚያሳየን ከፖለቲካ ውጭ የሆነው ድሃ የአማራ ተወላጆች ከነዚህ የተለያየ የፖለቲካ አቋምና ፍላጎት ካላቸው ሃይሎች ጋር ተደምረው በጨፍላቂነት፣ በነፍጠኛነት፣ በአሃዳዊነትና በዱሮ ስርዐት ናፋቂነት እየተፈረጁ እንደፖለቲካ ጠላት በመቆጠር ላይ መሆናቸውን ነው።

ይሄው ምሁር ጠቅላይ ሚንስትሩን ሳይቀር “አማራ ሆነዋል” ያሉበትን ምክንያት ሲያስረዱ እንዲህ ይላሉ፡-

Abiy’s father is Oromo. But he was raised by his Amhara mother, a fact that he has used extensively. Considering his cruelty against the Oromo who embraced him at the beginning, most Oromos now think that his close affinity with his mother shaped his values, philosophy, ideology, and culture.

ጸሃፊው የሚሉት ‘ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በአባታቸው ኦሮሞ ናቸው። ታዲያ በኦሮሞ ላይ ጨካኝ የሆኑት ለምንድን ነው ለሚለው ጥያቄ ብዙ ኦሮሞወች የሚሰጡት መልስ የአብይ እሴቶች፣ ፍልስፍናወች፣ ርዕዮተ አለምና ባህል አማራ በሆነችው እናታቸው በኩል ያገኙት ስለሆነ ነው የሚል ነው። ይህ የሚያሳየን አንድ በኦሮሞ ጥናት ትልቅ ስም ያላቸው ምሑር “most Oromos” ብለው ስለብዙ ኦሮሞዎች አስተሳሰብ የሰጡን ሥዕል ምን እንደሚመስል ነው፡፡ ይህም፣ ወልዳ የምታሳድግ እናት ሳትቀር አማራ ከሆነች ልጇን በኦሮሞ ላይ ጨካኝ የሚያደርግ እሴት ልታወርሰው ትችላለች ብለው እንደሚያስቡ ነው። በበኩሌ ይህ የልሂቃን እንጅ የተራው ኦሮሞ ሕዝብ እምነት ነው ብየ አልገምትም። ሆኖም ይህ አይነት እሳቤ ጋር በተያያዘ የአማራ ማንነት ባላቸው ዜጎች ምን ተደረገ የሚለውን እንይ። ኢሕአዴግ በ1983 ዓ.ም ሥልጣን ከያዘ ጀምሮ እስከአሁን ድረስ በአንድ ቦታ ብቻ ሳይሆን በልዩ ልዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የአማራ ማንነት ያላቸው በርካታ ሰዎች የአሰቃቂ ግድያ ሰላባ ሆነዋል። ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል። ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ ሰባዊ ክብራቸው ተደፍሯል፤ ስነልቦናቸው፣ ቤተሰባቸው፣ ስራቸው፣ ተስፋቸው ተሰባብሯል።

ይህ ጥቃት ፖለቲካዊ ምክንያት ቢኖረውም እንደከባድ ወንጀል ተውስዶ አጥፊወች አልተቀጡም፣ ተጠቂወች ፍትህ አላገኙም። ሌላው ቀርቶ የመንግስት ዋና አጀንዳ አልሆነም። ምድሪቱ በአማራ ላይ ወንጀል ፈጽሞ በነጻነት መኖር የሚቻልባት ሃገር ሆናለች። ይህም በፖለቲካ ምክንያት የሚፈጸም ወንጀል ከሕግ ቁጥጥር ውጭ ነው የሚል አደገኛ አንድምታ ፈጥሯል። ይህ በአማራ ማንነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል እንደምሳሌ ባነሳሁት የአማራ ማንነት ላይ ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ሰው ላይ ሊፈጸም የሚችልበትን ቅድመሁኔታ የሚያመቻች ነው። ይህም _ ፖለቲካ _ ራሱ ማንነትን ፈጥሮ፣ እራሱ ወንጅሎ፣ እራሱ ፍርድ የሚሰጥበት አደገኛ ስርአት የመላ ሃገሪቱ የፖለቲካ ባህል ሆኖ ማደጉን ያሳየናል። እንዲህ አይነት ስርአት ብዙ ቦታ ላይ ተከስቷል። በአይሁዶች፣ በጥቁሮች፣ በፍልስጥኤማውያን፣ በደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች፣ በኩርዶች፣ በዳርፉር ሱዳኖች ወዘተ፣ አስከፊ የንጹሃን መብት የተጣሰባቸው ቦታወች ሁሉ ዋና የሚያመሳስላቸው ጉዳይ በማንነት ላይ ያነጣጠረ ጥላቻና ውንጀላ ሰለባ መሆናቸው ነው። ከሰዎች ማንነት ላይ ያልመረጡትንና ያልተስማሙበትን ትርጉም ጭኖ፣ ከሌሎች የሚለያዩበትን የፖለቲካ አጥር ሰርቶ፣ ንጹሃንን የሚያስፈጅና የሚጨቁን ፖለቲካ ከአፓርታይድ አይነት አድሏዊነት እስከ ርዋንዳ አይነት አጠቃላይ ዘር የማጥፋት ወንጀል ድረስ የሚደርስ ክፋት ለመፈጸም አመቺ ነው። ይህ ስራት ደም በማፍሰስ የመሳሰሉ ወንጀሎች እየዳበረ ከሄደ በኋላ በማንነት የሚጠቁ ሰዎችን በሃሳብ መርዳት ወይም መወዳጀት ሳይቀር ወንጀለኛ እስከማድረግ ያደርሳል። ተጠቂወቹን ለመጠቃታቸው ምክንያቱ የራሳቸው ጥፋት ነው ብሎ ያሳምናል። በውይይት በምክክር ሊቀለበስ አይችልም።

የማንነት ጥቃትን እንደከባድ ወንጀል ለማስተናገድ መደረግ ያለባቸው በርካታ ጉዳዮች ቢኖሩም በዚህ ጽሁፍ ላይ የማተኩረው መደረግ የሌለባቸው ጥቂት ጉዳዮች ላይ ብቻ ይሆናል። ከእነዚህም ውስጥ “አማሮች ላይ የመብት ጥሰት የሚደርሰው በተሳሳተ የታሪክ ትርክት ነው” የሚሉትንና “ግድያው በዜግነት እንጅ በብሔር ማንነት ሊጠራ አይገባውም” የሚሉት ይገኙበታል። ዋናው ክርክሬ እነዚህ እሳቤወች የሰብዐዊ መብትን ጥያቄ ከርዕዮተአለም ጥያቄ ጋር በማደበላለቅ፣ ዘር ተኮር ጥቃትን ተራ ወንጀል አስመስሎ በማቅረብ፣ የመንግስትን አለማቀፋዊ ሃላፊነት በማሳነስ፣ ወንጀል የፖለቲካ አላማ ማስፈጸሚያ መሳሪያ ሆኖ እንዲቀጥል ምቹ ሁኔታ ይፈጥራሉ። በተጨማሪም አሁን ስራ ላይ ባለው የፖለቲካ አደረጃጀትና መዋቀር ውስጥ ዜግነት ብቻውን ስለማይከበር የአማራ ሕዝብ ከሕግ ከለላ ውጭ ራቁቱን እንዲቀር ያደርጉታል። በመደምደሚያየም የሃገራችንን እጣ ፈንታ ወደተሻለ አማራጭ ለማምጣት፣ በርዕዮተአለም ሳቢያ በአማራ ላይ የሚደርሰውን የሰብዐዊ መብቶች ጥሰት በስሙ መጥራትና ማውገዝ እጅግ ትንሹ ግን የመጀመሪያው እርምጃ ነው። ብዙ ሕዝብ ተፈናቅሎ፣ ተርቦና እየተገደለ ባለበት ባሁኑ ወቅት፣ ከፖለቲካ ይልቅ ለሕዝቦች ሕልውና ቅድሚያ የማይሰጥ ስርዐት በፍጹም ለሕዝብ ደንታ ቢስ ነው። በዚህ አይነት ስርአት ውስጥ ሕግ ፖለቲካውን ስለማይገዛው የዜግነትም ሆነ የብሔርተኝነት ፖለቲካ ለአማራ ሕዝብ ዋጋ የለውም። ተፈጥሯዊ ሰብዐዊ መብትን ከፖለቲካ ርዕዮተአለም በመለየት የሕልውና ጥያቄ ከሕግ በላይ ሆኖ ቅድሚያ ካልተሰጠውና በመብት ረጋጮች ላይ ህጋዊ ተጠያቂነት ካልተረጋገጠ፣ አግላይና አክራሪ የሆነው የብሔርተኝነት ትርክት ወንጀሉ ተደብቆለት ስለሚቀጥል፣ በሂደት የመንግስት ግልጽ ባህሪ ሆኖ በፖሊሲ ጭምር መገለጹ እንደማይቀር የበርካታ ሃገሮች ልምድ ያሳየናል።

