ትምህርት በኢትዮጵያ

Date:

የኢትዮጵያ ሕዝብ በነበረው የተፈጥሮ ዕውቀት አገሪቷን በሦስት ሺህ ዓመታት ገንብቶ አስረክቦና ሕዝባችን ለኑሮው የሚያስፈልገውን መሣሪያና ብልሃት ፈጥሮ ሲጠቀምበት የነበረውና እኛም አሁን በተራችን ያገለግለናል፡፡ ይህ የሚያኮራ ሕዝብ ንጉሠ ነገሥቱ ከዙፋን ከወረዱ ጀምሮ ነፍሰ ገዳዮች ሥልጣን ላይ ቁብ ካሉ በኋላ ከነርሱ በዕውቀት የተሻሉትን በመፍጀትና አገሪትዋን በዘር በመከፋፈል የዓለም መሳቂያ አድርገውናል፡፡

የኛ ኢትዮጵያ ምኒልክና ጣይቱ ያራመዱት ዓድዋ ላይ ጣሊያንን ያንበረከኩ የፈረንሳይ ወይን ጠጅ ቦርዶ ይጠጡ የነበሩና በቤንቴሌይ መኪና ይጓዙ የነበሩ ከትልቋ ብሪታኒያ ንግሥት ቪክቶሪያ ጋር በግራማፎን ሰላምታ የተቀያየሩ ዘመናዊ የስልክ አገልግሎት ያስገቡልን መሪዎች ነበሩን፡፡ አስደናቂውን የኢትዮጵያ ታሪክ በዓለም ትላልቁ ቤተ መጻሕፍቶች ውስጥ የሚገኙ የቀበሌ ርካሽ ዶክተሮች ሊያቆሽሹት ሞክረዋል፡፡ ትምክርት በኢትዮጵያ የተስፋፋው በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችና ምሁራን ብርታት ነው፡፡ ትምህርቱ በሙሉ በግዕዝና አማርኛ ስለሆነ አስተማሪዎቹ በሙሉ ቄሶችና ዲያቆኖች ነበሩ፡፡ የሚያስተምሩትም መጻፍና ማንበብ ብቻ ሳይሆን ወደፊት ቤተክርስቲያንን ለማገልገል ይችሉ ዘንድ መዝሙር፣ ፀሎትና ግዕዝም ጭምር ነበር፡፡

አፄ ምኒልክ የቄስ ትምህርት ቤቱን በዘመናዊ ት/ቤት ለመቀየር ወስነው በፈረንሳይኛ “ኤኮል ኤምፔሪያል ምኒሊክ” በአማርኛ “ዳግማዊ ምኒልክ ት/ቤት” ተብሎ በእ.አ.አ በ1906 ተመሠረተ፡፡ ተማሪዎቹም ሃይማኖታቸውን ማክበር እንዲቀጥሉ አስተማሪዎች በሙሉ ከግብፅ አሌክሳንድሪያ ከተማ ኦርቶዶክስ ፓትሪያክ ከሚኖሩበት አስመጡ፡፡ እስከ ሁለተኛ የዓለም ጦርነት ድረስ ኢትዮጵያ የምትጠቀምበት የፈረንሳይ ቋንቋ ስለነበር ዳግማዊ ምኒሊክ ት/ቤትም የሚያስተምሩት በፈረንሳይኛ ነበር፡፡ ዳግማዊ ምኒሊክንም ደግፈው ራስ መኮንን ወልደሚካኤል የሐረር አገረ ገዢ ተማሪ ቤት ከፈቱ፡፡ ቀጥሎም ልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን እ.አ.አ በ1925 በስማቸው አዲስ አበባ ውስጥ ተማሪ ቤት ከፈቱ፡፡

