አሜሪካ እና ኢራን ከስምምነት ከደረሱ በኋላ አሜሪካ እና አጋሮቿ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ለኢራን መልሶ ግንባታ ይሰጣል መባሉን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተባበሉ።
ፕሬዝዳንቱ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ እንደጻፉት ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ፈጽሞ እንደማይኖራት ከስምምነት ላይ መደረሱን ጠቅሰው፤ ነገር ግን አሜሪካ ለኢራን 300 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት ተስማምታለች የሚሉ ዘገባዎችን አስተባብለዋል።
ዶናልድ ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ “አሜሪካ ለኢራን 300 ሚሊዮን ዶላር ልትከፍል ነው በሚል የሚነገረው በደደብ ዲሞክራቶች የሚነገር ሐሰተኛ ዜና ነው” ብለዋል።
ኢራን እና አሜሪካ ደረሱበት የተባለው እና እራሳቸው ፕሬዝዳንት ትራምፕ ፈርመውበታል የተባለው ጦርነቱን የሚያስቆመው የመግባቢያ ሰነድ ዝርዝር ዋነኛው ይዘት ይፋ አልሆነም። ነገር ግን ከኢራን እና ከአሜሪካ በኩል እየወጡ ያሉ የስምምነቱ ይዘቶች ላይ አንዳንድ ልዩነቶች እየታዩ ነው።
ሁለቱም አገራት ከርቀት በኤሊክትሮኒክ መንገድ ተቀብለው የፈረሙትን የመግባቢያ ሰንድ ሙሉ ለሙሉ የተቀበሉት ሲሆን፣ የመጨረሻው ስምምነት አርብ ዕለት ስዊትዘርላንድ በተወካዮቻቸው አማካይነት ይፈረማል ተብሎ ይጠበቃል።