አንዳንድ ሰዎች በአማራ ማንንት ላይ የሚደርሰው በደል “‘በተሳሳተ የታሪክ ትርክት” የተፈጠረ ነው ብለው ሲናገሩ ይደመጣሉ። ከዚህ በመነሳትም ታሪክን ለማረም ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። ይህ ጥረት መጥፎ ባይሆንም ‘የታሪክ ስህተት’ የሚለው አቀራረብ ችግሩን በቀላሉ ሊታረም የሚችል እንደሆነ አድርጎ ስለሚያቀርብ አዘናጊ እንጅ ገላጭ ምክንያት አይደለም። ምክንያቱም የታሪክ ስህተት ቢሆን ኖሮ የሚፈታበት ቦታ ዩንቨርስቲ ውስጥ ወይም የታሪክ ጥናት ክርክር መድረክ ላይ ይሆን ነበር። ችግሩ የፖለቲካ እምነት (ርዕዮተአለም) ጉዳይ እንጅ የታሪክ አረዳድ ስህተት አይደለም። በታሪክ አረዳድና በርዕዮተአለም መካከል ያለውን ትልቅ ልዩነት በደንብ መገንዘብ ስለሚያስፈልግ ስለርዕዮተአለም ትንሺ ልበል።

ርዕዮተአለም፣ እያንዳንዳችን ራሳችንን እንደአንድ የማህበረሰብ አባል በመቁጠር ሃገር የምንገነባበት፣ ወይም የምናፈርስበት፣ ወይም በጋራ እንድንኖር የሚያደርገን የፖለቲካ እምነት ነው። ዋና አላማው አንድ የሚያደርገን ቋሚ የፖለቲካ እምነት መፍጠር ስለሆነ፣ ትኩረቱ እውነተኝነት ላይ አይደለም። ርእዮተአለም በውሸት ወይም ፈጠራ ላይ የተመረኮዘ ትርክትን እንደመነሻ ሊወስድ ይችላል። ለምሳሌ በነገስታቱ ዘመን ሕዝቡ በተሰጠው የስልጣን ተዋረድ መሰረት ጌቶቹን እያከበረ ለመኖር መሪወቹ ከፈጣሪ እንደተቀቡ አድርጎ ማመን ነበረበት። ይህ እምነት እውነት ቢሆንም ወይም ባይሆንም ለብዙ ሺ ዘመናት ሃገር ገንብቶ ለመኖር የሚያስችል ውጤት ነበረው። በዚያ ዘመን ይህንን እምነት የሚቃወም እንደ ከባድ ወንጀለኛ ይቆጠር ነበር። ርዕዮተ አለም ከሀይማኖት የሚለየው ትኩረቱ ፖለቲካ ላይ ስለሆነ ብቻ ነው። ርዕዮተአለም የማህበረሰብ የጋራ እምነት ስለሆነ፣ ለርዕዮተአለሙ ታማኝ የሆኑ ሰዎች ታማኝነታቸውን የሚያስመሰክሩት የርዕዮተአለሙን ጠላቶች አምርረው በመታገል ወይም በማጥፋት ነው። በ1966ቱ አብዮት በነገስታቱ መለኮታዊ ስልጣን ላይ የተመሰረተው ርዕዮተአለም ተሻረ። ከዚያ በኋላ፣ እስካሁን የምንጣላበት ዋና ምክንያት ሁላችንንም የሚያስማማ የጋራ ርዕዮተአለም መፍጠር ባለመቻላችን ነው።

ታሪካችን ውስጥ ጥፋትም በጎነትም ሞልቷል፤ ነገስታቱ መላእክትም ሰይጣናትም አልነበሩም፣ እንደእኛ ሰዎች ነበሩ። ሆኖም ፖለቲከኞች ከታሪክ ውስጥ የሚፈልጉትን መርጠው ወይም ፈጥረው የፖለቲካ እምነት ወይም ርዕዮተአለም ይሰራሉ። ርዕዮተአለም ፖለቲካዊ ሃይማኖት ነው። በውስጡ አክራሪም ለዘብተኛም አማኞች ስለሚሳተፉበት እንደመሪወቹ ለዘብተኛም ጽንፈኛም ባህሪ ይንጸባረቅበታል። የርዕዮተአለም አላማ የዱሮውን ታሪክ ለመቀየር ሳይሆን መጭውን ጊዜ ለመቆጣጠር የሚያስችል የተደራጀ ሃይል ማሰባሰብ ነው። እስካሁን ባለው ልምድ፣ ይህንን የተደራጀ ሃይል የሚያሰባስብበት ዋናውና አቋራጩ መንገድ ተከታዮቹን ሊያስተባብር የሚችል የጋራ ጠላት በመፍጠር ነው። በፖለቲካው አለም ውስጥ ሰዎች የጋራችን የሚሉት ዋና እውነታ የጠላታቸው ማንነት ሲሆን፣ ይህ ጠላታቸው የፖለቲካ አብሮነታቸውን ለማስቀጠል እጅግ አስፈላጊ ነገር ይሆናል። ይህ የጋራ ጠላት ከተፈጠረ በኋላ ተከታዮቹ የራሳቸውን የፖለቲካ ሰብዕና፣ ታሪክና አጠቃላይ የማንነታቸውን ትርጉም ሁሉ መገንባት የሚጀምሩት ጠላት ካሉት ማንነት በሚያርቅና በሚቃረን አግባብ ይሆናል። አንድነታቸውን፣ ቆራጥነታቸውንና ታማኝነታቸውን የሚያረጋግጡት የጋራ ጠላት ያሉትን በመፈረጅ፣ በማግለል፣ ባለመተባበር፣ በማጥላላት፣ በመስደብ፣ በመግደል፣ በማፈናቀል ሊሆን ይችላል። ይህንን የሚያደርጉት በተሳሳተ የታሪክ ትርክት ሳይሆን በራሳቸው የውስጥ ፖለቲካ ፍላጎት በመመራት ሆን ተብሎ በተመረጠና በተቀናባበረ ትርክት ይሆናል። ስለዚህ ታሪካዊ ትርክትን እንደግባት ቢጠቀምም፣ ርዕዮተአለም ተከታዮቹን በስሜት ለማታገል የሚፈጠር የፖለቲካ እምነት ስለሆነ የታሪክ ማስረጃ በማቅረብ እምነቱን ማስቀየር አይቻልም። ዛሬ አማራ ተብለው የሚሞቱት ሰዎች ከነገስታቱ ዘመን ጋር የሚያገናኛቸው ምንም አይነት የስልጣን ወይም የኢኮኖሚ ትስስር እንደሌለ ገዳዮቹም አይጠፋቸውም።