ቀስ በቀስ አገራችን የመጡት የካቶሊክ ቄሶችና እማሆይዎች ተማሪ ቤቶች መክፈት ጀመሩ፡፡ አዲስ አበባና ድሬዳዋ የተከፈቱት የአልያንስ ፍራንቤዝ ት/ቤቶች ያስተማሯቸው የኔንም አባት ጨምሮ አንደኛ ደረጃ ሲጨርሱ ሁሉም ምድር ባቡርና ጉምሩክ መሣሪያ ቤት ነበር የሚቀጠሩት፡፡ ተፈሪ መኮንን የተማሩት ደግሞ ጦር ሠራዊትን ለመገንባት ሆለታ በተከፈተው የጦር አካዳሚ ተመርጠው ጎርመስ ያሉት ተልከዋል፡፡ ከእነርሱ መካከል አገራችንን ያኮሩት የተከበሩ ጄኔራሎች ዓብይ አበበ፣ መርዕድ መንገሻ፣ ነጋ ኃይለሥላሴ፣ ሙሉጌታ ቡሊ፣ ተሾመ ዕርገቱ፣ ወልደዮሐንስ ሻታና፣ ከበደ ገብሬ፣ ታምራት ይገዙ፣ አክሉሉ ዳዲ፣ ዝናብዙ፣ አበበ ተፈሪን የመሳሰሉ ነበሩ፡፡ ብዙዎቹ በጦርነቱ ዘመን ወደ ሱዳን ዘልቀው ሚሊቴሪ አካዳሚ ተምረዋል፡፡ ሴቶቹ የእኔን እናት ጨምሮ ሚቢዴን ላዛሪስት የተማሩ ካቶሊኮች ናቸው፡፡ ሰፈራችን ለቡና ሲሰበስቡ በወሬያቸው ላይ የፈረንሳይ ቃላት ጣል ያደርጉ ነበር፡፡ ከጣሊያን ጦርነት በኋላ ጃንሆይ ከእንግሊዝ አገር ሲመለሱ መንግሥት ወይም ልዕላን መሳፍንቶቹ ያቋቋሙት ት/ቤቶች ወደ እንግሊዘኛ ቋንቋ ተቀየሩ፡፡

ጃንሆይ ራሳቸው ልጅ ሆነው የተማሩት በፈረንሳይኛ ቋንቋ ስለሆነ ቅር ሳይላቸው አልቀረም፡፡ እንዲያውም ከሱዳን አብሯቸው የመጣው ጄኔራል ዊንጌት በራሱ ስም ጉለሌ ት/ቤት ተመርቆለታል፡፡ ጃንሆይ ምንም እንግሊዝ አገር በነበሩበት ወቅት እንግሊዘኛ ተምረው ቢመለሱም ልባቸው እንዲረካ ፈረንሳይኛና እንግሊዘኛ የሚያውቁ የካናዳ መኮንን ት/ቤት ማስመጣታቸው በፈረንሳይኛ እንደ ፈለጉት ለመናገር እንዲችሉ ነው፡፡ በሁለት ወንድማማቾች ጳውሎስና ብስራት አክሊሉ ብርታት የጥንት ተፈሪ መኮንን ት/ቤት ተማሪዎች ማህበር ተቋቁሞ ላገር ቤት ዕርዳታ ይለግሣሉ፡፡ ጥንት የነበረው ችግር ተማሪ ቤቶች አንደኛ ደረጃ ብቻ ስለነበሩ ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ውጭ አገር መሄድ ያስፈልግ ነበር፡፡

በዚህም የተነሣ የኛን ቤተክርስቲያን ይቆጣጠሩ የነበሩት የግብፅ ኮፕት ኦርቶዶክስ ፓትሪያርክ ለመጀመሪያ ግዜ ሠላሳ አንድ የነፃ ትምህርት ሰጥተው ከዳግማዊ ምኒሊክና ከተፈሪ መኮንን የተመረጡት ሄደው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ጨርሰው አብዛኞቹ ወደ አገራቸው ሲመለሱ ሌሎቹ እንደ አክሊሉ ሃብተወልድ ዓይነቱ ወደ ፓሪስ ዩኒቨርሲቲ አመሩ፡፡ ወደ ቤሩት ሊባኖስ አምርተው የነበሩትም ወደ ፈረንሳይ አገር ሄደው ዩኒቨርሲቲ ሲቀጥሉ የተወሰኑት በፈረንሳይ ሚሊቴሪ አካዳሚ ስንስሪ በተባለው ሰልጥነው ተመልሰዋል፡፡ ከመኮንኖቹ መካከል አበበ ደገፋ፣ ዋቅጅራ ባርዳ፣ ኢያሱ መንገሻ፣ ክፍሌ ዕርገቱ፣ ያዕቆብ ገብረልዑል፣ አስፋው ወልደጊዮርጊስን እናስታውሳቸዋለን፡፡ አሌክሳንድሪያ ከሄዱት መካከል አካለ ወርቅ ሀብተወልድ፣ መሸሻ ኃይሌ፣ መክብብ ዳምጤ፣ የመሳሰሉት ነበሩ፡፡

