የአሁኑ የትምህርት ሁኔታ በጣም የሚያስገርም ነው፡፡ ጉለሌ እኛ ሰፈር አንድ የምናውቀው ሰው መኖሪያ ቤት የነበረውን “አልካን” የጤና ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቬርሲቲ ሆኖ ካየሁ በኋላ ተስፋ ቆርጫለሁ፡፡ ይሄን ጉድ ለማየት የሚፈልግ ራስ ደስታ ሆስፒታልን አልፎ በስተግራ ቁልቁል የምትወርድ መንገድን ተከትሎ ከአምሳ ሜትር በኋላ በስተግራ የሚገኝ ነው፡፡ የቱሪዝም ድርጅቶች ሊስታቸው ውስጥ መመዝገብ አለባቸው፡፡ ድሮ እናመሽበት የነበረው የውቤ በረሃ ሰፈር የሜዲካል ኮሌጅ ሆኗል፡፡ ጥንት ዶክተሮች የበዙበት አገር ግብፅ ነበር፡፡ ካይሮ መርካቶ የሚሄደው የውጭ አገር ሰው በሙሉ በነጋዴዎቹ የሚጠራው “ዶክተር” ተብሎ ነው፡፡ እኔም ለመጀመሪያ ግዜ ዶክተር የሆኑኩት እ.ኤ.አ በ1964 በካይሮ ገበያ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በየጉራንጉሩ ዩኒቨርሲቲ እንዲከፈትና ዲፕሎማ በሰፊው እንዲታደል ያደረጉት ከጫካ የመጡ የሕወሓት ባለሥልጣኖች ናቸው፡፡
ከአሜሪካን አገር ዲፕሎማ መግዛት ወይም አንድ ሰው ቀጥረው ጽሑፍ ካዘጋጀላቸው በኋላ ደቡብ አፍሪካ ልከው ዶክተር የሆኑ ሞልተዋል፡፡ አዲስ አበባ ወደ ቅድስት ማርያም ሰፈር በመረጡት አርዕስት ዓይነት ዲፕሎማሲ ሠርቶ የሚሸጥ አለ ተብያለሁ፡፡ እንዲያውም ካሜሪካን አገርም በውጭ ምንዛሬ ከተከፈለ ያስመጣል፡፡ የሕወሓት ካድሬዎች በሙሉ ባለ ዲፕሎማ ናቸው፡፡ እነኝህ ባለ ዲፕሎማዎቹም ሆኑ ከዩኒቨርሲቲ የተመረቁት አብዛኞቹ በጥሩ ከዩኒቨርሲቲ ከተመረቁት አብዛኞቹ በጥሩ እንግሊዘኛ አንድ ገጽ መጻፍ አይችሉም፡፡ ዱሮ ሰባተኛ ክፍል የሚጨርሰው ሼክስፒርን ያውቅ ነበር፡፡ ይሄም ሆኖ በሳይንስና ቴክኖሎጂ በጣም የሚያኮሩ ወጣቶች አሉ፡፡ እነርሱን በሙሉ ሰብስቦ ወደ ውጭም በመላክ ሆነ እዚያውም እንዲበለጽጉ የሚከታተል ክፍል ትምህርት ሚኒስቴር ማዘጋጀት አለበት፡፡ በኢሕአዴግ ትዕዛዝ ሥር ያለው ሚኒስቴር የዓባይ ውሃ የሚገኘው ትግራይ ውስጥ ነው በማለት ሲያስተምሩ ቆይተው፣ ራስ ዳሽንንም ጨምረው ነበር፡፡ ዓይን አውጪዎች ምሁራን ያሉበት አገር ውስጥ ትምህርት ይሻሻል ብሎ ለማመን ይከብዳል፡፡