ከዚህ አንጻር፣ በአማራ ላይ የሚደርሰው ጥቃት የታሪክ ስህተት ሊባል የማይገባበት ብዙ ምክንያቶች አሉ። ከኢሃዴግ የስልጣን ዘመን ጀምሮ፣ የአማራን ሕዝብ ብቻ ነጥሎ ከነገስታቱ ዘመን ጋር ያገናኘው የጨቋኝነት ትርክት የብሔር ፖለቲካ ዋና ማደራጃ ርዕዮተአለም አካል ሆኗል። ርዕዮተአለም ደሞ ከላይ እንዳልሁት በባህሪው ከታሪክ ይልቅ ለሃይማኖት ይቀርባል። በታሪክ ትንታኔ አይቀየርም። ምክንያቱም ዋናው አላማው ትናንትን ሳይሆን ነገን ለመቆጣጠር የሚያስችል ስርዐት ለመፍጠር ሃይል ማሰባሰብ ነው። በጥላቻ ላይ የተመሰረተ ርዕዮተአለም ከተፈጠረ በሗላ፣ አማራወች “አጥፍታችኋል” የሚባሉትን ሁሉ አሜን ብለው ቢያምኑ እንኳን፣ ጥላቻው የባህል የፖለቲካ፣ የተቋማትና የሕግ መሰረት ከያዘ በኋላ ርዕዮተአለሙን ማፍረስ ማለት የተፈጠረውን የሃይል ስብስብ የመበተን ያህል ከባድ ይሆናል። ምክንያቱም በብሔር ማንነት ብቻ የተደራጀ ፖለቲካ የብሔር ጠላት ያስፈልገዋል። በመደብ ማንነት የተደራጀ ፖለቲካ የመደብ ጠላት

ያስፈልገዋል። በጥቂት ግለሰቦች ስብከት፣ የታሪክ ማስረጃ በመደርደር፣ ወይም ለችግሩ እውቅና በመንፈግ ሊቀየር አይችልም። የአንድ ፖለቲካ ለዘብተኛነትና አክራሪነት የሚለካው ‘ጠላት’ ብሎ የፈረጀውን አካል በሚያስተናግድበት አግባብ ነው። ጠላቱን ሊደራደረውና ሊወዳደረው ከተነሳ (በሰለጠኑት ሃገሮች እንደሚታየው) የሚያስፈልገው የሃሳብ ትግል ነው። የሚገድል፣ የሚያፈናቅል ከሆነ (በእኛ ሃገር እንደሚታየው) የሚያስፈልገው የሕልውና ትግል ነው።

ከላይ እንዳልሁት ጠላትን በመፍጠርና በማጥቃት ግለቱን ጠብቆ የሚጓዝ ርዕዮተአለም በሕይወት ለመቀጠል ሲል የራሱን ለዘብተኛ አባላት ጨምሮ ማንኛውንም ተቃዋሚ ሰው በጠላትነት መፈረጁንና ማጥቃቱን ይቀጥላል።። በዚህ ሂደት መጨረሻም ራሱን በራሱ የሚያጠፋበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። በአክራሪ ርዕዮተአለም ሽፋን የሚፈጸመውን ወንጀል በሕግ መዳኘት ካልተቻለ የሚፈሰው ደምና የሚፈጸመው ወንጀል እንደጀግንነትና ድል ስለሚቆጠር የብዙ ሰዎችን ጭፍን ድጋፍ ያገኛል። ድጋፍ ባያደርጉም ዝም የሚሉ ሰዎች በዝምታቸው ወንጀሉ የተለመደና መፍትሄ የለሽ ሆኖ በሕዝብ እንዲታይ ያደርጉታል። ይህ የቅቡልነት ሂደትም (ኖርማላይዜሽን) ዛሬ በሁሉም አለም ላይ በጥቁሮች ላይ የሚደርሰው የዘር መድሎ ትክክል ባይሆንም የተለመደ ሆኖ እንደቀረው ሁሉ፣ በአማራ ላይ የሚደርሰውም ጥቃት ትክክል ባይሆንም ሊወገድ የማይችል ድርጊት ሆኖ እንዲቀጥል ያደርጉታል።። በተለይም በሃገርቤትና በውጭ ወንጀሉን የሚያድበሰብሱ ወይም ምክንያታዊ የሚያስመስሉ ትርክቶች (አሁን እንደሚታየው) ከተሰራጩ፣ መንግስት የርዕዮተአለሙን አክራሪ ባህሪ ከመቀየር ይልቅ የራሱን ባህሪ ለአክራሪወቹ በሚመች መንገድ ማስተካከል ይጀምራል። ጥቃቱን በመፍቀድና በማስፈጸም ደጋፊ ያበዛበታል። ለአክራሪወቹ አባላት ስልጣን ማደል ይጀምራል። በሂደትም አክራሪነትን የሚደግፉ ሰዎች ስልጣን ላይ ይበዙና በመንግስት ፖሊሲና ተቋማት ውስጥ የአክራሪወቹ አድሏዊ ፍላጎቶች በስውር ብቻ ሳይሆን በግልጽ መንጸባረቅ ይጀምራሉ። ያኔ የጥላቻ ርዕዮተአለም የሙስናና የህገወጥነት ጭምብል ይሆናል። እዚህ ላይ የአለማቀፉ የገንዘብ ስርዐት ባህርይም ለዚህ አስተዋጾ ያደርጋል።

አንዳንድ የሃገራችን የፖለቲካ ልሂቃን የምዕራቡን አለም ዲሞክራሲና የሊበራሊስዝም ፖለቲካ እንደጥሩ ልምድና አራያ መከተላቸው ትክክል አይደለም። የካፒታሊዝም ስርዐት በተለይም አሁን ያለው የኒዮሊበራሊዝም ወይም ቴክኖፊውዳሊዝም ስርዓት ካፒታል ወይም ካፒታል የሚፈልገው ክህሎት የሌላቸውን ሰዎች እንደሸክም እንጅ እንደሰው አይቆጥራቸውም። ለካፒታሊዝም ጥቅም የማይሰጡ ሰዎች የያዙትን የተፈጥሮ ሃብት ለካፒታል አስረክበው እንዲለቁ ይፈልጋል። ሰወቹን ግን አይፈልጋቸውም። ይህ የካፒታሊዝም ባህሪ አፍሪካ ውስጥ የእርስበርስ ግጭትን (ዋርሎርድ ፖሊቲክስ) ለራሱ መጠቀሚያ ለማድረግ ያልማል። ለምሳሌ አፍሪካውያን አብዛኛው ሕዝባቸው ለካፒታሊዝም የሚጠቅም ስላልሆነ የሰለጠነው አለም የስጋት ምንጭ ናቸው ብለው ማመን ከጀመሩ ቆይተዋል። ትኩረታቸው የራሳቸውን ጥቅም የሚያስከብር የጸጥታ ፖሊሲ መከተል ሲሆን ለዚህ አላማቸው ከእርዳታ መስጠት እስከ ጦር ሰፈር ምስረታ ድረስ ይሰራሉ። ባራክ ኦባማ በአህጉሪቱ አፍሪኮም በሚል አደራጅቶት የሄደው 36 የጦር ሰፈር ሰብዐዊ መብትን ለመጠበቅ አይደለም። በቅርቡ የአለማችን አንደኛ የመሬት ከበርቴ የሆነው ቢልጌት የአፍሪካ ሕዝብ መብዛት የአለም ሕዝብ የስጋት ምንጭ መሆኑን በግልጽ ሲናገር ሰምተናል። ቻይና የአፍሪካን ጥሬ እቃ እንዳታጣ ለመሪወቹ የፈለጉትን ሁሉ ታደርጋለች። ሰሞኑን ራሺያ 10 የሚደርሱ የጦር ካምፖችን ለመመስረት በመሯሯጥ ላይ ናት። ሌሎችም እንደ ህንድ፣ ቱርክ፣ ሳኡዲ ወዘተ አፍሪካን ለመቀራመት ይሯሯጣሉ። ይህ ሁሉ የሚያሳየን አፍሪካ ዛሬ ያለችው በበርሊን ኮንፈረንስ ዘመን ከነበረችው ሁኔታ ውስጥ መሆኗን ነው። ከዱሮው የነጮች የቀጥታ ቅኝ አገዛዝ ከአሁኑ የሚለየው የአሁኑ ድርብ ቅኝ አገዛዝ በመሆኑ ነው። ድርብ ቅኝ አገዛዝ የሚፈጠረው ነጮችና የአፍሪካ ልሂቃን የጥቅም ትሥስር በመፍጠር የሁለቱንም ጥቅም በሚያስጠብቅ ደረጃ ሕዝቡን ሲመዘብሩትና ሲያሰቃዩት ነው። ነጮቹ የሚፈልጉት ሕዝቡ የተፈጥሮ ሃብቱን ለመጠቀም በሚያስችለው አግባብ እንዳይደራጅ ማድረግ ነው። በሕግ ማስከበር ስም ረግጦ በማስተዳደርና በመግዛት ለእነሱ ኢኮኖሚ

