የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን አንዳንድ ሲል የጠራቸዉ አስመጪዎች በሕግ ከተፈቀደው በላይ የሆነ ዕቃ በሐሰተኛ ሰነድ አማካኝነት ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ላይ መሆናቸውን አጋለጠ።
ኮሚሽኑ በጻፈው አስቸኳይ ደብዳቤ ትዕዛዝ እንደሰጠው፣ አስመጪዎች “በባንክ ፈቃድ ላይ ከተገለጸው ትክክለኛ ብዛትና መጠን ውጭ በሆነ መልኩ በኢንቮይስ (Invoice) ላይ መረጃዎችን ጨምረው በመግለጽ ሰነዶችን እያስመዘገቡ ይገኛሉ” ብሏል።
የኮሚሽኑ የኢንተለጀንስ ዳይሬክቶሬት ባደረገው ማጣራትና 18 ዲክላራሲዮኖችን በናሙና በመመርመር፣ አስመጪዎች በኢንቮይስ ላይ ጨምረው በመግለጽ እና ቀረጥ/ታክሱን በዚያው መሰረት በማስላት፣ ከሕግ ውጭ የሆነ ዕቃ በሕጋዊ ሽፋን እያስገቡ መሆኑን አረጋግጧል። ይህም የጉምሩክ ሕጎችን የሚቃረን መሆኑን ኮሚሽኑ አስታውቋል።
ይህንን ተከትሎም ኮሚሽኑ በሁሉም የጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ አስቸኳይ ትዕዛዝ በማስተላለፍ፣ ሕገወጥ ድርጊቱን ፈጽመው በሚገኙ አስመጪዎች፣ የጉምሩክ አስተላላፊዎች እና ባለሙያዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ አስጠንቅቋል።
ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ ይህ ዓይነቱ የጉምሩክ ጥብቅ ቁጥጥር ከጥቁር ገበያ የውጭ ምንዛሬ በመጠቀም ሕገወጥ ንግድ የሚፈጽሙ አስመጪዎችን ህጋዊውን መንገድ እንዲከተሉ የሚያስገድድ ነው። በመሆኑም፣ በሕገወጥ መንገድ የሚካሄደው የውጭ ምንዛሬ ፍላጎት ሲቀንስ፣ ይህ እርምጃ የውጭ ምንዛሪ ገበያው እንዲረጋጋ አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለዋል።