የኮሎኔል አበበ ደገፋ የፖሊስ ኮሚሽነር የነበሩት ልጅ መስፍን አበበ እንደባቱ ከሳንቢሪ አካዳሚ የተመረቀ ጀኔራል ነው፡፡ እንግሊዝ አገር ሳንደርስት ሚሊቴር አካዳሚ የተማሩ ጄኔራል አማን አንዶም ሲሆኑ ከጦርነቱ በኋላ ዓለማየሁ አስፋውና መስፍን ገብረቃል ከዚያው አካዳሚ ተመርቀዋል፡፡ ዳሩ ግን የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቴ ኮተቤ ተከፍቶ የጨረሱት ሁሉ ወደ እንግሊዝ አገር ሄደው ተምረዋል፡፡ ከነርሱም መካከል የጃንሆይ ልጅ ልዑል ሣህለሥላሴ፣ አሰፋ ጥላሁን፣ አሰፋ መንገሻ፣ መንግሥቴ ለማ፣ ሜሪ ታደሰ፣ ሚካኤል እምሩና እንዳልካቸው መኮንንን የመሰሉ ባለሥልጣኖች ነበሩ፡፡ የኢትዮጵያም መሳፍንትና መኳንንት ልጆቻቸውን በራሳቸው ገንዘብ ልከው እንግሊዝ አገር ያስተምሩ ነበር፡፡ እንደኛ ቄስ ትምህርት ቤት አልጀመሩም፡፡ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት አንድ ዲፕሎማ የተዋሕዶ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አሳትሞ ከቄስ ትምህርት ቤት ለተመረቅነው እንዲሰጠን ማድረግ አለበት፡፡

የኛ ቄስ ትምህርት ቤት ከማን ያንሳል? በካርቶን ሳይሆን በበግና በበሬ ቆዳ ላይ ቁም ጽሕፈት ያለበት ዳዊት የደገምን ሰዎች ነን፡፡ በጣሊያን ወረራ ግዜ ተይዘው እንደ እስረኛ ወደ ጣሊያን አገር የተላኩት ሁሉ ጣሊያንኛ አጥንተው ተመልሰዋል፡፡ አዲስ አበባም ኮንቦላቶ የጣሊያን ት/ቤት ስለነበር ብዙዎች ገብተው ተምረዋል፡፡ አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ጣሊያንኛ አቀላጥፎ ነበር የሚናገረው፡፡ ከኮንስላቶ ሌላ በጉለሌ ሰፈር ጄኔራል ዊንጌት መድኃኔዓለም (ባላባት የነበረው) ኢንስቲቱ ፓስተር አባዲና ፖሊስ አካዳሚ መምህራን ማሰልጠኛ አርበኞች ት/ቤት (አባቶቻቸው ጦር ሜዳ ለወደቁ ልጆች) በዊዲሽ-ሚሽን ነበሩ፡፡ የምንታከምበት ሆስፒታል የራስ ደስታ ዳምጠው ሊፍት የነበረው ሲሆን ኢትዮጵያ ውስጥ በመጀመሪያ በሊፍት የተሳፈርን አንድም ፎቅ ብትሆን እኛ የጉለሌ ልጆች ነን፡፡ ኢትዮጵያ ምንም ድሃ ብትሆን ልጆችዋን ለማስተማር በጣም ጥራለች፡፡