ተፈላጊ የሆኑ የተፈጥሮ ሃብቶችን በልማት ስም እነሱ ለሚያትሙት ወረቀት (ገንዘብ) የሚለውጥ ከሕዝባዊነት ይልቅ ቡድናዊ ማንነት ያለው ስራት ይፈልጋሉ። ከአፍሪካ የሚፈልጉት መሬቷን፣ ውሃዋን፣ ማእድኗን፣ ከሕዝቧ ነጻ አድርጎ የሚያስረክባቸው አሽከር መንግስት ነው። በተለይም የሰው ጉልበት የማይፈለግበትና ሁሉንም ስራ በቴክኖሎጂ መስራት የሚቻልበት ጊዜ ላይ ስለደረስን፣ በዚህ ዘመን በህጋዊም ሆነ በህገወጥ መንገድ ድሃውን ሕዝብ ከተፈጥሮ ሃብት እየነጠለ መሬቱን ለካፒታል የሚያቀርብ፣ ለትርፍ የተቋቋመ የኮርፖሬሽን አይነት ቅርጽ ያለው ወንጀለኛ መንግስት በእጅጉ ይመቻቸዋል። ይህ መንግስት ቢዝነስ እንዲሰራ የሚፈልጉት ከግል ኩባንያወቻቸው ጋር ነው። ይህን የሚያደርጉበት አንዱ ምክንያት ራሳቸውን ከወንጀሉ ነጻ በማድረግ ለሰብዐዊ መብት የቆሙ ለመምሰልና አገልግሎቱን ሲጨርስ በሌላ መንግስት ለመተካት ነው። በኩባንያወቻቸው አማካኝነት የተፈጥሮ ሃብታችንን ሲጠቀሙ በመንግስታቸው በኩል ደግሞ ያገኘነውን የውጭ ምንዛሬ በእዳ ክፍያ ሰበብ መልሰው ይወስዱታል። ይህንን ዘዴ በኮንጎ፣ በአንጎላ፣ በቻድ፣ በዛምቢያ፣ በናይጀሪያ፣ በሱዳን፣ ወዘተ በግልጽ እየተገበሩት ነው። የእነዚህን አሳሳቢ ሁኔታወች ከእኛ ሁኔታ አንጻር በዝርዝር ለማቅረብ ሌላ ርዕስ ያስፈልጋል። ማለት የፈለግሁት ግን እስካሁን ባለው ልምድ፣ የውጭ መንግስታት ዋና ፍላጎት የራሳቸውን ጥቅም የሚያስከብር ስርዐት እንዲኖር ማድረግ ብቻ ስለሆነ አክራሪ ብሔርተኝነት ከነሱ ጥቅም ጋር ካልተጋጨ በደስታ አብረውት ይሰራሉ። እንደውም የሕዝቡን አጀንዳ ከኢኮኖሚ ላይ ሳይሆን ከፖለቲካው ላይ እንዲያተኩር ስለሚያደርግ የብሔርተኝነትን ፖለቲካ ይወዱታል።

ከላይ እንደገለጽሁት በማንነት ላይ የሚፈጸም ግድያንና መፈናቀልን የሚያህል ከባድ ወንጀል የለም። መንግስት ለማንነት ጥቃት የሚሰጠው መልስ የራሱን የመንግስትን ማንነትና ባህሪ የሚያሳይ ነው። በማንነታቸው የተጠቁ ሰዎች ከአካላዊ ጥቃቱ በላይ በቃላት የማይገለጽ የስነልቦና ስብራትና ውርደት ይሰማቸዋል። የተጠቁት በማንነታቸው ስለሆነ ማንነታቸው ዋጋ እንዳለውና እንደሚከበር የሚያሳይ እርምጃ ካልተወሰደ ዋጋቢስነትና ውርደት ይሰማቸዋል። በተለይ ጥቃቱ ሆን ተብሎ እንደእንስሣ እንደሆኑ በመቁጠር በአሰቃቂ ሁኔታ የተፈጸመ ከሆነ ሰው መሆናቸው እንዲሰማቸው የሚያደርግ አካሚ ድጋፍና እንክብካቤ ያሻቸዋል። መንግስት ይህንን የሚያደርገው የተጠቃው ማንነት የእኔም ማንነት ነው ብሎ ሲያምን ነው። ስለሆነም በማንነታቸው የተጠቁ ሰዎችን ጉዳይ ቁጥር አንድ አጀንዳ ካላደረገው የተጠቂወቹ የመኖር መብት በመንግስት አይጠበቅም ማለት ነው። ይህም ተጠቂወቹ ዝቅተኛነታቸውን እንዲቀበሉ፣ አጥቂወቹ ታሪክ ሰሪ እንዲባሉ የሚያደርግ አደገኛ መልዕክት ያስተላልፋል። በሂደትም የመንግስት ስርዐት ዋና ባህሪ ለፍትህና ለህጋዊነት ዋጋ የማይሰጥ ስለሚሆን በዚያው ልክ ዜጎችም ለመንግስትና ለህጋዊነት ዋጋ የማይሰጡ መሆን ይጀምራሉ። በንጹሃን ሰዎች ላይ የሚዘገንን ጥቃትን የሚፈቅድ ወይም የሚታገስ ህሊና ያላቸው ባለስልጣኖች ወደፊት የፖለቲካ ወይም የጥቅም ባላንጣወቻቸውን ይቅር ይላሉ ብሎ ማሰብ አዳጋች ነው። እስካሁን ባቀረብሁት ገለጻ አማራነትን በታሪክ አተረጓጎም ስህተት የተፈጠረ ማንነት አድርጎ ከማየት ይልቅ የብሔርተኝነት ልሂቃን የርዕዮተአለም ጠላት አድርገው በመሳል የተከታዮቻቸው ማታገያ ያደረጉት ማንነት መሆኑን በመገንዘብ ለዚህ የሚመጥን ምላሽ ላይ መዘጋጀት ያስፈልጋል። ይህን ምላሽ ወደፊት ከማየታችን በፊት ለሃሳብ ጥራት ይረዳል የምላቸውን ጥቂት ነጥቦች ላንሳ።

በአማራነታቸው የተጠቁ ሰዎችዜጎችናቸው ወይስአማሮች’?

