ኢትዮ ቴሌኮም የሦስት ዓመት መሪ እድገት ስትራቴጂ ማጠቃለያ ሪፕርት እንዲሁም የ2017 በጀት ዓመት ሪፓርት ማጠቃለያ በዛሬው ዕለት በማካሄድ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ ተቋሙ በበጀት ዓመቱ 462 ሺሕ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች እንደተደረጉበት አስታውቋል፡፡
በበጀት ዓመቱ 1 ሺሕ 683 አዲስ የሞባይል ጣቢያዎች መተከላቸውን የተናገሩት የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ፤ “ይህም በመሆኑ ከዚህ ቀደም የኔትዎርክ እና ሞባይል አገልግሎት የማያገኙ አካባቢዎች አገልግሎቱን እንዲያገኙ ያስቻለ ነው” ብለዋል።
“በዚህም ኢትዮ ቴሌኮም ያሉት ታዋሮች ብዛት 10 ሺሕ 10 ደርሷል” ያሉት ሥራ አስፈጻሚዋ፤ ከ1 ሺሕ 683 ውስጥ 954 ጣቢያዎች አገልግሎት በቅርበት የማያገኙ የነበሩ ቦታዎች ላይ የተገነቡ ሲሆን፤ 6 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም በ4ጂ ኔትዎርክ 512 ከተሞችን እና በ5ጂ ደግሞ 16 ከተሞችን ማገናኘት መቻሉን ገልጸዋል።
የፋይበር ተደራሽነት በተመለከተ በአጠቃላይ 22 ሺሕ 673 ነጥብ 1 መድረሱን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ኢትዮ ቴሌኮም በበጀት ዓመቱ 462 ሺሕ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች የተደረጉበት ሲሆን፤ ምንም አይነት ጥቃት እንዳልደረሰበት አስታውቀዋል።
ኩባንያው በአዲስ ጅማሮ በአዲስ እይታ የጀመረው አዲሱ የ2017 በጀት ዓመት የስትራቴጂ ዘመኑ ሦስተኛው ዓመት መሆኑንም ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል።
“በበጀት ዓመቱ ኩባንያው በተሰማራበት በሁሉም መስክ መሪነቱን በማስቀጠል በሀገሪቱ የቴሌኮም ዘርፍ የሕዝባችን ማህበረሰባዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁለንተናዊ እድገት ላይ አዎንታዊ አስተዋጽዖ የሚያመጡ፣ የተቋማትን አሰራር ቅልጥፍናና ምርታማነትን የሚያሳድጉ እንዲሁም፤ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ወሳኝ ሚና ያላቸው ዘርፎች አቅማቸውን አሟጠው እንዲጠቀሙ አድርጓል” ብለዋል።
ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በማስታጠቅ የተጀመረውን የሀገሪቱ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የማፋጠን እና ዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታን ማሳለጥን ታሳቢ ያደረገ እቅድ በማዘጋጀት ወደ ሥራ መገባቱን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ጨምረው አስታውሰዋል።
(አሐዱ ሬዲዮ)
