ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን በቅርቡ ካልከፈተች “በጣም ከባድ ጥቃት” ይደርስባታል ሲሉ ትራምፕ አስጠነቀቁ

Date:

ዶናልድ ትራምፕ የሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ “በቅርቡ” ይከፈታል አለበለዚያ ኢራን “በጣም ከባድ ጥቃት ይደርስባታል” ሲሉ ዛቱ።

በሁለቱ አገራት መካከል ስምምነት ሊፈረም ይችላል የሚለው ተስፋ እየጨመረ በመጣበት በአሁኑ ወቅት የዓለም ነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ ቅናሽ አሳይቷል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ እና የገንዘብ ሚኒስትሩ ስኮት ቤሴንት መርከቦች ከዚህ ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ በወሽመጡ በኩል ያለ ምንም ችግር ማለፍ እንዲችሉ የሚያደርግ ውይይት መካሄዱን እና አንዳንድ ለውጦች መታየታቸውን ከገለጹ በኋላ ፕሬዝዳንቱ ለፎክስ ኒውስ ቃለ መጠይቅ ሰጥተዋል።

የዓለም ነዳጅ አቅርቦት ሊሻሻል እንደሚችል ዜና ከተሰማ በኋላ የአንድ በርሜል የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በ5 በመቶ ገደማ ቀንሶ 80 ዶላር (60 ፓውንድ) ተሽጧል።

ነገር ግን ባለፉት ወራት የተደረጉት ውይይቶች ግጭቱን ለማርገብ አለመቻላቸው የነዳጅ ገበያው እንዲዋዥቅ አድርጎታል፣ በዚህም ምክንያት አሽከርካሪዎች በነዳጅ ዋጋ መጨመር ተጎድተዋል።

ትራምፕ ትናንት በካሊፎርኒያ ጉብኝት እያደረጉ በነበረበት ወቅት “በጣም ጥሩ ውይይት እያደረግን ነው” ሲሉ ኢራን ለወራት የዘለቀውን ግጭት ለማስቆም ስምምነት ላይ ለመድረስ ፍላጎት እንዳላት ተናግረዋል።

የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) “በሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ ደቡባዊ ክፍል ባለው ዓለም አቀፍ የውሃ መስመር በኩል ለማለፍ ለሚፈልጉ የንግድ መርከቦች ሁሉ ነፃ እና ክፍት ነው” ብሏል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከኢራን እና ኦማን ጋር ተጨማሪ መርከቦችን በባሕረ ሰላጤው ውስጥ ስለማሳለፍ የሚደረጉት ውይይቶች ለውጥ መታየት ጀምረዋል ሲሉ ተደምጠዋል።

ማርኮ ሩቢዮ ለጋዜጠኞች “በእነዚያ ውይይቶች ላይ መሻሻሎች ታይቷል፤ ግን እስካሁን የመጨረሻ ውሳኔ ላይ አልደረስንም። ይህ በቅርቡ እንደሚከናወን ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉ ተናግረዋል።

ቤሴንት በበኩላቸው የሆርሙዝን የባሕር ወሽመጥ እንደገና ለመክፈት የሚያስችል ስምምነት ማክሰኞ ወይም ረቡዕ ሊደረስ ይችላል ሲሉ ተደምጠዋል።

“ዛሬ [ማክሰኞ] ወይም ነገ [ረቡዕ] ወሽመጡን ለመክፈት እና ግጭቱን አርግቦ ወደ መደበኛ ሁኔታ ለመሸጋገር ስምምነት ላይ ልንደርስ እንችላለን” ሲሉ ለሲኤንቢሲ ተናግረዋል።

ኢራን በወሽመጡ በኩል የሚያልፉ መርከቦችን ቀረጥ እንድታስከፍል ይፈቀድ እንደሆን ተጠይቀው “የመንቀሳቀስ ነፃነት ይሆናል” ሲሉ መልሰዋል።

የአሜሪካ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ድርድር እየተካሄደ መሆኑን ቢገልጹም፣ሊፈረም የሚችለው ስምምነት ምን ሊመስል እንደሚችል ዝርዝር መረጃ አልወጣም።

ኢራን ከአሜሪካ ጋር ድርድር እንዳልተቀመጠች እንዲሁም ምንም ዓይነት ዕቅድ እንደሌላት ገልጻ በምትኩ ከኦማን ጋር እየተነጋገረች መሆኑን አስታውቃለች።

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ በኩል ለሚያልፉ መርከቦች አዲስ አሰራር መዘርጋትን በተመለከተ ከኦማን ጋር የተደረጉት ውይይቶች አዎንታዊ ነበሩ ብለዋል።

በዋሽንግተን እና ቴህራን መካከል ቁልፍ አሸማጋይ የሆነችው ኳታር ከሌሎች አደራዳሪዎች ጋር በመሆን ለጦርነቱ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ ለማግኘት ጥረት እያደረገች መሆኑን ገልጻለች። ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ ምንም ዓይነት ቀጥተኛ ውይይት እንዳልታቀደች አስታውቃለች።

ግጭቱ እየገፋ ሲሄድ አሜሪካ ዒላማውን ለይቶ የሚመቱ የረጅም ርቀት ሚሳኤሎቿን ክምችት በሙሉ ማለት በሚቻል ደረጃ ተጠቅማለች ሲሉ ለጉዳዩ ቀጥተኛ ቅርበት ያላቸው ሁለት ምንጮች ለቢቢሲ የአሜሪካ የዜና አጋር ሲቢኤስ ኒውስ ተናግረዋል።

የሆርሙዝ ወሽመጥ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል በሚደረገው ድርድር ማዕከላዊ ነጥብ ነው።

ግጭቱ በየካቲት ወር መጨረሻ ከመጀመሩ በፊት በወሽመጡ በኩል አንድ አምስተኛ የሚሆነውን የዓለም አቀፍ የነዳጅ እና ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ አቅርቦቶችን ይጓጓዙ ነበር።

BBC

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር በዓለም የምግብ ምርምር ድርጅት ሹመት ተሰጣቸው

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር እና የአግራ (AGRA) የቦርድ ሰብሳቢ...

አቶ ሳሙኤል ታፈሰ በካናዳ ሀገር ሊሸለሙ ነው

የሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ መስራችና ሊቀመንበር አቶ ሳሙኤል ታፈሰ በንግዱ...

በምክክሩ ወቅት በሀሳብ ልዩነት “አድማ የመቱ” ነበሩ

ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በ22ኛው ቀን ውሎው በስልታዊ ቡድን ደረጃ...

በፌደራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል ያለዉ ግጭት እንዳሳሰበው የአውሮፓ ሰላም ፋውንዴሽን ገለፀ

የአውሮፓ ሰላም ፋውንዴሽን  በኢትዮጵያ ፌደራላዊ  መንግሥት እና በህዝባዊ ወያኔ...