ንጉሠ ነገሥቱ ራሳቸው የትምህርት ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት የተጠነሰሰው ቀስ በቀስ ሊመሠረት ተችሎአል፡፡ በመጀመሪያ የሲቢል አቪዬሽን ት/ቤት ቀጥሎ የቴሌኮሚኒኬሽን ት/ቤት (በአፍሪካ የመጀመሪያው) ከዚያም የንግድ ት/ቤት፣ የተግበረ-ዕድ ት/ቤት፣ የነርሶች ት/ቤት፣ ሰፋ ያለ መምህራን ማሰልጠኛ በሐረር የእርሻ ት/ቤት በአምቦ ቀጥሎም ጅማ በመጨረሻም የእርሻ ኮሌጅ በሐረማያ ነበር፡፡ የመጀመሪያውን የእርሻ ት/ቤት ያቋቋሙት ራሳቸው ፈረንሳይ አገር የተማሩት ብላታ ማህተመሥላሴ ወልደመስቀል የትምህርት ሚኒስትር የነበረው የአቶ ሰይፉ ደርግ የረሸነው አባት ናቸው፡፡ ጃንሆይ የፈረንሳይኛ ቋንቋ ተማሪዎች ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸው ወደ አሌክሳንድሪያ እንዳይሄዱ ከፈረንሳይ መንግሥት ጋር ተወያይተው እ.ኤ.አ በ1948 ሊሴ ፍራንኮ ገብረማርያም ት/ቤት ተከፈተ፡፡ አሥራ አራት የምንሆነው ከአሊያንስ ፍራንሴዝ ሱማሌ ተራ ካለው ት/ቤት ሌሎች ከሌላ ስፍራ መጥተው በዚያኑ ዓመት ተመዘገብን ያስለቀቅነው ት/ቤት ውስጥ የነበሩት ቀበና ወንዙ አጠገብ ወደ ተሰራው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ተዛወሩ፡፡ ፈረንሳዮቹ ድንገት ሸሽተን እንግሊዝ ተማሪ ቤት እንዳንገባ ፈርተው በዕረፍት ሰዓት ከረሜላ ይሰጡን ነበር፡፡

የብዙዎቻችን አባቶች ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ስለነበሩ ተማሪ ቤት መጥተው መጽሐፍና ደብተር፣ እርሳስ ላፒስ ማስመሪያ ገዝተው ይሰጡን ነበር፡፡ በወር አምስት ብር ከመክፈል ሌላ የሚገዛው ዕቃ ውድ መሆኑን ስለሚረዱልን የሥራ ጥምደት ስለመጣ ትምህርት ሚኒስቴር ከበደ ሚካኤል፣ ተክለጻድቅ መኩሪያ ይድነቃቸው ተሰማን ባስተርጓሚነት ቀጥሮ አስቸኳይ የሆኑትን ሰነዶች ያስተረጉሙ ነበር፡፡ ከኔ ጋር ከአሊያንስ የመጡት በዕድሚያቸው ላቅ ያሉት ግማሹ ጉለሌ ኢንስቲቱ ፓስተር የላብራቶሪ ቴክኒሺያን ለመሆን ሌሎቹ የማዘጋጃ ቤቶች ቀያሽ (ጄዖሜትር) ለመሆን ተመልምለው ሄዱ፡፡

ሊሴ ገብረማርያም ባካሎሪያውን ያገኘ የፈረንሳይ መንግሥት በሚሰጠው ነፃ ትምህርት ወደ ፈረንሳይ አገር ሄዶ ይማራል፡፡ ከሊሴ ለመጀመሪያ ግዜ ፈረንሳይ አገር የሄዱ ብርሃኑ አበበ፣ ዮሐንስ ካሣ፣ ኤፍሬም አስፋው፣ ያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት እንዲሁም የኪነ-ጥበብ ት/ቤት የማዘጋጃ ቤት የቴክኒክ ት/ቤትና የፈረንሳይኛ ቋንቋ መምህራን ማሰልጠኛ መኮንን ሙላት (የአዲስ አበባ ከንቲባ የነበሩው) ናቸው፤ አዲስ አበባም ሌሎች ት/ቤቶች ነበሩ፡፡ በየነ መርዕድ (ሽመልስ ሀብቴ)፣ አመሃ ደስታ፣ አስፋወሰን(ልዑል መኮንን)፣ ተስፋ ኮከብ(አቃቂ) ሚሽን(ናዝሬት)፣ ቅዱስ ዩሴፍ(ካቶሊክ) የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ከዚያም አምቦ፣ ደሴ፣ ጅጅጋ፣ ነቀምት፣ ሐረር፣ ሰላሌ፣ ደብረማርቆስ፣ አድዋ፣ መቀሌ፣ ጅማ፣ ጎንደር፣ ድሬደዋ ት/ቤቶች ተከፍተዋል፡፡