ሰብዐዊነት የተፈጥሮ ስጦታ ነውና ሁሉም ሰው በሰውነቱ እኩል ነው። መንግስት የተፈጥሮ መብቶችን ለያንዳንዱ ግለሰብ የሚያስጠብቅበትን ሕግ ታሳቢ በማድረግ በተለምዶ ‘የዜግነት መብት’ ብለን እንጠራቸዋለን። ዋናው ቁምነገሩ ሰው በተፈጥሮ ያገኛቸውን መብቶች መንግስት የመጠበቅ ሃላፊነት አለበት የሚለው ነው፡፡ ይህን ሃላፊነት የሚወስድ መንግስት የሌላቸው ሰዎች፣ ዜግነት አልባ (ስቴትለስ) ሊሆኑ ይችላሉ። በማይንማር 600000 የሚደርሱ ሮሂንጋ የሚባሉ ጎሳ አባላትን መንግስት የእኔ ዜጎች አይደሉም ስላላቸው ዜግነት አልባ ሆነዋል። ይህ ሁኔታ በህንድም ተከስቷል። የሞዲ መንግስት ስልጣን ላይ ሲወጣ ህንድ የሂንዱይዝም እምነት ተከታዮች ሃገር ናት በማለት እስላሞችን ሃገር አልባ የሚያደርግና ለጅምላ ግድያ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ፖለቲካ ይዞ ብቅ ብሏል። ይህ አስተሳሰብ የኢኮኖሚ ጥቅም ያስገኘላቸው የሂንዱ ተከታዮች ሞዲን በከፍተኛ ሁኔታ በመደገፍ ላይ ናቸው። ፍልስጤማውያንም የራሳቸው ምድር ላይ ምድር አልባ ሆነው ብዙ ዘመናት እየገፉ ነው። እስራኤል የአይሁዶች ብቻ ሃገር ናት የሚለው የጽዮናዊያን ፖለቲካዊ አመለካከት ለእስራኤላውያን ጥቅም ስላለው አድሏዊ ስርአቱን ሕዝቡ በከፍተኛ ሁኔታ ይደግፈዋል። አንድን ሕዝብ ሃገር አልባ የሚያደርግ በዘር ማንነት ላይ የተገነባ ርእዮተአለም የፖለቲካ ስልጣን ካገኘ የማንነቱ ተከታዮች ስለሚደግፉት ተጠቂውን ሕዝብ የሚታደገው ምንም አይነት አለማቀፍ የፍትህ አካል የለም።

ወደሃገራችን ስንመለስ በሕግ “ኢትዮጵያዊ አይደለህም” የተባለ ስለሌለ በማንነት የሚጠቁ ሰዎች ችግር ለጊዜው የዜግነት ችግር አይደለም። አማራም ይሁን ትግሬ፣ አፋርም ይሁን ኦሮሞ ወዘተ ሁሉም ዜጎች በሁሉም የሃገሪቱ ቦታ ያለዐድልዎ የመኖር መብት እንዳላቸው በህገመንግስቱ ተደንግጓል። ሆኖም ወደተግባራዊነቱ ስንመለስ፣ ይህ የግለሰቦች መብት ከብሄሮች ሉዐላዊነት ስር ወድቋል። ህገመንግስቱን ተከትሎ በተደራጀው የብሔርተኝነት ርዕዮተአለም ሳቢያ፣ በአማራ ሕዝብ ላይ እንደዜጋ ሳይሆን እንደአማራነት የተፈጠረ ማፈናቀልና ግድያ ተፈጥሯል። ግድያው አንድ ወቅት ብቻ የተከሰተ ሳይሆን፣ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ፣ እጅግ ዘግናኝ ግፎች የተፈጸሙበትና በበርካታ ቦታወች የተከሰተ ነው። በበደኖ፣ በአርባ ጉጉ፣ በገለምሶ፣ በጋራ ሙለታ፣ በወተር፣ በሃብሩ፣ በአጋሮ፣ በአሰቦት፣ በሸቤ፣ ወዘተ በገደል በመወርወር፣ በቢላዋ በመታረድ፣ በእሳት በመቃጠል፣ በጥይት በመደብደብ አማራ ማንነት ባላቸው ላይ አሰቃቂ ግፍ ተፈጽሟል። የአገዳደል ዘዴው ራሱ በማንኛውም ንጹህ ዜጋ ላይ የሚፈጸም የተለመደ አይነት ወንጀል አይደለም። የነፍሰጡር ሴትን ሆድ ቀዶ ልጁን በማውጣት ለእናት መስጠት፣ በእሳትና ዱላ ደብድቦ መግደል፣ ህጻናትን ማረድ፣ አስከሬን ጎዳና ላይ መጎተት የመሳሰሉ የጭካኔ ድርጊቶች እንደተፈጸሙ ማስረጃወች ያስረዳሉ። ከግድያው ጀርባ በአማራነት ላይ የተዘራውን ጥላቻ ምክንያታዊ የሚያስመስሉ የትምህርት፣ የጥናት፣ የሃይማኖት፣ የሃውልት፣ የስነቃል፣ የሙዚቃና የትጥቅ እንቅስቃሴወች አሁንም አሉ። በዚህ አውድ የሚፈጸምን በደል ‘በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚደርስ በደል’ ብሎ መጥራት የመሳለቅ ያህል ነው። እዚህ ላይ አንዳንድ ሰዎች በየዋህነት ‘ግን ምን ችግር አለው ዜጋ ቢባሉ” ስለሚሉ አንዳንድ ነጥቦችን ማየት ያስፈልጋል።

አንዱ ምክንያት በብሔር ማንነታቸው የሚገደሉ ሰዎችን ባልተገደሉበት ምክንያት ዜጋ ብሎ መጥራት ማለት ገዳዮቻቸው ተራ የግድያ ወንጀል የፈጸሙ እንጅ የዘር ጥቃት ያደረሱ እንዳልሆኑ የሚያደርግ ከለላ መስጠት ነው። የሰብአዊ መብት ድንጋጌወች ሁሉ የዘር ተኮር ጥቃትን ከዜጎች ተራ ጥቃት የተለየ ትኩረት የሚሰጧቸው ብሔርተኝነትን ለማስፋፋት ፈልገው አይደለም። ጉዳዩ ከተራ ወንጀል በተለየ መልኩ አለማቀፍ ትኩረትና መፍትሄ ስለሚያስፈልገው ነው፡፡ አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ከተገደለ በኋላ ሁኔታውን አጣርቶ የኢትዮጵያ ሰብዐዊ መብት ኮሚሽን ባወጣው ዘገባ ላይ ግድያውን በሰብዐዊነት ላይ የተፈጸመ ከባድ ወንጀል እንደሆነና የዘር ማጥፋት ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል ያለውን ስጋት አስታውቋል። ይህ አይነት ወንጀል አለማቀፍ ወንጀል ነው። ወንጀሉ በኢትዮጵያዊነት ላይ ካለን የአመለካከት ልዩነት ጋር አይያያዝም። ወንጀሉ አንድን ማንነት የፖለቲካ ጠላት አድርጎ በመሳል፣ ከፖለቲካ ውጭ የሚኖሩ ድሃ ገበሬወችን ለግልጽ ጥቃት የሚያጋልጥ፣ ሰላማዊ ዜጎች በወገኖቻቸው ላይ ግፍ እንዲፈጽሙ የሚያነሳሳ ኢ-ሰብአባዊነት ነው። ምንም አይነት አላማ ቢኖረው፣ ይህ አይነት የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሰላማዊ ሰዎችን ማጥቃትከጀመረበት ከዚያች ሰአት ጀምሮ ከፖለቲካ አውድ ወጥቶ ወደአሸባሪነትና ኢሰባዊነት አውድ እየተሸጋገረ ነው ማለት ነው። ይህ የአሸባሪነት የሽግግር ሂደት ዝም ከተባለ፣ በገዳዮቹና በተገዳዮቹ ብቻ የሚቆም የዜጎች ጠብ ሳይሆን ኦሮሞና አማራ በሆኑ ሰዎች መካከል ሁሉ ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ ጥላቻን የሚያሰራጭና፣ የሕዝቦችን ተስፋ እስከመጨረሻው ከንቱ ሊያስቀር የሚችል አደገኛ መርዝ ይሆናል።

