‹‹አቶ ገዱ ለተናገሩት ነገር ዋጋ መስጠት ይገባል››

Date:

‹‹ነገሮችን በጥንቃቄ ይዞ መወያየት የሚቻልበት ዕድል ነበር››

ያሬድ ኃይለማርያም (የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

በቅርቡ የሚኒስትሮች ም/ቤት በአማራ ክልል ያወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከቀናት በፊት የሀገሪቱ ከፍተኛው የሥልጣን አካል የኾነው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት እንዲተገበር አጽድቋል፡፡ በክልሉ እየተባባሰ ያለውን ግጭት እና ይኽን ተከትሎም እየደረሰ ያለውን የንጹሐን ሞት እና የአካል ጉዳት፣ ብሎም በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ስለሚፈጸመው አፈሳ እና የጅምላ እሥራት ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ያሬድ ኃይለማርያም ጋር የሚከተለውን አጠር ያለ ቆይታ አድርገናል፡፡ እነኾ!  

ግዮን፡- በቅርቡ በአማራ ክልል የተከሠተውን ግጭት እንዴት ታየዋለህ?

ያሬድ፡- በአማራ ክልል የተፈጠረው ችግር ሀገሪቱን ወደ ሌላ ቀውስ እየመራት ይገኛል፡፡ ከሁለት ዓመት የጦርነት ቀውስ ሳናገግም እንደገና አዲስ የግጭት አዙሪት ውስጥ ገብተናል፡፡ ይሄ በጣም አሳዛኝና አሳሳቢ ነገር ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ግጭት ማቆም አልተቻለም፡፡ ይኼ ኢትዮጵያን ወዴት ይወስዳል የሚለው ደግሞ ወደፊት የምናየው ይኾናል፡፡ የልዩ ኃይሎችን ትጥቅ ማስፈታት ተከትሎ አማራ ክልል ላይ የታየው አደጋ እና መጀመሪያውንም መንግሥት ጉዳዩን የያዘበት አግባብ ችግር ያለበት ነው፡፡ እነዚህ ታጣቂ ኃይሎች ከመንግሥት ጋር አብረው ግንባር ገጥመው የትግራዩ ጦርነት ላይ ዋና ተሳታፊ የነበሩ ናቸው፡፡ ስለዚህ ከማዕከላዊ መንግሥት ጋር በጣም የተቀራረቡ ኃይሎች ናቸው፡፡ ከመጀመሪያውም ወንጀለኛ ጠላት ተብለው የተፈረጁ ኃይሎች አይደሉም፡፡ የመንግሥት ኃይል የነበሩ ናቸው፡፡ ስለዚህ ከታጣቂዎቹ ጋር የሚደረገው ግንኙነት በጣም ጥንቃቄ የተሞላበትና የፈጀውን ያህል ጊዜ ቢፈጅ እንኳን ውይይትና መግባባት ላይ የተመሠረተ የችግር አፈታት ስልት የሚያፈልገው ነው፡፡ ለመንግሥትና ለታጣቂ ኃይልም የሚበጀውም ይኼ ነበር፡፡ ነገር ግን መንግሥት በተቃራኒው በአዋጅ መልክ በአማራ ክልል የሚገኘውን የታጠቀው ኃይል ሁሉ ትጥቅ እንዲፈታና ወደ ተለያየ የፀጥታ መዋቅር እንዲገባ አዘዘ፡፡ እምቢ ካሉም ኃይል እንደሚጠቀም ገለፀ፡፡ ወዲያው ክልሉ ወደ ቀውስ አመራ፡፡ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከመታወጁ በፊት የክልሉ ፕሬዝዳንት የድረሱልን ጥሪ ከማቅረባቸው ከወራት በፊት ኤታማዡር ሹሙ በሰጡት ትዕዛዝ ክልሉ በመከላከያ የጸጥታ ኃይል ተዘምቶበት ነበር፡፡ ብዙ ጉዳት ደርሶ ግጭቶቹ ከተካረሩ በኋላ የክልሉ መንግሥት ከአቅሜ በላይ ነው ብሎ ጥሪ አደረገ፡፡ ከመጀመሪያው የክልሉ መንግሥት ችግሩን በራሱ ሊፈታው አልሞከረም፡፡

ግዮን፡- የክልሉን መንግሥት ችግሩን በራሱ መፍታት ያልቻለው ለምንድን ነው ማለት ይቻላል?