ከተፈጥሮ ዩኒቨርሲቲ የተመረቁት የኛ ነጋዴዎች ጠጅ ሆነ ጠላ ጉልት ይሁን መርካቶ ነግደው ሀብታም የሆኑት መደመር መቀነስ ማብዛትና ማካፈል በደንብ ስላወቁ ነው፡፡ እነ ሁነኛው መራ የሽቶ ፋብሪካ፣ ማሞ ካቻ ትራንስፖርት፣ ቱፋ ሻይ፣ ከዲር ኤባ ቡና፣ ተፈሪ ሻረው የአምቦ ውሃ፣ ቸልፒ ዞማኮላ ባለቤት የመሳሰሉ ነበሩ፡፡ አሁን ያሉት ሀብታሞች በተለይ የሚያስደንቁ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ከሕወሃት ጋር የተሻረኩ ሲሆኑ ሌሎቹ ከተፈጥሮ ዩኒቨርሲቲ የመጡ የሚያኮሩ ዜጎች ናቸው፡፡ በተለይ እኔ ባልስማማበትም ጫት በመሸጥ ሀብታም የሆኑት ሴት ወይዘሮ ጫት በመላው ኢትዮጵያ ቢታገድ ደስ ይለኛል፡፡ የምንተክለውን ጅቡቲና ሱማሌ አገር መላክ እንችላለን፡፡ ድሮ ከሐረርና ድሬደዋ ውጭ አይገኝም ነበር፡፡ ድሬደዋ አሊያንስ ፍራንሴዝ ሳስተምር አንዳንዶቹ ተማሪዎች እንደ መስቲካ ያኝኩ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በ1956 አንዱ ተማሪዬ አሁን የጅቡቲ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ኦማር ጌሌ ነበር፡፡ ለማኛውም የኛ ነጋዴዎች ፒ.ኤች.ዲ፣ ማስተር፣ ቢኤ የሚሉት ተረት ጭራሽ አይገባቸውም፡፡
ከሁሉ አልፎ ተርፎ በኛ ዘመን አብዛኞዎቹ ት/ቤቶች የሙዚቃ ባንድ ነበራቸው፡፡ ከእነርሱ መሪነት ነው እንደ ወታደር ተሰልፈን በልዩ ልዩ በዓሎች የምንካፈለው፡፡ የበተለይ ለገና ቤተ መንግሥት ሄደን ከጃንሆይ እጅ ሹራብና ብስኩት እንቀበል የነበረው፡፡ ጃንሆይም ከቀትር በኋላ አዳሪ ተማሪዎችን ሲጎበኙ ብርቱካን ሙዝ ካደሉ በኋላ ሙዚቀኞቹ የተማሩትን አዲስ መዝሙር ያሰሟቸው ነበር፡፡ ጥንት የኢትዮጵያ ፓስፖርት በአማርኛ በቁም ጽሕፈት የተደረሰ ነው፡፡ ፈራሚዎቹ አፄ ምኒሊክ፣ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በንጉሡ ስም ነበር የሚፈርሙት፡፡ በአማርኛ የተጻፈውን ወደ ፈረንሳይኛ የሚተረጉም እዚያው ሚኒስቴር ውስጥ ነበሩ፡፡ እ.ኤ.አ በ1924 ከልዑል ራስ ተፈሪ መኮንን ጋር አውሮፓን የጎበኙትና እ.ኤ.አ በ1948 በፓሪስ የኢትዮጵያ አምባሰደር አቶ ተስፋዬ ተገኝ ብዙዎቹን ፓስፖርቶች ይተረጉሙ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ዋናው ድክመት የቋንቋ ችግር ነው፡፡ በሕወሓት ዘመን የሚላኩ ዲፕሎማቶች የክልላቸውን እንጂ የሚያገለግሉበትን አገር ቋንቋ አያውቁም ነበር፡፡ አንድ ሴኔጋል የነበረ አምባሳደር ሚስቱ እንደ ኢራን ተወላጆች ጓንት አድርጋ የሰው እጅ አልጨብጥም በማለት አሳፍራን ኢትዮጵያ ምን ነካት የሚል ትችት አጋጥሞናል፡፡
