“ባለፉት ዓመታት በተለያየ ዘርፍ በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት ሴክተር እና በልማት ሥራዎች አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል። አደናቃፊ ኹኔታዎችን በመለየትና በመታገል ሥራዎቻችን ለሕዝብ ተደራሽ ለማድረግ ሕዝብን የሚጎዱ ተግባራትን አንጥሮ በማውጣት የታገልንበት መድረክ ነው። ባለፉት ወራት ግብዓት ለሕዝብ ሳይደርስ በሕገወጥ መልክ የመሸጥ አዝማሚያ ታይቷል፡፡ ወደ መድረክ ከመምጣታችን በፊት ከሕዝብ መረጃ መሰብሰባችን አጥፊዎችን ለመለየት አስችሎናል፤ ሐዋሳ ከተማ ላይም ከፍተኛ ሌብነትና ብልሹ አሰራር ታይቷል፡፡ የግምገማ መድረኩ እየተካሄደ ባለበት ከተጠያቂነት ለማምለጥ አቋርጠው በመውጣት የሸሹ ግለሰቦች አሉ፡፡ በተደረገው ማጣራት 97 ሰዎች ከማዳበሪያ ግብዓት ጋር በተያያዘ ለሕግ እንዲቀርቡ እየተሰራ ነው፡፡”
ደስታ ሌዳሞ፣ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር
ኤስ.ኤም.ኤን፣ ነሐሴ 15 ቀን 2014 ዓ.ም
“በ2015 በጀት ዓመት ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች 5 ነጥብ 21 ቢለዮን የአሜሪካን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 3 ነጥብ 64 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል። አፈጻጸሙም የዕቅዱን 69 ነጥብ 79 በመቶ ነው፤ በበጀት ዓመቱ ያጋጠሙ ውጫዊ እና ተቋማዊ የውስጥ ችግሮች የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት እንቅፋቶ ተፈጥረዋል። ከላኪዎች ጋር እየተደረገ ያለው የአፈፃጸም ግምገማ የምክክር መድረክም በስራ ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመፍታት ከወጪ ንግድ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ ጉልህ ፋይዳ ይኖረዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም በተያዘው የ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት የወጪ ምርቶች በጥራት እና መጠን ለውጭ ገበያ የሚቀርቡበትን ስርዓት በማሻሻል ላኪዎች የሚያጋጥማቸውን ችግር መፍትሔ ለመስጠት በቁርጠኝነት ይሠራል።”
ካሳሁን ጎፌ፤ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ
ኢዜአ፣ ነሐሴ 15 ቀን 2015 ዓ.ም
“በክልሉ የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያጎለብቱ የተለያዩ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ ይገኛሉ። በክልሉ ትኩረት ከተሰጣቸው የመሰረተ ልማት ስራዎች መካከል አንዱ የመብራት ፕሮጀክት ነው፡፡ ይህም በተለይ የሀረር የዓለም ቅርስነቷን በጠበቀና የህብረተሰቡን የመብራት ችግር ሊፈታ የሚችል መልኩ እየተከናወነ ይገኛል። ከህገወጥ የቤቶች ግንባታ እና የመሬት ወረራ ጋር በተያያዘ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን በሚመለከትም ህገወጥ የቤት ግንባታና የመሬት ወረራን መከላከል የሁሉም ሀላፊነት ሊኾን ይገባል። በተለይም የደንብ ማስከበር ተቋም ጠንካራ አደረጃጀት ተግባራዊ በማድረግ እና ከፍትህ ተቋማት ጋር በመቀናጀት የህግ የበላይነት የማረጋገጥ ስራ ማጠናከር ያስፈልጋል።”
አቶ ኦርዲን በድሪ፣ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳደር
ሀረሪ ቲቪ፣ ነሐሴ 15 ቀን 2015 ዓ.ም
“በ2015 በጀት ዓመት የታክስ ማጭበርበር ምርመራ ከተደረገባቸው 528 ድርጅቶች ውስጥ 322 የሚሆኑት ሀሰተኛ ደረሰኝ ተገኝቶባቸዋል። ድርጅቶቹ ያቀረቡት የአምሥት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር የሀሰተኛ ደረሰኝ ግብይት ውድቅ ተደርጎ ወለድና ቅጣቱን ጨምሮ 12 ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር እንዲከፍሉ ተደርጓል። ሚኒስቴሩ የታክስ ማጭበርበር ምርመራ ቡድን አቋቁሞ ሕገወጥ ተግባራትን የመከላከል፣ ተግባራቱን በሚፈጽሙ ላይ ደግሞ ርምጃ የመውሰድ፣ ግንዛቤ የማስጨበጥ እና የምርመራ ሥራ እየሠራ ይገኛል። ቡድኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን 864 ተጠርጣሪዎች በሕግ ቁጥጥር ሥር ሆነው ምርመራ እንዲደረግባቸው አድርጓል። በተጨማሪ ሁለት ማተሚያ ቤቶችና 10 ድርጅቶች ሀሰተኛ ደረሰኝ እያተሙ ሲያሰራጩ እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል።”