ያሬድ፡- የክልሉ መንግሥት ችግሩን ለመፍታት ምን ያህል ጥረት እንዳደረገ በዝርዝር አላውቅም፡፡ ነገር ግን የክልሉ አመራሮች የሚሉት ችግሩን በሰላም ለመፍታት ብዙ ጥረት አድርገናል ነው፡፡ በቂ ነው በቂ አይደለም የሚለውን በጥልቀት ስለማላውቅ ምንም ማለት አልችልም፡፡ ነገር ግን ለእኔ በጊዜ ገደብ እስከዚህ ግዜ ትጥቅ ፍቱ ካለዚያም በኃይል አስፈታችኋለሁ ከማለት ይልቅ የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ነድፎ ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስድስት ወር እንደሰጠ ሁሉ ለድርድር ስድስት ወር በመስጠት ችግሩን ማቅለል ይቻል ነበር፡፡ ለሰላም ሲባል ረጅም ጊዜ መጨረስ ችግር የለውም፡፡ በእርግጥ ሂደቱ አሰልቺ ሊኾን ይችላል፡፡ ነገር ግን ውይይት ማድረግ ቢቻል ኖሮ በእኔ እምነት ወደዚህ ዓይነት ግጭት ውስጥ አይገባም ነበር ብዬ አስባለሁ፡፡ ጉዳዩን በኃይል ለመፍታት በመንግሥት በኩል የተሄደበት ፍጥነት የሰላም ዕድሎችን በር እንዲዘጉ ያደረገ ይመስለኛል፡፡ ግጭቱንም በማፋጠን ሌላው ወገን እልህ እንዲጋባ የገፋፋም ይመስለኛል፡፡ ለሚዲያ ትርክቶችና ነገሮችን ማባባስ ለሚፈልጉ ወገኖችም በር እየከፈተ ይመስለኛል፡፡

ግዮን፡- መንግሥት ለምንድነው በዚህ ዙሪያ ሆደ ሰፊ መኾን የተሳነው ይላሉ?

ያሬድ፡- መንግሥት ከተለያዩ የመብት ተቋማት የተሰጠውን ምክረ ሐሳብም አልተቀበለም፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ይህን አስመልክቶ ለምክር ቤቱ ጭምር ሪፖርት አቅርቧል፡፡ ምክር ቤቱ ጫና እንዲያደርግበት ጠይቀው ነበር፡፡ ስለዚህ በእኔ እይታ በመንግሥት በኩል ሁሉንም ነገር በኃይል የመፍታት መንገድን እንደዋና ስልት ወስዶ በመሥራት ላይ የሚገኝ ይመስለኛል፡፡ ከሰሞኑም በነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማፅደቅም ምክር ቤቱ ላይ በነበረው ስብሰባ የፓርቲው ዋና ግንባር የኾኑት አቶ ገዱ የመንግሥትን አካሄድ ትክክል አለመኾኑን ሲሞግቱ ነበር፡፡ ‹‹ተሳስተናል፤ ለሁሉም የሀገሪቱ ግጭቶች ኃይልና መሳሪያ እንደችግር መፍቻ መጠቀማችን ስሕተት ነው፡፡ አካሄዱ ችግሮችን ከመፍታት ይልቅ ችግር የሚያባብስ ነው፡፡›› ብለዋል አቶ ገዱ፡፡ ስለዚህ ለአብዛኛው ግጭት መንግሥት ቶሎ የኃይል እርምጃ መውሰዱን ወደ ጦርነት ገብቶ ሁሉንም አካል በጉልበት ለመፍታት መሞከር ብዙ እንደማያዋጣ የትግራዩም ጦርነት መስክሯል፡፡ አንዳንድ ሁኔታዎች ሲነጻጸሩ ደግሞ ለምሳሌ ኦሮሚያ ክልል የኦነግ ሸኔ ኃይልም ላይ የጦርነት እርምጃ ነበር፡፡ የድሮንና የጀት ጥቃትም አልፎ አልፎ ተፈጽሟል፡፡ ነገር ግን የክልሉ መንግሥት ያ ሁሉ እልቂት ተከስቶ፣ ባንኮች ተዘርፈው፣ የመንግሥት ተቋማት ወድመው፣ በርካታ ንፁሓን ዜጎች ተገድለው፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለው፣ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ‹‹ከአቅሜ በላይ ነው መንግሥት ይግባልኝ›› አላለም፡፡ ነገር ግን ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ለመሥራት ተሞክሯል፡፡