ይህን ወንጀል ለማስቆም የመጀመሪያው ተግባር የወንጀሉን የፖለቲካ ጭምብል አውልቆ አረመኔያዊ ድርጉቱን ለሕዝብ በግልጽ ማሳየት ይሆናል። ከዚያም የመገናኛ ብዙሃን የጥቃቱ ሰለባ የሆኑትን ሰዎች ታሪክ ለሕዝብ በክብር በማሳወቅ፣ ሽማግሌወችና የሃይማኖት መሪወች የእርቅና ምክክር ስራቶችን በሕዝብ ፊት እንዲፈጽሙ በማድረግ፤ የሕዝብ ለሕዝብ ውይይት በመክፈት፣ በመንግስት በኩል አጥፊወችን በሕግ በመቅጣት፣ ተጎጅወችን በማቋቋምና በመካስ፣ እንዲሁም እርዳታ በማሰባበር የተጎዱትን ለማቋቋም ጠንክሮ መስራት አለበት። ይህ ጥረት በሃገሪቱ የሰላምና የትብብር ተስፋ መፍጠር ይችላል። ይህን ካላደረገ ግን ጥቃቱን ይደግፈዋል ወይም አይቃወመውም፣ ወይም እንደአንድ ተፈጥሯዊ አደጋ ያየዋል ማለት ነው።

የማንነት ጥቃትን በስሙ አለመጥራት የምንከተለው ስርዐት ለመብት የማይመች መሆኑ ታውቆ አስፈላጊ መሻሻሎች እንዳይደረጉ ያደርጋል። መቸም በሕይወት ከመኖር መብት የሚበልጥ መብት ያለ አይመስለኝም። የመንግስት ዋና ሃላፊነት ሕይወትን መጠበቅ ነው። የህገመንግስቱ አቀራረብ ብሔርተኝነትን እንደሉዐላዊ የጋራ መብት ስለሚቆጥር፣ መንግስት የግለሰብ መብትን አስከብራለሁ የሚለው በብሔርተኝነት መዋቅር ውስጥ አልፎ ነው። ይህ የቱንም ያህል አስቸጋሪ ቢሆንም የመንግስትን ሃላፊነት ግን አያቀልለትም። መንግስት የተፈጥሮ መብት በብሔር ልዩነት እንዳይረገጥ የማድረግ አለማቀፋዊ ግዴት አለበት። በማንነት ላይ የሚፈጸም ጥቃትን በስሙ የማንጠራው ከሆነ ግን ይህንን ግዴታ ከመንግስት ትከሻ ላይ እናወርድለታለን። ጉዳዩ የስርዐት ችግር ወይም በፖለቲካ ስም የሚፈጸም ከባድ ወንጀል ሳይሆን የጥቂት ሰዎች ህገወጥነት ችግር ብቻ ተደርጎ እንዲታይ ይሆናል። ይህ ደግሞ በሌላ አባባል የብሔር ፌደራሊዝሙ አተገባበር የፖለቲካ ወንጀልን ከሕግ ቁጥጥር ውጭ አድርጎ እንዲቀጥል ያደርጋል:: ከዚህ በዘመናዊ የጦር መሳሪያ ከተደራጀ ገዳይ ሃይል በስተጀርባ ማን እንዳለም ለማወቅ አይቻልም። የአሜሪካን ጨምሮ በርካታ መንግስታት ከተጠያቂነት ለመሸሽ ህገወጥ ቡድኖችን አስታጥቀው ብዙ ወንጀል ስለሚያስፈጽሙ፣ ሕዝብ መንግስትን እንዳይጠራጠር ከተፈለገ ጥርት ያለ መረጃ መስጠትና ቁርጠኛነቱን በተግባር ማሳየት አለበት።

የማንነት ጥቃትን በስሙ አለመጥራት ጽንፈኝነትን የበለጠ ያባብሳል። ዘር ተኮር ጥቃት በአለማቀፍና ሃገራቀፍ ደረጃ በስሙ ካልታወቀ መንግስትም ይሁን ጽንፈኞች እርምጃቸውን ለማስተካከል የሚያስገድድ ጫና እንዳይደርስባቸው ምክንያት ይሆናል። እንደውም በተቃራኒው ጽንፈኞች ያለማንም ተከራካሪ ትርክታቸው ትክክለኛ የፖለቲካ ምክንያትና የሕዝብ ድጋፍ እንዳለው አድርገው ለማቅረብ ነጻ እድል ያገኛሉ። ዘርንና የፖለቲካ እምነትን በሚያደባልቅ ሁኔታ ኦሮሞም ይሁን ጉራጌ፣ ትግሬም ይሁን አማራ ብቻ የኢትዮጵያዊነት ወይም የአንድነት ፖለቲካ አቀንቃኝ የሆኑትን ሁሉ ‘አማራ’ በሚል ስም በመፈረጅ፣ ለጠላታቸው የብሔር ማንነት በመስጠት፣ የራሳቸውን የብሔር ትግል በሕዝቦች የማንንት ልዩነት ላይ ይመሰርታሉ። የጥቃታቸው ሰለባ የሚሆኑትን ሰላማዊ ሰዎች ከፖለቲካ ጠላቶቻቸው ጋር አንድ ማንነት እንዳላቸው አድርገው ከፈረጁ በኋላ ወንጀልን የተቀደሰ የነጻነት ትግል አካል አድርገው ለማቅረብ ይመቻቸዋል። በዚህ ሂደት ህጻናትንና እናቶችን ጭምር የገደሉ ሰዎች የፈጸሙትን አረመኔአዊ ተግባር የማንነታቸው አካል አድርገው ስለሚያዩት የበለጠ ጥፋት ለመፈጸም የሚያነሳሳ ስነልቦናዊ ፍላጎት ያድርባቸዋል። ይህ ሰላማዊ ሕዝቦችን ለከባድ ወንጀል የሚያጋልጥ አሰራር በግልጽ ካልተነገረና የሕዝብ ተቃውሞ ካልገጠመው በሃገር ብቻ ሳይሆን በውጭም ብዙ አድማጭ ያገኛል። ምክንያቱም አብዛኛው የአለም ሕዝብ አፍሪካውያንን የብሔር ዘረኞች አድርጎ ስለሚያይ የኢትዮጵያን ነባር ገጽታ በቀላሉ ወደሌላው የአፍሪካ የጎሳ ዘረኝነት ታሪክ ለመቀየር ከባድ አይሆንበትም።