የቦይ ስካውት ትምህርትም በተፈሪ መኮንን፣ ዳግማዊ ምኒሊክ፣ ዘነበ ወርቅ፣ ሊሴ ገብረማርያም፣ እቴጌ መነን ተቋቋመ፡፡ በዓመት አንድ ግዜ ትምህርት ሚኒስቴር ጃንሜዳ ላይ ጀንቡሬ አዘጋጅቶ ሁላችንም እንሰበሰብ ነበር፡፡ ቅዳሜ ቅዳሜ የየትምህርት ቤቱ ስካውቶች ዩኒፎርማቸውን ለብሰው ድንኳኖቻቸውን ጀርባቸው ላይ ተሸክመው እንጦጦ፣ ሱልልታ፣ ጋራ ሙለታ፣ ገፈርሳ፣ ቢሾፍቱ፣ አቃቂ፣ ወጨጫ በእግራቸው እየሄዱ አድረው ይመለሱ ነበር፡፡ ጥንት ውጭ አገር ለሚሄዱት ተማሪዎች ልብስ መግዣ አምስት መቶ ብር ይሰጣል፡፡ ከዚያም ከትምህርት ሚኒስቴር አንድ ኃላፊ ተወክሎ ተማሪዎቹን ፒያሣ ይዞ ሄዶ የሚያስፈልጋቸውን አሰፍቶ ገዝቶ ያስረክባቸዋል፡፡

ከክፍለ ሐገር የሚመጡትን አዳሪ ተማሪዎች ከዩኒፎርም ሌላ ለገና እና ለክረምት ወደ መጡበት ለዕረፍት ሄደው እንዲመለሱ የሚያስፈልገውን ወጪ ትምህርት ሚኒስቴር ይችላል፡፡ ብዙዎቹ ተማሪዎች እሴታቸው መታጠቢያ ሻወር ስለሌለ ፍል ውሃ ከተማሪ ቤት በሰልፍ ሄደን በትምህርት ሚኒስቴር ሂሳብ እንታጠብ ነበር፡፡ ፍል ውሃ አካባቢ የነበረው ፓስቲ፣ ሱካር ዋጋውም አራት ፍራንክ (አስር ሳንቲም) ነበር፡፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ደግሞ ቅማል እንዳያጠቃን በየወሩ ዲዲቲ ጭንቅላታችን ላይ መንፋትና የዓይን ምርመራ እንድናደርግ ይተባበር ነበር፡፡ በስፖርት መስክ ሁሉም ት/ቤቶች የሚያስፈልጋቸውን መሣሪያዎችና ዩኒፎርም በሙሉ ገዝቶ የሚያድለው ትምህርት ሚኒስቴር ነው፡፡

ለምሳሌ እያንዳንዱ ሦስት የእግር ኳስ ቡድኖች (ኤ-ቢ-ሲ) ነበሩት፡፡ የትምህርት ሚኒስቴር እግር ኳስ ሻምፒዮና ግጥሚያዎቹ ዕሮብ ከቀትር በኋላ ነበረ፡፡ ራቅ ካለ ስፍራ ለምሳ ከኮተቤ ወይም ጉለሌ የሚመቱትን ቡድኖች የሚያመላልስ የክብር ዘበኛ ማክ ወታደር ማጓጓዣ ነው፡፡ የክብር ዘበኛ ሚሊቴሪ አካዳሚ አስተማሪ የነበረው ሻለቃ ኦኒ-ኒስካኔን ነው መሰለኝ ስፖርት እንዲስፋፋ አለቆቹ ዘንድ ዘመቻ ያካሄደው፡፡ የኢትዮጵያ ፉትቦል ፌዴሬሽን ሲቋቋም ለአቶ ይድነቃቸው ተሰማ አምስት መቶ ብር ብድር አንድ ጽሕፈት ቤት ጃንሜዳ ከተላላኪ ጋር የሰጠ የክብር ዘበኛ መምሪያ ነው፡፡ ከዚያም ኦኒ-ኒስካኔንን የትምህርት ሚኒስቴር የስፖርት ክፍል ዳይሪክተር ሆኖ ለኢትዮጵያ ት/ቤቶች የስፖርት አስተማሪ እንዲኖራቸው ለመጀመሪያ ግዜ ሐረር መምህራን ማሠልጠኛ ያስተማሩን ሰዊድኖች ናቸው፡፡