እዚያ ግብዣ ላይ ትገኝ የነበረች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኤች.አይቪ.ኤድስ የአፍሪካ ዳይሬክተር ዶክተር መስከረም በቀለ የቢሮ ሠራተኞቿን አስመጥታ እንዲያስተናግዱ አደርጋለች፡፡ እ.ኤ.አ በ1958 አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ለመጀመሪያ ጊዜ በፊፋ ኮንግሬስ ለመካፈል ሲዊድን የሄዱ ግዜ ስብሰባውን በእንግሊዘኛ ቋንቋ በደንብ የሚከታተልለት ሰው አጠገቡ እንዲኖር ስለፈለገ አቶ አባተ ጌታቸው በስቶኮልም ኤምባሲያችን አንደኛ ፀሐፊን አስመዝግቦት ነበር፡፡ ትናንት ዲፕሎማቶቻችን የሚያገለግሉትን አገር ቋንቋ ማታ ማታ እየተማሩ ራሳቸውን ለመቻል ይጥሩ ነበር፡፡ አብዛኞዎቹ ኤምባሲዎቸቻችን አገር ውስጥ ለብዙ ዓመታት የኖረና ቋንቋውን የሚያውቅ ያገራችን ተወላጅ የሆነ ሰው ይቀጥራሉ፡፡ እነኝህ ሰዎች የኤምባሲውን ሥራ ከማቃለል ሌላ የቆንሲሉን ተግባር በመፈፀም የታወቁ ናቸው፡፡ ፓሪስ ከተማ ያለው አቶ ሰፈፈ ገብሬ የኢትዮጵያውያን ሆነ የፈረንሳዮቹን ጉዳይ በማስፈፀም የተመሰገነ ታዛዥና ሰው አክባሪ ነው፡፡ ሁሉንም ለመርዳት ሁልጊዜ ዝግጁ የሆነ የኢትዮጵያንና የፈረንሳይን ታሪክ በደንብ የሚያውቅ ነው፡፡ ጥንት የኛ አምባሳደሮች የሚለብሱት ድንቅ የሆነ ፕሮቶኮል የጠበቀ ልብሶች ነበር፡፡ ያሁኖቹ ክራቫት መምረጥ እንኳን ያቃታቸው ይመስላል፡፡ ደግነቱ እንደ ሌሎቹ አፍሪካዊያኖች ያገር ልብስ መልበስ ከጀመሩ በኋላ እያማረባቸው ነው፡፡ ሴቶቻችን ምንም ችግር የለባቸውም፡፡
እዚሁ ፓሪስ ኤምባሲ ውስጥ በሹፌርነት እንዲያገለግሉ እ.ኤ.አ በ1951 ከጠቅላይ ሚኒስትሩ መሥሪያ ቤት የተዛወሩት አቶ ግፋው ጉሣ ስልሣ ዓመት ካገለገሉ በኋላ ጡረታ ወጥተዋል፡፡ አቶ ግፋው የፊታውራሪ ታፈሰ ሀብተሚካኤል (የሀብተ ሥላሴ የቱሪዝም መሥራቹ አባት) የብላታ ኤፍሬም ተወልደ መድህን፣ የጄነራል ዐቢይ አበበ የአቶ አካለወርቅ ሀብተወልድ ፓሪስ አምባሳደር ኾነው ያገለገልዋቸው ባለሥልጣኖች ናቸው፡፡ ጃንሆይ ለጄኔራል ደጎል ቀብር ፓሪስ የመጡ ግዜ አሁን ዘጠና ስምንት ዓመት የሆናቸው አቶ ግፋው ጎሣ ናቸው ያመላለሷቸው፡፡ በጠቅላላው አሥራ አራት አምባሳደሮች ያገለገሉ ሁላችንንም የሚያኮሩ ዜጋ ናቸው፡፡ ክብርት እመቤት ሣህለወርቅ ዘውዴ የኢትዮጵያ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ፓሪስ አምባሳደር በነበሩበት ወቅት ከአቶ ግፋው ጎሣ ጋር ይተዋወቃሉ፡፡ በጥለት የደመቀውን ቀሚስና ነጠላ ወይም ኩታ ጣል አድርገው ሲመጡ በጣም ነው የሚያምርባቸው፡፡ ጥንት ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በፈረንሳይ፣ ጅቡቲ፣ ሴኔጋል፣ ኮት-ዲቭዋር ሞሮኮ የሚመጡ አምባሳደሮች ፈረንሳይኛ የሚያውቁ ነበር፡፡