በማንነት ላይ የሚፈጸምን ጥቃት በግልጽ አለመታገል የፖለቲካ ትርፍ ማግኛ እንዲሆን ያደርገዋል። በዜግነት ወይም በኢትዮጵያ አንድነት እናምናለን የሚሉ ልዩ ልዩ ፖለቲከኞች ከፖለቲካ ተሳትፎ ውጭ የሆነው የአማራ ሕዝብ በነሱ የፖለቲካ አቋም ምክንያት የሚደርስበትን ጉዳት ተገንዝበው በማንንት ላይ የሚፈጸምን ወንጀል ከፖለቲካ በመለየት ለአለም ለማሳወቅ ሲጥሩ አይታዩም። ይባስ ብለው በአማራ ማንነት የሚደርሰውን የሰብዐዊ መብት ጥቃት በግልጽ ባለመናገር ራሳቸውን ከብሔር ፖለቲካ የነጹና ገለልተኞች የሆኑ አድርገው ለማቅረብ ሲሞክሩ ይስተዋላሉ። ይህም በማንንት ላይ የሚፈጸመው ወንጀል የሕግ ሳይሆን የፖለቲካ አጀንዳ ብቻ ሆኖ እንዲጥል አስተዋጾ ያደርጋል። እነዚህና ሌሎችም ምክንያቶች በማንንት ላይ የሚፈጸም ወንጀልን እንደፖለቲካ መሳሪያ የሚጠቀም ባህልን ያጠናክራሉ። ይህ ሁኔታ ወደፊት ከቀጠለና በማንነት ላይ የሚደርሰው ወንጀል እንደተድበሰበሰ ከቀረ፣ መንግስት ራሱ በአክራሪነት የተፈጠረውን የፖለቲካ ሃይል የራሱ አጀንዳ ማስፈጸሚያ ያደርገዋል። በዚህም ምክንያት ሃገሪቱ የከፋ የአድልወ ስርዐት ውስጥ ልናገኛት እንችላለን። ይህንን ሁኔታ ለመቀነስ በተለይም ከመንግስት የሚጠበቀው የመጀመሪያው እርምጃ በማንነት ሳቢያ የሚደርሰውን ግድያና መፈናቀል በስሙ በመጥራትና፣ በሕግ እንዲዳኝ እንጅ የፖለቲካ ትርፍ ማግኛ እንዳይሆን ማድረግ ነው።

በማንነት ላይ የሚደርስ ጥቃት በስሙ መገለጽ ያለበት ከተጠቃው ማንነት ጋር የሚያያዝ መፍትሄ ስለሚያስፈልገው ነው። በአማራ ማንነት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በስሙ አለመጥራት የሚጠቃውን የአማራ ማንነት ለመታደግ ምንም ነገር እንዳይደረግ ያደርጋል። በሕይወት የመኖር መብት ከሁሉም መብቶች ስለሚበልጥ የመንግስት ቀዳሚ አስፈላጊነት ይህንን መብት ማስከበር ነው። መንግስት የሰዎችን በሕይወት የመኖር መብት አሁን ባለው የብሔርተኝነት መዋቅር ውስጥ ማረጋገጥ ካልቻለ፣ ያለው ብቸኛ አማራጭ ከግለሰቦች ጋር እንደብሔር የፈጸመውን ህገመንግስታዊ ጋብቻ አፍርሶ እንደዜጋ መዋዋል ይሆናል። (እርግጥ ይህን እሚያደርግ ከሆነ የዜግነት መብቶች የብሔር መብትን እንዳይረግጡ ማድረግም ይኖርበታል)። ያኔ ሰዎች በብሔር ስማቸው ቢገለጹ ወይም ባይገለጹ ላያከራክር ይችላል። አሁን ግን ዜግነት በራሱ በቂ ሆኖ በማይከበርበት ሁኔታ፣ የብሔር ጥቃትን በስሙ አለመጥራት፣ አማራወችን ያለህገመንግስት ከለላ ራቁታቸውን ማስቀረት ይሆናል። መርሳት የሌለብን እውነታ፦ የተጎጅወቹን ጥቃት የብሔር ማንነታቸው ምክንያትየደረሰ ነው ብሎ አለመጥራት ሕይወታቸውን ከብሔር ፖለቲካ ነጻ አያደርገውም። ይልቁንም፣ በሕይወታቸውና በኑሯቸው ላይ የተፈጸመው ወንጀል የፖለቲካ አጀንዳ ማራገቢያ ሆኖ ይቀጥላል። (በነገራችን ላይ ዜግነትም ይሁን ብሔርተኝነት ከባዕዳን የቀዳነው ትርከት እንጅ ከሃገራችን ሕዝብ ባህልና ልምድ የወረስናቸው ሃሳቦች አይደሉም። ሁለቱም ሳይኖሩ ኢትዮጵያ ለብዙ ጊዜ ኑራለች። ይህንን ለመተንተን ግን ሌላ ሰፊ ርእስ ያስፈልጋል።)።

አንዳንዶች አማራወች ተበደሉ ብሎ መናገርን ለአንድ ብሔር መቆም እንደማለት አድርገው ይቆጥሩታል፡፡ ይህ አተያይ ግን የተበዳዮቹን ሰብዐዊ መብት በራስ ርዕዮተአለም ብቻ ከማየት የሚነሳ ስህተት ነው። የዘር ፖለቲካን አልቀበልም የሚለው እሳቤ ችግር የለበትም፡፡ በእኔ እምነት የብሔርም ይሁን የአንድነት ፖለቲካ ከሕዝብ ውስጥ በፈለቁ ፍላጎቶችና እሳቤወች ካልተመራ አብዛኛውን ድሃ ሕዝብ አያገለግልም። ያም ሆነ ይህ፣ ፖለቲከኞች የአንድነትም ይሁን የብሔርተኝነት ፖለቲካን የማራመድ መብታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ከሰላማዊው የአማራ ሕዝብ ጥቃት ጋር ተያይዞ እየተነሳ ያለው ጥያቄ የርዕዮተአለም ሳይሆን የመብትና የገሃዱ አለም ጥያቄ መሆኑን ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ትግሬም ይሁን አማራ፣ ኦሮሞም ይሁን ኮንሶ እንደዜጋ ብቻ ሳይሆን፣ እንደብሔር ማንነቱም እንድንቆምለት የሚያስገድድ ሁኔታ ተፈጥሯል። የቱንም አይነት የተለያየ የፖለቲካ እሳቤ ቢኖረን፣ የማንነት መብት የፖለቲካ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሕግ ጉዳይ ስለሆነ ይህ መብት ሊከበር ይገባል። ይሁን እንጂ፣ ህገመንግስቱ የብሔር ማንነትን በሕግ መከበር እንዳለበት መብት አድርጎ ከደነገገ በኋላ አፈጻጸሙን ግን አማራነትን ተከባሪ ሳይሆን ተጠቂ እንዲሆን በሚያደርግ የፖለቲካ አውድ ላይ ጥሎታል። መንግስት ይህ የፖለቲካ አውድ የሕግ መብትን እንዳይጥስ የማድረግ ግዴታ አለበት። ይህን ካላደረገ መንግስት የአማራን ማንነት በሕግ የፈጠረው ለማስከበር ሳይሆን ለማስጠቃት አልሞ ነው ብሎ ለመናገር ያስደፍራል።