ይህ የተደረገው ችግሮች ያሉባቸው አካባቢዎች ብቻ እንጂ በሙሉ ኦሮሚያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አልታወጀም፡፡ ይህ አለመደረጉ የግጭቱን መጠን ይቀንሰዋል፡፡ በታንዛንያ የተደረገው የሸኔና የመንግሥት ውይይትም ጥሩ ጅማሬ ነበር፡፡ መንግሥት አገር አቋርጦ ሄዶ አንድ በብዙ ሰብዓዊ ጥሰቶች ከሚጠየቅ፤ ለብዙ ሰዎች ሕይወት መጥፋት ኃላፊነት ከሚወስድ አማጺ ኃይል ጋር ለመደራደር ያደረገው ጥረትና ትዕግስት የሚደነቅ ነው፡፡ ቤኒሻንጉልም ከታጣቂ ኃይሎች ጋር ድርድር ተደርጓል፡፡ ይሄ የሚበረታታ ነገር ነው፡፡ ቢያንስ የተፈፀመው ነገር እንዳለ ኾኖ አዳዲስ ግድያና መፈናቀሎች እንዳያመጣ ያደርጋል፡፡ ይህን አካሄድ በአማራ ክልል ካሉ ኃይሎችም ጋር ማድረግ ይቻል ነበር፡፡ ነገሮችን በጥንቃቄ ይዞ መወያየት የሚቻልበት ዕድል ነበር፡፡ እነዚያን እድሎች አቶ ገዱም እንዳሉት መንግሥት በአግባቡ አልተጠቀመባቸውም፡፡ በመንግሥት በኩል የተመረጠው የኃይል መንገድ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ጠቅላላ ግጭቱን አባብሶታል፡፡ ነገሮች አሁን ላይ ከቁጥጥር ውጪ ኾነው መንግሥት ድሮን እስከመጠቀም ደርሷል፡፡

ግዮን፡- የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሕጉ ለመንግሥት የሚያጎናፅፈው የተለየ ኃይል ምንድነው?

ያሬድ፡- የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚታወጀው በአንድ ሀገር ውስጥ የሀገሪቱን ሰላም የሚያናጋ ችግር ሲፈጠርና በተለመደው የሕግ ሥርዓት ሰላምና ጸጥታ ማስፈን ሳይቻል ሲቀር ነው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለግጭት ብቻ ሳይኾን ለወረርሽኝ፣ ለተፈጥሮ አደጋና ለመሳሰሉት አጋጣሚዎችም ይታወጃል፡፡ ዓላማው አዋጁ እንዲታወጅ ምክንያት የኾነውን የቀውስ ሁኔታ መቆጣጠር ነው፡፡ ይህ ሲደረግ ግን መጠቀም የሚቻለው ተመጣጣኝ ኃይልን ብቻ ነው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማለት ለመንግሥት ያልተገደበ ሥልጣን የሚሠጥ ማለት አይደለም፡፡ ለዚያም ነው ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ረጅም ጊዜ እንዳይወስድ፤ የዜጎች መሠረታዊ መብቶችንና ነፃነቶችን ያለ አግባብ እንዳይጣሱ፤ መንግሥት ተመጣጣኝ ያልኾነ ኃይል እንዳይጠቀም ሲል ያሳሰበው፡፡ ተመጣጣኝ ያልኾነ ኃይል ማለት ጠመንጃ ይዞ ለመጣ ኃይል ላይ ታንክና ሌሎች ነገሮችን መጠቀም ማለት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የአየር ጥቃቶች በረሃማና ገጠራማ ቦታዎች ላይ ሲኾን ወታደራዊ ቦታዎችን ዒላማ ያደርጋሉ፡፡ ከተማ ውስጥ ሲኾን ግን የዜጎች ሕይወት አደጋ ውስጥ ይወድቃል፡፡ በሰሜኑ ጦርነት ጊዜም መቀሌ ውስጥ የተከሰተው የዚሁ ዓይነት ነው፡፡ አንዳንዴ ታጣቂ ኃይሎች ሕዝብ መሐል ሊገቡ ይችላሉ፡፡