አሁን እንግሊዝ ተናጋሪው ይበዛል፡፡ ባሁኑ ወቅት ቢያንስ በፓሪስ፣ በቤዢንግ፣ በዋሽንግተን ዲሲ በኒውዮርክና ጂኔቫ ያሉት አምባሳደሮች ሥራቸውን በተገቢ ሁኔታ የሚፈጽሙ ናቸው፡፡ አሁን ችግር በገጠመን ግዜ የአገራችንን መብት ለማስከበር ይታገላሉ፡፡ እ.ኤ.አ በ1973 ቻይናን ስጎበኝ የሰማሁት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ውስጥ ቢያንስ አንድ ሰው ያንድ አገር ቋንቋ በማጥናት በመላው ዓለም ያለውን ቋንቋዎች በሙሉ የሚያውቅ ሠራተኞች እንዳልዋቸው ነው፡፡ የያንዳንዱን አገር ፖለቲካ ለመከታተልና ለመሰለል የትምህርትን ጠቃሚነት ያስረዳል፡፡ እና አገራችን ውስጥ ዕድለኞች ሁነን ብዙ ዓይነት ቋንቋ ለመማር ችለናል፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ የአርመንኛ፣ የግሪክ፣ የጣሊያን፣ የጀርመን፣ የዓረብ፣ የሕንድ፣ የአሜሪካ፣ የስፓኒሽ (ማታ ማታ) የፈረንሳይና የእንግሊዝ ት/ቤቶች አሉ፡፡ እኛ ቄስ ት/ቤት ሆነን ኮምፒውተርና ሞባይል ስልክ ይፈጠራል ብለን አላሰብንም፡፡ እናም የሚታየን መሬት ላይ ቁጭ ተብሎ ከመማር ደንበኛ ተማሪ ቤት ገብተን በጠረጴዛና ወንበር ለመጠቀም ነው፡፡
ሕይወት ቋሚ ት/ቤት መሆኑ ከገባን ቆይተናል፡፡ በዚህ በሽምግልና ዕድሜ ያልገጠመን ችግር የለም፡፡ የዘንድሮ ልጆች በቴክኖሎጂ ጥበብ ያላቸው ዕውቀት የሚገርም ነው፡፡ የኛም የሀገራችንን ልጆች ድህንነታችንን አስወግደን እነርሱም በቴክኖሎጂ በትምህርት እንዲራመዱ መንግሥት ጥረት እንደሚያደርግ ተስፋ አለን፡፡ አሁንም ቢሆን እርስ በራሳቸው በመማር የከተማውን የቴክኖሎጂ ሱቆች ያስተዳድራሉ፡፡ የአገራችንን ሕዝብ በጣም የጠቀመው አባትና እናት ዘመዶች ጎረቤቶች የሚሠጡት የቃል ትምህርት ነው፡፡ እና የአገራችን ታሪክ የተማርነው እቤት የሚነግሩንን ነው፡፡ ለሁሉም ምሥጋናችን የላቀ ነው፡፡ በተለይ የተማርነው ሥነ-ምግባር ያገራችንን ባሕል፣ ሰውን ማገዝ፣ መታዘዝ ሽማግሌና ታላላቅን ማክበር ነው፡፡ ጥንት ሁለት ልጆች ሲጣሉ ያየ ሰው ጆሮ ቆንጥጦ መክሮ የሚሄድ ነው፡፡ ባህሉ እንጂ የሚያስገድደው ሕግ አልነበረም፡፡