እዚህ ላይ ራሳቸውን የኢትዮጵያ አንድነት ጠበቃ አድርገው የሚያዩ ሰዎችን አቋም መቃኘት ያስፈልጋል። እነዚህ ሃይሎች፣ የብሔር ፖለቲካ ቀርቶ ሁሉም ሰዎች ዜጋ ሆነው በእኩልነት ይኑሩ፣ ህገመንግስቱም የብሔር ፖለቲካን ያስወግድ ሲሉ ይደመጣሉ። በመሰረቱ ይህ የህገመንግስት ይቀየር የሚል ትግል አስፈላጊ የሚሆነው በህገመንግስቱ ትግበራ ምክንያት በአማራወች ላይ የደረሰውን መዋቅራዊ ጭቆና አስቀድሞ ወይም በአንድ ላይ ለመፍታት የሚያስችል ቅድመ ሁኔታ መፍጠር የሚቻል ከሆነ ነው። የህገመንግስቱ መነሻ ምንም እንኳን አማራን ጨቋኝ አድርጎ በማየት የተፈጠረ ቢሆንም፣ በአሁኑ ጊዜ ራሱ አማራ በተጨቋኝነት ውስጥ የሚገኝ ማንነት ሆኗል። ስለዚህ ህገመንግስቱ ይቀየር የሚለው ትግል ዘረኛው የአድልወ መዋቅር ይወገድ ከሚለው ትግል ሳይነጠል መቅረብ ያለበት ጥያቄ ነው። ከዚህ በኋላ ህገመንግስቱን መቀየር ላይ ያነጣጠረ ትግል ብቻውን የእኩልነት ጥያቄን መፍታት እንዳይችል የሚያደርግ መዋቅራዊ እውነታ ተፈጥሯል። ይህ መዋቅር (structure) በጦር ሰራዊቱ፣ በኢኮኖሚውና በሰራተኛው አወቃቀር ላይ ስር ሰዶ ከተጠናከረ በኋላ፣ በኢኮኖሚ፣ በሚሊተሪ፣ በስልጣን ክፍፍል የአንድ ወይም የጥቂት ብሔር አባላት የበላይነት ከተረጋገጠ በኋላ፣ የህገመንግስቱ ብቻውን መቀየር ለአማራ ሕዝብ ፋይዳ ላይኖረው ይችላል። እርግጥ ከአማራ ውስጥ የስልጣን ተቋዳሽ የሚሆኑ ሰዎች ይኖራሉ፤ እርግጥ የዜግነት ፖለቲካ አራማጆች በሁሉም ቦታ የመስራት መብት እናገኛለን በሚል ሊደሰቱ ይችላሉ። ሆኖም በአማራው ላይ ህቡእ የዘር ጭቆናና ግልጽ የመደብ ጭቆና ተነባብሮ ሊጫንበት ይችላል።

በማንኛውም ሁኔታ በዘር ልዩነት ሳቢያ የተፈጠረው መዋቅር እንዳለ የሚቀጥል ከሆነ፣ የአማራ ሕዝብ ጠቡ ከህገመንግስቱ ጋር ሳይሆን ህገመንግስቱን ከሚያስቀጥለው መዋቅር ጋር መሆን አለበት። በብሔር ማንነቱ ምክንያት የተገለለና የሚጨቆን ማህበረሰብ ቢያንስ ለጊዜውም ቢሆን ማንነቱን የሚያከብርለት ህገመንግስት ካለ ያንን መብት ለራሱ ጥቅም ሊገለገልበት ይገባል። እዚህ ላይ የዘረኝነትን ትግል እንደምሳሌ መውሰድ ይቻላል። ነጮች ዘረኝነትን መሰረት ያደረገ ህገመንግስት ነበራቸው። በዚያ ሕግ ተጠቅመው መጀመሪያ የኢኮኖሚዉን፣ የወታደሩን፣ የቢሮክራሲውንና የማህበራዊውን ዘርፍ ሁሉ በነጭ የበላይነት አስተሳሰብ ከሞሉት በኋላ ራሳቸውን ልክ እንደነጻነት፣ ዲሞክራሲያዊነትና እንደእኩልነት ጠበቃ ለማቅረብ ሲሉ ዘረኝነትን የሚቃወሙ ሆነው ቀረቡ። ዘረኝነት ማህበራዊ፣ ባህላዊና መዋቅራዊ መሰረት ከያዘ በኋላ ከህጋቸው ቢሰርዙትም ለጥቁሮችና ለሌሎች ንኡሳን ግን ያመጣላቸው ለውጥ ኢምንት ነበር።

ዛሬ እንደአሜሪካ ባሉት ሃገሮች ውስጥ ዘረኝነት በሕግ ቢታገድም የባህል፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ መሰረቱ ሳይናድ እየቀጠለ ነው። የባህልና የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎችም አንዱ ችግርም ይህ ነው። ሰብአዊ መብት “አንተም ሰው ነህ እኔም ሰው ነኝ፣ ስለዚህ አንተም እኔም እኩል ተፈጥሯዊ መብት አለን” ይልሃል። ግን ይህን ሲልህ እሱ ሚልየነር ነው አንተ ደግሞ ቤት አልባ ነህ። እኩል ያልሆኑ ሰዎችን እኩል እንደሆኑ አስመስሎ የበላይነትን ማስቀጠል የቻሉበት ዘዴ ነው።በስልጣን መዋቅርና በኢክኖሚ እኩል ያልሆኑ ሰዎችን በህጉ መሰረት እኩል ናችሁ ብትላቸው ለድሆቹ ምን ይጠቅማል? የእኩልነት ሕግ ፍትሃዊነትን መሰረት ካላደረገ የጭቆና ጭምብል ይሆናል። ህገመንግስቱ ከፍትሃዊነት ጋር አብሮ ካልተሻሻለ የኢፍትሃዊነት ጭምብል ሆኖ መቀጠሉ አይቀርም። ስለዚህ፣ ህገመንግስቱ ሲወገድ ወይም ሲሻሻል እስካሁን ይዞት የመጣው አድልዎ፣ ግፍና ጭቆናም አብሮት መወገድ ወይም መስተካከል አለበት። ቢያንስ ቢያንስ አማራውን የሚያገል አስተሳሰብና መዋቅር በከፍተኛ ደረጃ ከተፈጠረ በኋላ አሁን በህገመንግስቱ መሻሻል የአማራ ችግር ይፈታል ወይስ ይባባባሳል ብሎ በጥንቃቄ ማሰብ ያስፈልጋል።

ለማጠቃለል፣ የአማራም ይሁን የአፋር፣ የትግሬም ይሁን የኦሮሞ፣ የጉራጌም ይሁን የኮንሶ ማንኛውንም ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት በሚፈጸምበት ጊዜ በኢትዮጵያ አንድነት አምናለሁ የሚል ሰው “የማምነው በዜግነት እንጅ በብሔር አባልነት አይደለም” በማለት ወይም በሌላ ምክንያት ጥቃቱን ተራ ጥቃት አድርጎ መመልከት የለበትም። በብሔርተኝነት የሚያምንም ሰው “የማምነው በብሔርተኝነት እንጅ በዜግነት አይደለም” ብሎ ጥቃቱን ዝም ሊል አይገባውም። ይህንን ማድረግ ፖለቲካ ከሕግ ቁጥጥር ውጭ እንዲሰራ መተባበር ነው። በማንነት ላይ የሚፈጸም ጥቃት ከፖለቲካ አጀንዳነቱ በፊት ከፍተኛ የሆነ አለማቀፍ ወንጀል ነው። የማንነት ውንጀላ በሕግ ካልታረመ ማንኛውንም ሰው በሰበብ ባስባቡ ሰለባ ስለሚያደርግ ማህበረሰባችንን በፍርሃት አስሮ የሚያኖር ሰንሰለት ይሆናል። ብዙ ፖለቲከኞች ያላቸው አቋም “ያንተ መብት በእኔ የፖለቲካ እሳቤ ካልተቀረጸ አያገባኝም” የሚል አይነት ነው። ይህ ማለት ከሰው ሕይወት የራስን ርዕዮተአለም ማስቀደም ይሆናል። በሌላ አባባል የወንጀሉን ግዝፈት ተቀብሎ በስሙ መጥራትና ማውገዝ የመፍትሄ ፍላጎት ምልክት ነው።

(ይቀጥላል)…

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለጥምቀት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል አደረሳችሁ፣ አደረሰን!! በክርስቲያኖች ዘንድ ጥምቀት...

የአርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ስርዓተ ቀብር ተፈጸመ

የአርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ስርዓተ ቀብር በመንበረ ጸባኦት ቅድስት...

በእስር ላይ የሚገኙት መምህርት መስከረም ዓይናቸው በጽኑ መታመሙን ጠበቃቸው ገለጹ

ከሁለት ዓመት በላይ በእስር ላይ የሚገኙት መምህርት መስከረም አበራ...

ንግድ ባንክ “ስታርፔይ” የተሰኘ አዲስ መተግበሪያ ይፋ አደረገ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል ባንክ ሥርዓቱን ይበልጥ ዘመናዊና ቀልጣፋ...