አቶ ይድነቃቸው እግር ኳስን የሚመለከት ከዳኝነት ጀምሮ ሻምፒዮና ማዘጋጀትና በየክፍለ ሀገሩ ፌዴሬሽን ለመመስረት በይፋ ኃላፊነቱን ለመምህራኖቹ ሰጥቶ ነበር፡፡ ስዊድኖች የነበሩበት አካዳሚዎች በሙሉ የእግር ኳስ ቡድኖች አቋቁመዋል፡፡ ክብር ዘበኛ፣ አየር ኃይልና ፖሊስ በዚያን ግዜ በሁሉም ቡድኖች ውስጥ የሚሰለፉት ከሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች የመጡ ናቸው፡፡ የተማሪዎች ቡድን የነበረው ቅዱስ ጊዮርጊስ ነበር፡፡ የኤርትራ ቡድኖች ስማቸው ዘር ላይ የተመሠረተ ሐማሴን፣ አካለጉዛይ፣ የሚባል ስለነበር አቶ ይድነቃቸው ዘርና ሃይማኖት ነክ የሆነ ምልክቶች መቀበል የለብንም በማለት ስም ሲያስቀይር በዚያ ወታደሮቹንም እንዲቀይሩ አስገድዶ ጦር ሠራዊት (መቻል) ክብር ዘበኛ (መኩሪያ) አየር ኃይል (ንብ) ፖሊስ (ኦሜድላ) ተብለው ተሰየሙ፡፡ አሁን የኢትዮጵያ እግር ኳስ የወደቀው እነኛ በዕውቀታቸውም የሚጠቀሙ እንደ መንግሥቱ ወርቁ፣ ነፀረ ወልደ ሥላሴ፣ ሸዋንግዛው አጎናፍር፣ አዋድ መሃመድ፣ ተቀዳ ዓለሙ፣ ዘውዴ ሳሙኤል፣ ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስን የመሳሰሉ ስለጠፉ ነው፡፡ አዲሱ የአፍሪካ ፉትቦል ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት የደቡብ አፍሪካው ቢሊየነር ሞትሴፔ ከኪሱ አሥር ሚሊዮን ዶላር አውጥቶ የአፍሪካ የትምህርት ቤቶች ሻምፒዮና ሊያዘጋጅ ነው፡፡

በአገራችን በአትሌቲክስ ዝነኛ የነበሩት ተማሪዎቸ አበራ ካሳ፣ ንጉሤ ሮባ፣ ሁሴን ሮብሌ፣ ሰይድ ሙሳ፣ ኡመር ሮያሌ፣ ተፈሪና ክፍሌ በላይ፣ ሁሴን ቀረቦጮ የመሳሰሉት ከመቶ ሜትር አንስቶ እስከ ሺ አምስት መቶ የሚሮጡ ቀልጣፋዎች ነበሩ፡፡ እቴጌ መነንና ሊሴ ገብረማርያም ጥሩ ጥሩ ሩጮች ነበሩ፡፡ በዓመት አንድ ግዜ በሚዘጋጀው የት/ቤቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ልክ እንደ ዓለም ሻምፒዮና ሁሉም ዓይነት ውድድር ያለበት እቴጌና ጃንሆይ መጥተው የሚመለከቱት ነበር፡፡ የአዲስ አበባ ወወክማ (YMCA) በተለይ የቅርጫት ኳስ በኢትዮጵያ እንዲስፋፋ ትልቅ ጥረት አድርጓል፡፡ መሪዎችም አሰልጥነዋል፡፡ የሐረርን ሚሊቴሪ አካዳሚ ያቋቋሙት ሕንዶች ሲሆኑ ምፅዋ ላይ የባሕር ኃይል አካዳሚ የመሠረቱ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሲመሠረት አስተዳዳሪውም ሆነ አብራሪዎቹ ከቲ ደብልዩ ኩባንያ የመጡ አሜሪኖች ነበሩ፡፡ ሆስቴሶችም ከፈረንሳይ ነበር የሚቀጠሩት፡፡ ቀስ በቀስ ከኢትዮጵያ አየር ኃይል የመጡ ፓይለቶች እንደ ዓለማየሁ አበበ፣ አዳሙ መድሃኔ፣ አስፋ አየለ፣ ደስታ ኃይሌ፣ አፈወርቄ ደምሴ፣ ላቀው ወልደማርያም፣ ጅፋር በቀለ፣ ደብሩ ድንበሩን የመሳሰሉት አሜሪካኖቹን ተክተው አፍሪካን ማኩራት ጀመሩ፡፡