የደርግ ወታደሮችን ኮሚኒዝም ምን እንደሆነ ለማስተማር ሞክረው የፈጠሩት የተማሪዎች ንቅናቄ ነው፡፡ ከዚያ ከደርግ ግዜ ጀምረው ተወልደው ያደጉ የኛን ኢትዮጵያ ጭራሽ አያውቁም፡፡ ደርግም ያስተማራቸው እስክስታ፣ የሌሊት ዘበኝነት፣ መሰለል፣ ማጋለጥና መጠቆም የስታሊንን ሲስተም ነው፡፡ አንዳንዶቹ አሁንም አሉ፡፡ አሁን እንኳን ካፒታሊስት ሆነዋል፡፡ ደርግ የረሸናቸው መኮንኖች በሙሉ አገራችን በስንት ድካም የደርግ ወንበዴዎችን በመፍራት የታሰሩትና የተረሸኑት ወይም ጠብ መጫር ያልፈለጉትን እቤታቸው ውስጥ ያጠራቀሙትን የታሪክ ሰነዶች በሙሉ ከነፎቶግራፎቹ አቃጥለውታል፡፡ በመጀመሪያ የጣሊያን ፋሽሽቶች ቀጥሎ ኢትዮጵያዊያን አከሰሩን፡፡ ስልሣ ሦስቱ የተረሸኑት ባለሥልጣኖች በትምህርት ያሳለፉትን ግዜና በሥራ መስክ የሰጡትን አገልግሎት ብንደምር የሚገባቸው ሽልማትና ክብር ነበር፡፡ አሁን ባገራችን ያለውን ሁኔታ ስንመለከት ከደርግ ግዜ አንስቶ ያፈራነው የነፍስ ገዳ ቁጥር ከፍ ብሎአል፡፡ ሕወሓት የዘረጋው የአፓርታይድ ፖለቲካ በተለይ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚለውን ዘር ለማጥፋት ሁሉም እየተባበረ ነው፡፡ አገራችን አሳዛኝ ሁኔታ ላይ ነች፡፡ እግዚአብሔር እናት ኢትዮጵያን እንዲያድናት ከመፀለይ አንቆጠብም፡፡ ክፉውንም ሆነ ደጉን ለመፈፀም ዕውቀት ያስፈልጋል፡፡ ዕውቀት ደግሞ የሚገኘው በትምህርት ነው፡፡ ጠቃሜታው የገባቸው ሁሉ ናቸው ዲፕሎማ የሚገዙት፡፡
ሁላችንንም የሚያስጨንቀው ለግዜው ሕዝባችንን ያፈናቀሉትና የረሸኑት ያላንዳች ፍርሃት እቤታቸው ቁጭ ብለው ጠላ ሲጠጡ ማየቱ ነው፡፡ ማንም ደፍሮ አይጠይቃቸውም፣ የኔ ዘር እስካልተነካ ድረስ ምንቸገረኝ የሚል አቋም የነፈሰበት ግዜ ነው፡፡ በአገራችን የተማረ አርቆ አስተዋይ ቢበዛ ኖሮ ከመገዳደሉ መወያየቱ የሚሻል መሆኑን መረዳት ይችሉ ነበር፡፡ ወደፊት የሚዘጋጀው ምርጫ ያንዱ ዘር ከሌላው እንዳይበልጥ ለማስተካከል የተዘጋጀ ጭፍጨፋ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ወደ መቃብር የሄደው የምርጫ ካርድ ባይደርሰውም በመሞቱ የተነሣ የአንዱን ዘር ቁጥር ሳይበዛ አይቀርም፡፡ ወይም ተደምሮ ይሆናል፡፡ ይሄ ሁሉ ግርግር ፓርላማ ገብተው ለማጨብጨብ ነው፡፡ እኛ እንኳን ስታዲየም ገብተን የምናጨበጭበው ለቡድናችን ነው፡፡ የዴሞክራሲ ሕግ የተከበረ ስለሆነ ሁሉም ለሚፈልገው ክለብ ያጨበጭባል፡፡ እኔን የምታሳዝነኝ ዴሞክራቷ ብርቱካን ሚዴቅሳ ነች፡፡