አደባባይ ላይ፣ ትምህርት ቤት፣ ቤተክርስቲያን ውስጥ የተለያየ ቦታ ታጣቂ ኃይሎች ሊመሸጉ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ዓለም አቀፍ የጦር ሕግ አለ፡፡ በዓለም አቀፍ የጦር ሕግ ጠላት የሚባለው አካል የትኛውም የንጹሐን መንቀሳቀሻ ቦታ መመሸግ አይችልም፡፡ ቢመሽግ እንኳን አጥቂው ኃይል ሲቪሊያንን በተለያየ ስትራቴጂ ከቦታው ካራቀ በኋላ ነው ጥቃት መሰንዘር የሚችለው፡፡ ሰሞኑን ፍኖተ ሰላም ላይ የተከሰተው ነገር ታጣቂዎች አሉ ተብሎ የእነርሱን እንቅስቃሴ ለመግታት ተብሎ የተደረገው ነገር ከተማዋን አደጋ ላይ ከመጣሉም በላይ በርካታ ንጹሐንን እንዲደገሉ ምክንያት ኾኗል፡፡ በቢቢሲ ዘገባ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ25 በላይ ነው፡፡ አንዳንድ ዘጋቢዎች ደግሞ ሟቾችን ወደ ሰባ ከፍ ያደርጓቸዋል፡፡ ይሄ ጥቃት ዓለም አቀፍ የጦር ሕግን የጣሰና ዓለም ዐቀፍ የሰብዓዊ መብትን የተላለፈ ነው፡፡ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማዕቀፍም ያለፈ ተግባር ነው፡፡ ስለዚህ ይህን መሰል ጥቃቶች መደገም የለባቸውም፡፡ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንም ባወጣው መግለጫ ለሁለቱም አካላት ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡ በተለይ በመንግሥት በኩል የሚወሰዱ እርምጃዎች የንፁሐንን ዜጎች ሕይወት አደጋ ላይ እንዳይጥሉ አሳስቧል፡፡ የጅምላ እስርንም በተመለከተ አዲስ አበባን ጨምሮ የተለያዩ ከተሞች ላይ የሚደረግ አፈሳ ትክክል አይደለም፡፡ በዚህ ዙሪያ እስካሁን ከመንግሥት በኩል የታመነና የተነገረ ነገር የለም፡፡ መንግሥት 23 ሰዎች እንደታሠሩ ነው የገለፀው፡፡ ነገር ግን በተለያዩ ከተሞች የጅምላ እስር እየተፈጸመ ነው፡፡ ታሳሪዎች የት እንዳሉና በምን ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ይኼም በራሱ ሌላ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን የሚያስከትል ተግባር ነው፡፡

ግዮን፡- የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲወጣ እናንተ ሥራችሁን ለማከናወን እንቅፋት አይኾንባቸውም?

ያሬድ፡- እንደድርጅት እኔ የምመራው ድርጅት ቀጥታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን አይመረምርም፡፡ እኛ በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና በጋዜጠኞች መብት ላይ አተኩረን ነው የምንሠራው፡፡ ነገር ግን እኛ ጉዳያቸውን የምንከታተልላቸው ጋዜጠኞች የሰብዓዊ መብት ተማጋቾች ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም ከግጭቱም ጋር ተያይዞ ሕይወታቸው አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡ አሁን እንኳን ከሰሞኑን እስር ጋር ተያይዞ ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረውና ሌሎችም ታስረዋል፡፡

