በሞዛምቢክ 6 ሺሕ የሚደርሱ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ታግተው የሚገኙ ሲሆን፤ ዜጎቹን ወደ ሀገር ለመመለስ የፋይናስ እጥረት እንደገጠመው የሴቶችና ማህበራዊ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በሚኒስቴሩ የሰዎች ዝውውር ማስተባበሪያ የተመላሽ ዜጎች ክትትል መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ደረጄ ተጊበሉ ነገሩኝ ሲል አሐዱ ሬዲዮ እንደዘገበው ፤ 6 ሺሕ የሚሆኑት ታጋቾች በሞዛምቢክ እንደሚገኙና “እንደ ዛምቢያ ባሉ ሀገራትም በውል የማይታወቁ ዜጎቻቸን በእስር ቤት ውስጥ የሰብዓዊ ጥሰት እየተፈፀመባቸዉ እንደሚገኙ መረጃዉ ደርሶናል” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
መንግሥት አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ከፍተኛ የትራንስፖርት ወጭ ስለሚጠይቀው፤ ከአጋር ድርጅት ጋር በመነጋገር እርዳታ እየተጠየቀ መሆኑን ጨምረው የየቆሙት ሀላፊው ዜጎችን በኢትዮጵያ አየር መንገድ በቀጥታ ከፍሎ ለማምጣት አየር መንገዱ የቢዝነስ ሴክተር ስለሆነ ከፍተኛ ወጭ ስለሚጠይቅ አንዱ ችግር መሆኑንም አስረድተዋል።
“ከውጭ ሀገር ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ ነው” የሚሉት መሪ ሥራ አስፈፃሚው፤ “መንግሥት በራሱ ውል ፈርሞ ከስደት ለሚመለሱ ዜጎች በጀት ከመደበ በሗላ፤ ወደ ሥራ ሲገባ ከጠበቀዉ በላይ እየሆነበት ነው” ሲሉም መናገራቸውን ነው ዘገባው ያመላከተው፡፡
በሕገ-ወጥም ሆነ በሕጋዊ መንገድ ከሀገር የሚወጡ ዜጎችን የኢትዮጵያ መንግሥት የሰብዓዊ የመብት ጥሰት እንዳይፈፀምባቸው የውጭ ዲፕሎማሲውን አጠናክሮ ይቀጥላል የሚሉት ደረጄ፤ “እስካሁን ባለው አፈፃጸምም ከአንዳንድ ሀገራት ዉጭ፤ ዜጎቻችንን በሰላማዊ መንገድ እየተመለሱ ነው” ሲሉ ጠቁመዋል።