በአሜሪካ፣ አውሮፓ፣ አውስትራሊያ፣ አፍሪካ የተበታተኑት ኢትዮጵያዊያን ምሁራኖችና ባለ ሙያዎች አገራቸው ገብተው በሰላም መሥራት ቢችሉ ኖሮ ትልቅ ለውጥ ለማየት እንችል ነበር፡፡ “ታዲያስ” የሚባለው በኒውዮርክ ከተማ የሚገኘው ዌብሳይት በአቶ ሊበን ኤቢሳ ዋና አዘጋጅነት የሚመራው በአሜሪካን አገር ተወልደው ወይም ከኢትዮጵያ መጥተው እዚ ያደጉ ወጣቶች ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ጨርሰው በሥራ መስክ የተሠማሩትን በየግዜው ስለሚያስተዋውቅ ሁላችንም ኩራት ይሰማናል፡፡ ወጣቶቹ ከፍተኛ ኃላፊነት የተረከቡ በአሜሪካ ካሉት ኩባንያዎች የታወቁትን የሚያስተዳድሩ ናቸው፡፡ እንዲያውም ሴቶቹ ከወንዶቹ ይበልጣሉ፡፡ ይህ በግልፅ የሚያስረዳን የኢትዮጵያ ወጣቶች የትምህርት ዕድል ከደረሳቸው የማይቦዝኑ መሆኑን ነው፡፡ ለቤተሰባቸው ገንዘብ ይላኩ እንጂ በተራ ሥራ ተይዘው እንግሊዘኛ ቋንቋ እንኳን በደንብ መናገር ሳይችሉ የሚኖሩም አሉ፡፡ አስደናቂው ባዶ እጃቸውን አሜሪካ ገብተው ተምረው የከበሩ ሚሊየነር ያገራችን ሰዎች አሉ፡፡ የኢትዮጵያን የትምህርት ሁኔታ በደንብ ለመረዳት የዶክተር አክሊሉ ሀብቴ ከካናዳና አሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች የተመረቀው የአዲስ አበባ ዪኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት የነበረው የደረሰውን ሰፊ መጽሐፍ ማንበብ ያስፈልጋል፡፡
ኢትዮጵያ ስመ ገናና የነበሩ ደራሴዎች እንደ ብላታ መስርዔ ሐዘን ወልደ ቂርቆስ፣ አቶ ተክለጻዲቅ መኩሪያ፣ አቶ ከበደ ሚካኤል፣ አቶ ሐዲስ ዓለማየሁ (ፍቅር እስከ መቃብር በፈረንሳይኛ ተተርጉሞ ፓሪስ ለሽያጭ ቀርቦአል) አቶ ዘውዴ ረታ፣ አቶ ዬፍታሔ ንጉሤ፣ አቶ ፀጋዬ ገብረመድህን፣ አቶ ታደሰ ዘውዴ የመሳሰሉት ነበሩ፡፡ በኪነ-ጥበብ የታወቁት ሰዓሊዎች አቶ አፈወርቅ ተክሌ፣ አቶ አለፈለገ ሰላም፣ አቶ ገብረክርስቶስ ደስታ፣ አቶ እስክንድር ቦጎሲያን በሙዚቃ አቶ አሸናፊ ከበደ ነበሩ፡፡ የጥንት ተማሪዎች በሙሉ በባዶ እግራቸው እየሄዱ ኳስም እየተጫወቱ ሰዓት ሳይኖራቸው ፀሐይ ስትነሳ ዶሮ ኩኩሉ ሲል ሰምተው ተነስተው የት/ቤቱ ቃጭል ሳይጮህ የሚደርሱ ነበሩ፡፡ ሁሉም ማርፈድ የጀመረው ሰዓት እጁ ላይ ካሠረ በኋላ ነው፡፡ አሁንማ ቴክኖሎጂ ዓለም ውስጥ ስለገባን ፌስቡክ ኢንስታግራም፣ ቲዊተር ፣ ኤሜል፣ ሜሴንጀር፣ ተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚዎች ሆነናል፡፡ ያገራችን ወጣቶች በተለይ ክፍለ ሀገር የሚገኙት ዕድሉ እንዲገጥማቸው ቴሌኮሙኒኬሽን ጥረት እንደሚያደርግ ተስፋ አለን፡፡ በኛ ዘመን መጻፍ የሚችለው ልጅ ለሰፈሩ ሰዎች ደብዳቤ በማርቀቅ ይረዳ ነበር፡፡ ለዘመዶቻቸው ደብዳቤ የሚጽፉት ሁሉ የሚጀምሩት ለአባቴ፣ እናቴ፣ አጎቴ፣ አክስቴ፣ ወዳጄ እገሌ ከተባለ በኋላ “ከሰማይ ርቀት ከምድር ስፋት በስተቀር” እንደምንድነህ እንደምንድናችሁ ይባላል፡፡ ደብዳቤው የሚላከው በሰው እጅ ወይም በፖስት ቤት አድራሻ ሳይጻፍበት የተላኩ ደብዳቤዎች በመላ ኢትዮጵያ ያከፋፍል የነበረ ፖስታ ቤት የኛ ብቻ ነው፡፡
አገራችን ውስጥ ያሉት የባህል ባለሙያዎች መድሃኒት ቀማሚ፣ ወጌሻ፣ አዋላጅ ለሌሎች ሳያስተምሩ በማረፋቸው የተነሣ ዕውቀት መባከኑ ይቆጫል፡፡ ጠንቋይ እንኳን ለማስተማር ያዳግተዋል፡፡ ደግነቱ እናቶቻችን የመሰለ መምህር የለም፡፡ በተለይ ለሴት ልጅ የምግብ አሠራር ባያስተምሩዋቸው ኖሮ እንዳሁኖቹ እንቁላል መጥበስ ላይ ይቆሙ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ አፍሪካን የሚያስቀና በአውሮፓና አሜሪካን ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚያስተምሩት የአማርኛ ቋንቋ እዚሁ አገራችን ውስጥ ተንቆ የላቲን ፊደል የሚጠቀሙበት አሳዛኝ ዘመን ተፈጥሮአል፡፡ በፈረንሳይ አገር ለዩኒቨርሲቲ መግቢያ በሚሰጡት የቋንቋ ፈተናዎች ከግሪክ ላቲን እንግሊዝ ስፓኒሽ ጋር አማርኛም ተሰልፏል፡፡ በጣም የሚገርመው ደግሞ እኛም እንደ አውሮፓኖች የላቲን ቋንቋ ተመሳሳይ ግዕዝ ቋንቋ ያለን ኩሩ ሕዝብ ነን፡፡ “ጤና ይስጥልኝ” ለማለት አንድ ሜትር ርዝመት ያለው ቃል በፈረንጅ ፊደል ስለጻፈ የሚደሰቱ ሊኖሩ ይችላል፡፡ ያገሬ ሰው ግን ድንቄም ነው የሚለው፡፡ ትምሀርት የሁሉም ጉዳይ ቁልፍ ነው፡፡ መጽሐፍ ማንበብን የመሰል ጥቅም የለም፡፡
በዓለም ላይ የነበሩት ፈላስፋዎች የጻፉትን ማንበብ ራሱ አእምሮን እንደሚያንፅ ግልፅ ነው፡፡ እንዲያውም እኛ ኢትዮጵያዊያዎች በልዩ ልዩ ቋንቋ ማንበብ ስለምንችል ዕድለኞች ነን፡፡ አንግሎፎን፣ ፍራንኮፎን፣ አራባፎን፣ ሉዞሮን (ፖርቱጊዝ) ኤስፖኞፎን ተብላ በተከፋፈለችው አፍሪካ ውስጥ አማርኛፎን እኛ ብቻ ነን፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስና በቁራን ውስጥ የተጠቀሰች ኢትዮጵያ ብቻ ነች፡፡ እስካሁን የውጭ ጠላቶቻችንን እንደምንም ብላ በአርበኞችዋ ብርታት መክታ ኖራለች፡፡ አሁን ያስቸገረው በየቦታ የፈነዳው የውስጥ ጠላት ነው፡፡ ጨካኝ ነፍስ ገዳዮች መሆናቸው ግልፅ ነው፡፡ ዓላማቸው ደሃውን ሕዝብ ማጥፋት ነው፡፡ ያ የዋህና ደግ ሕዝባችን ደርግና ሕወሓት በፈጠረው የአረመኔ ቡድኖች ተጨፍጭፎ አለቀ ፤ ተፈናቀለ፡፡ ኢትዮጵያ በሰላም እንድትኖር በትምህርት ጋሻና ጦር እንከላከል፡፡