ገና አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከመውጣቱ በፊት ዘጠኝ የምንኾን የሲቪክ ማህበራት ‹‹ይኼ ነገር ሀገሪቱ ውስጥ ያለውን የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ያባብሳል፤ ስለዚህ መንግሥት ጉዳዩን እጅግ በተሞላው ሁኔታ ይያዝ፡፡ ከልክ ያለፈ ኃይል አይጠቅም፡፡ መንግሥትን ጨምሮ የግጭት ተሳታፊ ኃይሎች በተቻለ መጠን ለውይይት እድል እንዲሰጡ፤ በሚንቀሳቀሱባቸው ቦታዎች ንፁሐን እንዳይጎዱ እና አጠቃላይ የሰላም ውይይት ይደረግ›› ስንል ጥሪ አስተላልፈናል፡፡ ከዚህ ባለፈ ይህ ጉዳይ ቀጥታ የሚመለከታቸው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉባዔ ናቸው፡፡ ኢሰመጉም፣ ኢሰመኮም ሪፖርቶችን አውጥተዋል፡፡ ሐሳባቸውንም እንጋራቸዋለን፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ሀገሪቱ ሰላም ካልኾነችና በየቀኑ ሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚፈፀም ከኾነ በዘርፉ የምንሠራ ድርጅቶች በጠቅላላ ሥራችን ያ ይኾናል፡፡ ምክንያቱም ዜጎች በየዕለቱ መፈናቀል፣ መሳደድና ሞት የሚገጥማቸው ከኾነ እነርሱን መደገፉን እና ቀውሱ ላይ ያተኮረ ነገር እንድንሠራ መገደዳችን አይቀሬ ስለኾነ ነው፡፡

ግዮን፡- ኢሰመኮ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለአንድ ወር እንዲቆይ እና በአማራ ክልል ብቻ እንዲገደብ ቢጠይቅም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዋጁን ለ6 ወራት አጽድቆታል፡፡ ይኼ የሚፈጥረው ነገር ምንድነው?

ያሬድ፡- ኮሚሽኑ የመንግሥት አካል እንደመኾኑ መጠን ለመንግሥት ምክረ ሐሳብና ማሳሰቢያ መስጠት አለበት፡፡ ያንን ነው ያደረገው፡፡ በመጀመሪያ መንግሥት ‹‹በክልሉ ውስጥ ያሉ ከተሞችን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሬያለሁ፤ ሁኔታዎቹ በእኔ ሥር ናቸው›› ስላለ ‹‹እንደዚያ ከኾነ የስድስት ወር አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አያስፈልግም›› ሲል ነው ኢሰመኮ መግለጫውን ያወጣው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተፈጥሮው መብት ገዳቢ ነው፡፡ ስለዚህ የዜጎች መብት ለ6 ወራት መገደቡ ሌላ የሚፈጥረው ችግርና ቀውስ አለ፡፡ እንደመሰባሰብና መንቀሳቀስ ያሉ መብቶችን እና አጠቃላይ ነጻነትን ይገድባል፡፡ ከዚህ አንፃር ለ6 ወራት ዜጎችን አፍኖ ማቆየት ብዙ የመብት ጥሰቶችን ስለሚያስከትል አዋጁ ከተቻለ በሳምንታት ወይም በወር ውስጥ እንዲያበቃ ኮሚሽኑ ምክረ ሐሳብ ሰጥቶ ነበር፡፡ መንግሥትም ኾነ ታጣቂ ኃይሎቹ ከኃይል እርምጃ እንዲቆጠቡ እና ችግራቸውን በሰላም እንዲፈቱ አሳስቦም ነበር፡፡ ነገር ግን ምክረ ሐሳቡ ፓርላማው ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ይኼ የሚያሳየው በቀጣይ ብዙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሊደርሱ እንደሚችሉ ነው፡፡

ግዮን፡- የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲጸድቅ በአቶ ገዱ የተነሱትን ሐሳቦች አንተ እንዴት አዩዋቸው?

ያሬድ፡- ከተለመደው የፓርላማ አሠራር ውጪ እንግዳ ነገር በዚህ ዕለት ተፈፅሟል፡፡ ፓርላማው ሁሉንም ዓይነት ስብሰባዎች በክፍት ያካሂድ ነበር፡፡ ከዚህ ቀደም እንዲያውም ጠ/ሚኒስትሩ የፓርላማ ብቻ ሳይኾን የካቢኔ ውይይት ጭምር በክፍት መታየት አለበት ብለው ነበር፤ ነገር ግን አልኾነም፡፡ ምንናልባት ከስብሰባው በፊት ከአማራ ክልል በመጡ የፓርላማ አባላት ላይ ብዙ ማሳሰቢያ እና ዛቻ ስለነበረ በአንድ በኩል የእነርሱን ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል ሊኾን ይችላል ዝግ የተደረገው፡፡ በሌላ መንገድ ደግሞ ፓርላማ ውስጥ የተደረጉ የሐሳብ ፍጭቶች ወደ ሕዝቡ ከወጡ መንግሥት ውስጥ ክፍተት እንዳለ ማሳያ ሊኾኑ ስለሚችሉ ሌላ ነገር ያመጣል በሚል ፖለቲካዊ ሥጋትም ሊኾን ይችላል ዝግነቱ የተመረጠው፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን የተወሰኑ ሚዲያዎች ገብተው ስለነበር ሪፖርተር የአቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ንግግር ሙሉውን አውጥቶታል፡፡

የእርሳቸውን ንግግር ተከትሎ የሚሰጡ የተለያዩ አስተያቶች እኔ ብዙ አልቀበላቸውም፡፡ እርሳቸው እንደሰው ሕሊና አላቸው፡፡ ስለዚህ ለተናገሩት ነገር ዋጋ መስጠት ይገባል፡፡ በእርግጥ ሰዎች ቢጠራጠሩም አይገርመኝም፡፡ ምክንያቱም ያሳለፍነውን የፖለቲከኞች ክህደት የምንዘነጋው አይደለም፡፡ ፖለቲከኞች ንግግራቸውን ይክዳሉ፡፡ ትላንት የተናገሩትን ነገር መቶ ፐርሰንት የሚቃረን ነገር ዛሬ ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን የእርሳቸው ንግግር በስልት የተነገረ ነገር አድርገው የሚያሰቡ ወገኖችን ሐሳብ አልጋራም፡፡ ስለዚህ አቶ ገዱ የተናገሩት ነገር ለእኔ ትክክለኛ ነው፡፡ በመጀመሪያ አቶ ገዱ ክልሉ ውስጥ የተጠራቀመ ብሶት መኖሩን፤ የክልሉ ሕዝብ ተደጋጋሚ የፍትሕ ጥያቄ አቅርቦ እንደነበር፤ መንገዶች ይዘጉበት እንደነበር፤ ከየቦታው በማንነት ይፈናቀል ይገደል እንደነበር፤ የከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አማራው ማኅበረሰብ ላይ ይደርስ እንደነበር፤ አቤቱታውም እንደማይሰማ ነው የገለፁት፡፡ ሕዝቡ ‹‹መንገድ ይዘጋብኛል›› ሲል ጠ/ሚኒስትሩ ራሱ ለሰላም ሲባል እንደሚዘጋ መግለፃቸው አይዘነጋም፡፡ የዚህ ዓይነት እንግልት በአማራ ሕዝብ ላይ ተደጋግሞ የተከሰተ ነበር፡፡ በመኾኑም ሕዝቡ ለመንግሥት ያለው እይታ እንዲቀየር አድርጎታል፡፡

በተለይ በቅርቡ ገበሬዎች ከተማ ውስጥ ጅራፍ እያጮሁ ሰልፍ አድርገዋል፡፡ አቶ ገዱም ደግሞ ለዚያ ክልል ከማንም በላይ ቅርብ ከመኾናቸው አንፃር የተናገሩት ነገር እውነት ነው፡፡ የተከፋ ገበሬ ፣ የተከፋ ወጣት ፣ የተከፋ ሕዝብ፣ የተከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተፈፀመበት፣ የተከፋ ተፈናቃይ አለ፡፡ ለዚህ ደግሞ ከመንግሥት በኩል የሚሠጡት ምላሾች በቂ አይደሉም፡፡ ስለዚህ ፍትሕ የሚጠይቅ አካል አለ፡፡ ይህን አካል አቶ ገዱ በጥሩ ሁኔታ ገልፀውታል፡፡ እንዲሁም የመንግሥት አስገዳጅ መግለጫዎችና የኃይል አጠቃቀሙ ያለው ክፍተት ምን እንደኾነ አስቀምጠውታል፡፡ ያለፈው አምስት ዓመት የነበሩ ችግሮችን ሁሉ የብልፅግና መንግሥት በኃይል ለመፍታት እንደሚጥርም ገልፀዋል፡፡ ይህም ሀገሪቷን አደጋ ውስጥ እንደሚከት አንስተዋል፤ ይኼ እኛ ደጋግመን ስንጮኽበት የነበረ ጉዳይ ነው፡፡ የመፍትሔ ሀሳብ ብለው ያቀረቡት የውይይትና የንግግር መፍትሔም እንደእኔ እይታ ትክክለኛና ጊዜውን የጠበቀ ምክረ ሀሳብ ለምክር ቤቱ ሰጥተዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ አቶ ገዱ ይህን ሲናገሩ ሊያቋርጧቸው የጣሩ የምክር ቤቱን አባላት ተቋቁመው ነው ሐሳበቸውን የጨረሱት፡፡ ይኼ ደግሞ ለታሪክ ተመዝግቦ ይቀመጥላቸዋል፡፡ ምክር ቤቱም ሐሳባቸውን አልተቀበለውም፡፡ የእርሳቸው ያ ሁሉ ምክር አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዳይፀድቅ ነበር፡፡