አቶ ሲሳይ ገዙ፣ በገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ማጭበርበር ምርመራ ዳይሬክተር
ኢፕድ፣ ነሐሴ 14 ቀን 2015 ዓ.ም
“በክልሉ በተለያዩ ከተሞችና ወረዳዎች በነበረው ግጭት የትራንስፖርት ዘርፉ ችግሮች ገጥመውት ቆይቷል። ሆኖም አሁን ላይ በተፈጠረ አንጻራዊ ሰላም በክልሉ ውስጥ ሁሉም የትራንስፖርት አማራጮች አገልግሎት እየሰጡ ይገኛል። ግጭቱ በተከሰተበት ወቅት የትራንስፖርት አገልግሎት በመቋረጡ በርካታ ዜጎች አካባቢያቸውን ለቀው በወጡበት መመለስ ያልቻሉበት አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር፡፡ ይህም በርካቶችን ለእንግልትና ለመጉላላት ዳርጎ ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ግጭቱ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ሀገር አቀፍ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና የሚወስዱበት ወቅት ላይ ስለነበር ተማሪዎች ተፈትነው ወደ መጡበት አካባቢ ለመመለስ አስቸጋሪ ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር፡፡ የክልሉ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ባለሥልጣን በየደረጃው ያለው አመራርና ሠራተኛ የተገኘውን መኪና በመጠቀም ተፈታኝ ተማሪዎች ተማሪ መሆናቸውን የሚገልጽ ባነር በመለጠፍ ወደ ቤተሰቦቻቸው በሰላም እንዲመለሱ ተሠርቷል።”
አቶ ዘውዱ ማለደ፣ የአማራ ክልል ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር
አሚኮ፣ ነሐሴ 13 ቀን 2015 ዓም
“በ2015 በጀት ዓመት የተለያየ ዝርያ ያላቸው 101 ነጥብ 36 ሺህ ቶን የዓሣ ምርት ተገኝቷል። ዓሣ ትልልቅ ሐይቆች በሚገኝባቸው ባህርዳር፣ አርባምንጭ፣ ሐዋሳና ጋምቤላን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ በስፋት እየተመረተ ይገኛል። በዓሣ እርባታ ዘርፍ የነበሩትን ችግሮች በመለየት የማሻሻያ ሥራዎች ተሠርተዋል፤ በተለይም የዓሣ መኖ፣ የጫጩት ጥራትና ብዛትን ጨምሮ የማስገሪያ ቁሳቁሶች ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ሥራ በመከናወን ላይ ይገኛል። በዓሣ ልማት ዘርፍ ለተሰማሩ ከሦስት ሺህ አምስት መቶ በላይ ለሆኑ ዜጎች የተለያዩ ሥልጠናዎች ተሰጥተዋል፤ ሥልጠናው በዓሣ እርባታ፣ በዓሣ ማስገሪያ መረብ ሥራና ጥገና እንዲሁም በመኖ አቅርቦትና ዝግጅት ላይ የሚያተኩር ነው።”
ዶክተር ፋሲል ዳዊት፣ በግብርና ሚኒስቴር የዓሣ ሀብት ልማት ዴስክ ኃላፊ
አዲስ ዘመን፣ ነሐሴ 15 ቀን 2015 ዓም
“በ2016 ዓ.ም. እነዚያን ተሳታፊዎች እንደገና ለማሰባሰብ ዕቅድ አለን፡፡ በእርግጥ ብዙ ጉዳዮች ተለዋውጠዋል፡፡ እነሱን አሰባስበን እንደገና ነገሮችን እንዲገመግሙ ዕቅድ አለ፡፡ ነገር ግን ማይንድ ኢትዮጵያ የብዙ ተቋማት ስብስብ ነው፡፡ ከጅምሩ የተቋቋመበት ዓላማም አገራዊ ምክክር ለማድረግ ነበር፡፡ ነገር ግን አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ስለተቋቋመ ማይንድ ተሰብስቦ ሌላ ትይዩ ምክክር ማድረግ አይችልም፡፡ ስለዚህ እንደ አንድ አካል ማይንድ የሚባል ስብስብ አሁን የለም፡፡ ነገር ግን በዚህ ውስጥ ተሰብስበው የነበሩ ተቋማትና ድርጅቶች በየግል እየተገናኘን እናወራለን፣ እንነጋገራለን ሁሉም ተቋም በየራሱ ይሠራል፡፡”
ንጉሡ አክሊሉ (ዶ/ር)፣ የዴስቲኒ ኢትዮጵያ የምክክር መድረክ ተባባሪ መሥራች
ሪፖርተር፣ ነሐሴ 14 ቀን 2015 ዓም
“ኃይል ማመንጫው በተርባይን ላይ በደረሰ መጠነኛ ችግር ምክንያት ከጥር ወር 2014 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ አመት ከሶስት ወር የኤሌክትሪክ ኃይል ሳያመርት ቆይቷል። በእነዚህ ጊዜያት ቆሻሻ በማቃጠል ለአዲስ አበባ ፅዳት አስተዋጽኦ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ከግንቦት 15 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ተርባይኑ ተጠግኖ ወደ ስራ ገብቷል። በዚህም ኃይል ማመንጫው 12 ነጥብ 5 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት ጀምሯል። ኃይል ማመንጫው አሁን ላይ በአንድ ቦይለር (ቆሻሻ ማቃጠያ) በግማሽ አቅሙ እየሰራ ይገኛል፡፡ ሁለተኛውን ቦይለር ጠግኖ ወደ ስራ ለማስገባት መለዋወጫ ታዞ እየተጠበቀ ይገኛል።”
ብሩክ ኤባ፣ የረጲ ደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ስራ አስኪያጅ
አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ፣ ነሐሴ 15 ቀን 2015 ዓ.ም