አድሚኒስራሲያቅንም ለመጀመሪያ ግዜ የተረከበው ኢትዮጵያዊው ከአየር ኃይል የመጣው ፓይለትና ሜካኒካል ኢንጂኔር ኮሎኔል ስምረት መድኃኔ ነው፡፡ አሁን አየር መንገዳችን የራሱን ፓይለቶችና ቴክኒሺያኖች ያሠለጥናል፡፡ ከአፍሪካም መጥተው የሚማሩ አሉ፡፡ አብዜዎቹም ሆኑ ቴክኒሻዮኖቹ በብዙ አፍሪካ አገሮች ተቀጥረው ይሰራሉ፡፡ ለምሳሌ የኤኳቶሪያል ጊኔ ፕሬዚዳንት ዋናው ፓይለት ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ከጦርነቱ በኋላ እዚሁ አገራችን የቀሩት ከኢትዮጵያን ጋር የተጋቡት ጣሊያኖች በልዩ ልዩ ሞያ በተለይ በጋራዥ ሚካኒክ ሥራ አናጢ ግንበኛ ኤሌክትሪክና ውሃ ሠራተኛ፣ ምግብ አሠራር፣ ልብስና ጫማ ስፌት ያስተማሩ እነርሱ ናቸው፡፡ የኛም ሰው እውቀቱን ለማዳበር ያጓጓ ስለነበር ራሱን ችሎ በተራው እያስተማረ የኑሮ ሁኔታችንን ለማሻሻል ተችሎአል፡፡ አፍሪካ ውስጥ ከመናገሻ ከተማው የትም አውራጃ ብትሄድ ጋራዥና ቴክኒሺያኖች በቀላል ልታገኝ የምትችለው ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለዕድገትም የሚያስፈልጋትን የትምህርት ዓይነት በመመረጥ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ፣ ሕንፃ ኮሌጅ፣ ጎንደር ላይ ሜዲካል ኮሌጅ በመክፈት ትምህርት ተስፋፋ፡፡

በዚያን ዘመን ለትምህርት ሂዶ ውጭ አገር የቀረ የለም፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቀጠራቸው አንደ ሽፈራው ዘለቀ፣ እልፍአገድ ጎበና አይነቶቹ ብቻ ናቸው የቀሩት፡፡ ከውጭ አገርም የሚመለሱት ሥራ እስኪያገኙ ድረስ እቴጌ ሆቴል የሚያርፉት በትምህርት ሚኒስቴር ወጪ ነበር፡፡ ዘመኑ ክራቫትና ሱፍ ልብስ ባርኔጣ በልክ የተሰፋ የሚጠቀሙ የተወሰኑ ሰዎች ስለነበር ከውጭ አገር የሚመለሱት ተማሪዎች በሙሉ ሱፍ ለብሰው ሽክ ብለው ፒያሳ ውስጥ ሲዘዋወሩ ከፈረንጅ አገር መምጣታቸው ይታወቃል፡፡ በመጀመሪያ ወደ አሜሪካን አገር የተላኩት ሶስት ተማሪዎች መላኩ በያን፣ ወርቁ ጎበና እና በሻውረድ ናቸው፡፡ ዶክተር መላኩ በያን በጠላት ወረራ ግዜ ኒውዮርክ ውስት “ዘ-ቮይስ ኦፍ ኢትዮጵያ” የሚል ጋዜጣ ያቋቆሙና ጥቁር አሜሪካኖች ፓይለቶች ኮሎኔል ሮበንስንን ቀጥረው ወደ ኢትዮጵያ የላኩ የጃንሆይ ወኪል ነበሩ፡፡

———— (ይቀጥላል)

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

አገር እንዲህ ዓይንህን ለአፈር ይባላል?

በተጀመረው የአለም ዋንጫ ደቡብ አፍሪካ በሜክሲኮ መሸነፏን ተከትሎ አፍሪካ...

አሜሪካ እና ኢራን የመጀመሪያ ደረጃ ስምምነት በ24 ሰዓት ውስጥ እንደሚፈራረሙ ፓኪስታን አስታወቀች

ዩናይትድ ስቴትስ እና ኢራን በሰላም ድርድሩ ማዕቀፎች ላይ መስማማታቸውን...

ምንገድ ላይ

(በእውቀቱ ስዩም) በቀደም ከሆነ ቦታ ተነስቼ ወደ አልሆነ ቦታ ስራመድ...

ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነ ኢየሱስ በጡረታ ከኃላፊነታቸው ተሰናበቱ

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንና የአዲስ አበባ አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ...