በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ በምስራቅ ጉራጌ ዞን፣ ምስራቅ መስቃን ወረዳ ኢንሰኖ ነዋሪዎች እንደተናገሩት፣ በኢንሰኖ ዎቻ ገነነ ተብሎ በሚጠራው አከባቢ ሰኔ 25 ሌሊት የታጠቁ ሃይሎች በድጋሚ በፈፀሙት ድንገተኛ ጥቃት 4 ሰዎች ሲሞቱ 7 ሰዎች መቁሰላቸውን ገልፀዋል።
ቃላቸውን የሰጡ ሁለት የኢንሰኖ ወረዳ ነዋሪዎች ” ጥቃቱ በቤተሰብ ፕሮግራም ላይ በተሰባሰቡ የቤተሰብ አባላትና ጎረቤታሞች ላይ ነው የደረሰው ” ብለው ” ከተገደሉት ውስጥ ሁለቱ አባትና ልጅ ናቸው ” ሲሉ አስረድተዋል።
ሌላ የአከባቢው ነዋሪም ” ዛሬ አራት ሰው አንድ ቦታ ቀብረናል፣ ባልና ልጇን አንድ ላይ ያጣች እናት እራሷን ስታ ሆስፒታል ገብታለች ” ሲሉ ስለ ጥቃቱ አሰቃቂነት ተናግረዋል።
ስለ ቆሰሉ ሰዎች ብዛት ነዋሪዎቹ ሁለት አይነት ቁጥር ያነሱ ሲሆን ከፊሉ 5 ከፊሉ ደግሞ 7 ናቸው ሲሉ ነው አስረድተዋል።
ከምስራቅ ጉራጌ ዞን እና ከምስራቅ ማስቃን ወረዳ ፖሊስ በጉዳዩ ዙሪያ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነዉ ጥረት ስልክ ባለመስራቱ እና ባለመነሳቱ ምላሻቸው በዚህ ዘገባ አልተካተተም።
@tikvahethiopia