ግዮን፤- በመጨረሻ በኢትዮጵያ ያለው የሰብዓዊ መብት ሁኔታ በምን መልኩ መሻሻል ይችላል ይላሉ?

ያሬድ፡- ኢትዮጵያ አሁን ያለችው ቀውስ ውስጥ ነው፡፡ በፓርላማ ደረጃ ውይይት የተደረገውም አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀውም ቀውስ ውስጥ ስላለን ነው፡፡ ለጊዜው አሁን ላለንበት አስፈሪ፣ አሳሳቢና አደገኛ ችግር መፍትሔ የሚኾነው የአስቸኳይ ጊዜ የቀስው መፍትሔ አፈላላጊ አካል ማቋቋም ነው፡፡ አስቸኳይ የቀውስ መፍትሔ አፈላላጊ ግብረ ኃይል ቶሎ ተቋቁሞ የሁሉም ክልሎች ችግሮች ወደፊት መጥተው ከአዙሪቱ መውጣት አለብን ብዬ አስባለሁ፡፡ የምክክር ኮሚቴው አካሄድ የራሱ ጊዜና አካሄድ አለው፡፡ የሚፈጀው ጊዜም አለ፡፡ የሽግግር ፍትሕም እንዲሁ ጊዜ ወሳጅ ነው፡፡ ሁለቱም ጉዳዮች የተረጋጋ የፖለቲካ ሁኔታን ይፈልጋሉ፡ በተረጋጋ የፖለቲካ አየር ውስጥ ነው ውይይት ማድረግ የሚቻለው፡፡ አሁን ግን ቀውስ ውስጥ ያለን በመኾኑ የቀውስ መፍትሔ አፈላላጊ ብሔራዊ አካል ያስፈልገናል፡፡ ሁሉም ባለድርሻ አካል ያሉበት ወሳኝ የኾኑ ጉዳዮች ላይ ያተኮረና ከገባንበት ቀውስ እንድንወጣ የሚለው ላይ የሚያተኩር ውይይት ቢደረግ መልካም ነው እላለሁ፡፡ ለዚያም የሁሉም ማኅበረሰብ እምነት የሚጥልባቸው ሰዎች ቢሳተፉበት ጥሩ ነው፡፡ ከገባንበት ቀውስ መውጫ መንገድም ይጠቁሙናል ብዬ አስባለሁ፡፡ ግዮን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢያን ስም ከልብ እናመሰግናለን፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

አባቴ ለእኔ አባት ብቻ አልነበረም፤ ለእናቴ ታማኝ ባል፣ ለሁላችንም ደግሞ የደስታ ምንጭ ነበር

"አባዬ… ዛሬ ላለሁበት ማንነት መሰረት የሆንከኝ አንተ ነህ!" ​የአርቲስት...

የአንበሶቹ ትንሳኤ፦ የዳካር እንባ እና የቴራንጋ ድል

​በዳካር ሰማይ ስር ዛሬ ጨረቃ አልወጣችም፤ ይልቁንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ...

የጥምቀት በዓል በመላ ሀገሪቱ በድምቀት እየተከበረ ነው

የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት...

“ሎዛ ዘፀአት”እና “የሎዛ ድርሳናት”ተከታታይ ረጅም ልቦለድ መጻሕፍት ተመረቁ

በጋዜጠኛና ደራሲ መርዕድ እስጢፋኖስ የተጻፉት ሎዛ ዘፀአት(2014 ዓ.ም) እና...